ዘረኛው የመለስ ዜናዊ አገዛዝ ታማኝነታቸው እየመነመነ የመጣ ባለ ከፍተኛ ማዕረግ የጦር አባላትን በጡረታ አባረረ። አብዛኞቹ ተባራሪዎች የሌሎች ብሔረሰብ አባላት መሆናቸው ታወቀ

የወያኔ መከላከያ ሚንስቴር ሰሞኑን ይፋ ባደረገው ዜና በወያኔ የመተካካት ፖሊሲ በመከላኪያ ሠራዊት ውስጥ ካሉት ከፍተኛ ባለማዕረጎች ውስጥ 13 ጀኔራሎችና 303 ሌፍቴናንት ኮሌነልነትና ሙሉ ኮሌነል ማዕረግ ያላቸው አባላት በጡረታ ስም ከሰራዊቱ መገለላቸው ታውቆአል።

የግንቦት7 ምንጮች መረጃ እንደሚያመለክተው ግን በጡረታ ከተገለሉት አብዛኞቹ ከቀርብ ጊዜያቶች ወዲህ በመላው አገሪቱ ውስጥ በተከሰተው የኑሮ ውድነትና እየተስፋፋ በመጣው የፖለቲካ አፈና ምክንያት ህዝባዊ አመጽ ቢቀሰቀስ ከአገዛዙ ጎን መቆማቸው ጥርጣሬ ውስጥ የገባ ባለማዕረጎችን ከሰራዊቱ ውስጥ አስቀድሞ ለማስወገድ የተወሰደ እርምጃ እንደሆ ነው።

በሰራዊቱ ውስጥ የፈላጭ ቆራጭነት ሥልጣን ያለውና በዕድሜም ቢሆን ከአብዛኛዎቹ ተሰናባቾች በአንጋፋነት ላይ ካለው ሳሞራ ዩኑስ ጋር በፈጠሩት ግጭት ለመለስ ዜናዊ ቡድን ታማኝ መሆናቸው ጥርጣሬ ውስጥ በመግባቱ ከሰራዊቱ ውስጥ ገለል እንዲሉ ከተፈለጉት ጥቂት የትግራይ ተወላጆች በስተቀር አብዛኞቹ ተሰናባቾች የአማራ፤ የኦሮሞና የሌሎች ብሄረሰብ ተወላጆች እንደሆኑ የሚናገሩ ምንጮች፤ ትግርኛ ተናጋሪዎቹ ወደሌላ ሲቪል መሥሪያ ቤትና በህወሃት ሥር በሚተዳደሩ ንግድ ድርጅቶች ለእስከዛሬው አገልግሎታቸው እና ህወሃት ለሁለት በተከፈለበት ወቅት ድጋፋቸውን ለመለስ ቡድን በመስጠት እንዲያንሰራራ በማድረግ ላበረከቱት ውለታ የሚመጥን ሹመት እንደተዘጋጀላቸው ገልጸዋል።

እንደመረጃ ምንጮቻችን መረጃ ከተባራሪዎቹ ወገን የሆኑት የአማራ የጦር መኮንኖች አብዛኞቹ ከነጀኔራል ተፈራ ማሞ ጋር የቅርብ ጓደኝነት የነበራቸው በመሆናቸው ላለፉት 3 አመታት እያንዳንዱ እንቅስቃሴያቸው በህወሃት ወታደራዊ ደህንነት ክትትል ሲደረግባቸው የኖረ ነው።

መለስ ዜናዊ ለህወሃት አንጋፋ ታጋዮች ከፍተኛ የጦር መኮንንነት ማዕረግ ባደለበት ወቅት ለተለጣፊ ድርጅቶቹ በሰጠው ኮታ ከኦህዴድ ለጄነራልነት ማዕረግ የበቃው ባጫ ደበሌም ከተባረሩት ጄኔራሎች መካከል አንዱ መሆኑ ታውቆአል። ባጫ ደበሌ የህወሃት አለቆቹን ተፈጥሮ በለገሰችው የዳንስ ችሎታው ያዝናና የነበረ መሆኑን በአንድ ወቅት የህወሃት የፕሬስ ሃላፍ የነበረውና ድርጅቱን ለቆ ከአገር ከወጣ ጊዜ ጀምሮ የወያኔን ወንጀሎች በማጋለጥ ሥራ ላይ የተጠመደው ደራሲ ተስፋዬ ገብረአብ ባሳተመው የደራሲው ማስታወሻ በሚባለው መጽሐፍ ለንባብ ማብቃቱ ይታወሳል።

ከተባረሩት ታዋቂ የትግራይ ጄኔራሎች መካከል በአንድ ወቅት ለመለስ ዜናዊ እጅግ ታማኝ የነበረውና ቦኋላ ግን ታማኝነቱ ጥያቄ ውስጥ በመግባቱ ከሳሞራ የኑስ ጋር ግጭት ውስጥ ገብቶ እንደነበር የታወቀው ዮሀንስ ገብረመስቀል ይገኝበታል ተብሎአል።

መለስ ዜናዊን በመከላኪያ ሰራዊቱ ውስጥ የጀመረው ቅነሳ በትግራይ የበላይነት ምክንያት በሰራዊቱ ውስጥ ጎልቶ እየታየ ያለውን ኩርፊያና ተቃውሞ የበለጠ የሚያባብስ እንደሆነ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የግንቦት 7 ሬዲዮ ባለፈው ቅዳሜ የዜና እወጃው የወያኔ የመከላኪያ ሚንስቴር ሚንስትር ሲራጅ ፈርጌሳ የኦሮሞ ብሄረሰብ ተወላጅ ነው ያለው በስህተት ስለሆነ የስልጤ ብሄረሰብ ተወላጅ ተብሎ አንዲስተካከል ከይቅርታ ጋር እንጠይቃለን።