መለስ ዜናዊ ከማንም አይሻልም!!!
መለስ ዜናዊ ከደርጉና ከአጼዎቹ ጋር ራሱን እያወዳደረ እኔ እሻላችኋለው እያለ ሲሰብክ እነሆ ሦስት አስርተ ዓመታትን አስቆጥሯል። ይሄንንም ስብከት ያመኑ ብዙ ሰዎች መኖራቸውም እውነት ነው።
መለስ ዜናዊ ዘመኑ ከደረሰበት የእደገት ደረጃ እጅግ ወደ ኋላ እርቆ የሚጓዝ ክፍ ዘረኛ በመሆኑ ሁል ግዜ ራሱን የሚያወዳድረው ከሙታን ጋር ነው እንጂ ከህያዋን ጋር አይደለም። በህያዋን መንደር የሚያቆመውን ምንም በጎ ተግባር ስላልሰራ ሙታንን ፍለጋ መቶና ሃምሳ ዓመት ወደ ኋላ ይጓዛል።
መለስ ዜናዊን ከሙታን ጋር እያወዳደሩ እርሱ ይሻላል ማለት ለማሰብ ፍላጎት ከማጣት የሚመነጭ የሞኝ ሃሳብ ነው። ለማሰብ ፍላጎት ያለው ሰው ምንም እንኳን ቀደመው የነበሩ ገዥዎች አምባገነንና ጨፍጫፊ ቢሆኑም እንደ መለስ ዜናዊ በዘረኝነት የተለከፉ አለመሆናቸውን ይረዳ ነበር።መለስ ዜናዊ ተወልደኩበት የሚለውን ብሄር “እናንተ እኮ እንደሌሎቹ ሳትሆኑ ወርቅ ናችሁ “ብሎ በአደባባይ መናገሩን ሰምተናል። ለማሰብ ፍላጎት ያለው ሰው ቀደመው የነበሩ ገዥዎች በአገሪቱ ሉዓላዊነት ላይ ከማንም ጋር እንደማይደራደሩ ማየት ይችል ነበር። በተቃራኒው ደግሞ መለስ ዜናዊ የቀደሙት ዜጎች ያቆዩልንን ድንበር እያፈረሰ ለባእዳን የመስጠቱ ጉዳይ ይከሰትላቸው ነበር። መለስ ዜናዊ በታሪክ፤ በሃይማኖትና በባህል የተሳሰረውን ወንድማማች ህዝብ በግንባር ቀደም ተዋናይነት በመለያየት በአገርና በታሪክ ላይ የፈጸመው የክህደት ወንጀል ውሎ ሳያድር የበሬ ግምባር በምታክል መሬት ላይ ትርጉም አልባ ጦርነት አስነስቶ ያስፈጃቸው ከመቶ ሺህ በላይ ወጣቶችን ክንቱ የህይወት መስዋዕትነት ያስተዋለ የሰውየውን መሰሪነት በእስካሁን ታሪካችን ከነበሩን መሪዎች ስለመሻሉ ሳይሆን ሉአላዊነታችንንና ነጻነታችንን በመግፈፍ ባሪያ ሊያደርጉን ሞክረው ካልተሳካላቸው ባዕዳን ወራሪዎች ተርታ እንደሚያሰልፈው በተገነዘቡ ነበር። የአገርን አንጡራ ሃብት በመዝረፍና በሙስና በመጨማለቅም መለስ ዜናዊን የሚስተካከል በታሪካችን ገጥሞን እንደማያውቅ ይረዳ ነበር።
መለስ ዜናዊ ክፉ ዘረኛ ነው። በአንድ አገር ህዝብ መካከል የጠብ ግድግዳ እየገነባ መኖሩ ደህና ተደርጎ የሚታወቅበት ምግባሩ ነው።ከአንድ አገር ህዝብ መካከል ተወለድኩበት የሚለውን ብሄረሰብ ጠቅሶ ”አንተ እኮ እንደሌሎቹ አይደለህም ወርቅ ነህ እንጂ” ማለቱን ከአንደበቱ ሰምተናል። ይህ እንዲያው የአፍ ወለምታ ሳይሆን ሆን ተብሎ ታስቦበት የተነገር ነው። በክፉም በደጉም አብሮ ተከባብሮና ተሳስሮ የኖረ ህዝብ በአንድነት ቁሞ ስለአንድ ነገር በጋራ እንዳይመክር ለማድረግ የተጠቀመበት መሰሪ ዜዴ ነው። ከቀደሙት የአገራችን አምባገነኖች መካከል እንዲህ ያለ ነገር በአደባባይ ሲናገር የተሰማ አልታየም። ከመለስ ዜናዊ ቀድመው የነበሩ እንዲህ ያለ ነገር ቢናገሩ እንኳ ዘመኑና የነበሩበት የእድገት ደረጃ ስለሆነ የመለስ ዜናዊን ያክል የሚያሳፍርና የሚያሳስብ አይሆንም። እንዲህ ያለ ነውር ነገርን በአደባባይ ለመናገር ትንሽም ቢሆን እፍረት የማይሰማው ግለሰብ እንደምን ሁኖ ከቀደሙት ገዥዎች ሊሻል ይችላል?
እርግጥ ነው ከመለስ ዜናዊ ቀድመው በአገሪቷ ጫንቃ ላይ ተጭነው የነበሩ ገዥዎች አምባገነኖች ናቸው።እነርሱም ቢሆኑ ዴሞክራት ነን ሲሉ አልተሰሙም። ምንም እንኳ አምባገነን ቢሆኑም በአገራቸው ሉዓላዊነት ላይ ከማንም ጋር ተደራድረውና የአገሪቷን ጥቅም አሳልፈው ሲሰጡ ታይተው አይታወቁም። የአገሪቷን ዳር ድንበር አስፍተውና አስከብረው ኑረው አለፉ እንጂ እንደመለስ ዜናዊ የአገሪቷን ድንበር አፍርሰው ለባእዳን አልሰጡም።በዚህ ረገድ ቀድመው የነበሩ ገዥዎች ቢያንስ ከመለስ ዜናዊ ይሻላሉ። መለስ ከጋምቤላ አንስቶ እስከ ጎንደር ድረስ ያለውን ለም መሬት ኢትዮጵያዊ ገበሬዎችን አፈናቅሎ ለባእዳን መስጠቱ የቅርብ ግዜ ትዝታችን ነው። እንዲህ ያለ ቡድን እንደምን ሁኖ ከቀደሙት ገዥዎች ይሻላል ሊባል ይችላል?
ከመለስ ዜናዊ ቀድመው የነበሩ ገዥዎች አገሪቷ የእኔ ነች አሉ እንጂ አገራቸውን እንደ ሌላ ባእድ አገር አያዩም ነበር። መለስ ዜናዊ ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያዊያን ካለው ብርቱ ጥላቻ የተነሳ “ይህች አገር” ይላል እንጂ አንድም ቀን “ወገኖቼ” ወይም ደግሞ “የተከበራችሁ የአገሬ ሰዎች” ሲል ተሰምቶ አይታወቅም። በመለስ ዜናዊ እምነት አገሪቷ የእርሱ አይደለምችም። ኢትዮጵያዊያንም ወገኖቹ አይደሉም። የእርሱ ያልሆነችን አገር በተቻለው ሁሉ ማዋረድና መዘርፍ እንጂ ክብሯን መጠበቅ መለስ ዜናዊ የተጠራበት ተልእኮው አይደለም። በዚህም መሠረት አገሪቷን እንደ አገር ሊያቆሙ የሚችሉ እሴቶችን በሙሉ ለማጥፋት ብርቱ ጥረት አድርጓል።አንዱን ሃይማኖት ከሌላው ጋር አጋጭቶ የንጹሃን ደም እንዲፈስ አድርጓል።አንዱን ብሄር የሌላው ብሄር ጠላት ነው ሲል ጽፏል ሰብኳል። በአገሪቷ ውስጥ እውነት እንዳይነገርና እንዳይለመድ አድርጓል። ዜጎችም በወንድሞቻቸውና በእህቶቻቸው ላይ በሃሰት እንዲመሰከሩ በማስገደድ ይህም በመገናኛ ብዙሃን ለህዝቡ እንዲደርስ አስደርጎ የዜጎችን ቅስም ለመስብር ጥረት አድርጓል። ቢያንስ ከመለስ ዜናዊ በፊት የነበሩ ገዥዎች በእንዲህ ያለ ነውር ውስጥ ባለመሳተፋቸው ከመለስ ዜናዊ ይሻላሉ።
የመለስ ዜናዊ አስተዳደር ከቀደሙት የሚለይበት ሌላው መልኩ ደግሞ ዝሪፊያ ነው። መለስና የኤልዛቤል መንፈስ ነች ተብላ የምትታወቀው ሚስቱ አዜብ መስፍን የአገሪቷን ሃብት በመዝረፍ ተግባር ላይ ተጠምደዋል። ይህም ዝሪፊያቸው በተባበሩት መንግስታት ሪፖርት ላይ ቀርቦ ሰምተነዋል። እስክ ዛሬ ድረስ ህገ ወጥ በሆነ መንገድ ከአገሪቷ ተዘርፎ በውጭ አገራት ባንክ ውስጥ የተደበቀው ገንዘብ ከአስራ አንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ ሁኗል። እንዲህ ያለ ዝሪፊያ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ታይቶ አይታወቅም። ይህን ዝሪፊያ የሰማ ሰው እንደምን ሁኖ መለስ ዜናዊ ከቀደሙት ገዥዎች ይሻላል ብሎ ሊናገር ይችላል ?
በአጠቃላይ አነጋገር መለስ ዜናዊ ከቀደሙት ገዥዎች ይሻላል ብሎ ይህን የዘራፊና የዘረኛ ቡድን መደገፍ ትክክል አይደለም። መለስ ዜናዊ ከቀደሙት ነገስታትና ሌሎች አይሻልም። መለስ ዜናዊ ዘረኛ፤ ውሸታምና ዘራፊ የሆነ ግለሰብ ነው። የሚመራውም ቡድን እንዲያው ነው። ከቀደሙት የሚሻልበት በጎ ነገር ሳይኖረው ይሻላል ብሎ መደገፍ አሳፋሪ ነው።እንዲህ የሚሉ ሰዎች ”Animal Farm” በተባለው መጽሃፍ ውስጥ ምንም ነገር ሳያስቡ “ሁለት እግሮች ሁሉ መጥፎ፤ አራት እግሮች ሁሉ ጥሩ” እያሉ ከሚያላዝኑ በጎች የሚለዩ አይሆኑም።
ስለሆነም እያሰቡ አገሪቷንና ዜጎቿን የሚያዋርዱ ሃይሎችን ሳያስቡ መደገፍ ከተጠያቂነት የሚያስመልጥ አይደለም። ግንቦት ሰባት ሁለቱንም ሃይሎች ለይቶ አያያቸውም።
ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ !!!