በስዊድናዊያኑ ላይ የተላለፈውን የግፍ ብይንና የቅጣት ውሳኔን እንቃወማለን፤ የኢትዮጵያዊያኑ ጉዳይ ደግሞ ያስጨንቀናል!!!
የመለስ ዜናዊ የይስሙላ ችሎት በስዊድናዊያን ጋዜጠኞች ማርቲን ሽብየ እና ጆአን ፐርሰን ላይ የጥፋተኝነት ብይን ከሰጠ በኋላ እያንዳንዳንዳቸውን በአስራ አንድ ዓመታት ጽኑ እስራት መቅጣቱ መላውን ዓለም አስቆጥቷል።
ግንቦት 7: የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄም እነዚህን የመለስ ዜናዊ የይስሙላ ችሎት ውሳኔዎችን አጥብቆ ያወግዛል።
እርግጥ ነው ለእኛ ለኢትዮጵያዊያን እነዚህን የመሰሉ ፍርደ ገምድል ውሳኔዎች ለሃያ ዓመታት የኖርንበት ነውና አዲስ ነገር አይደሉም።
እንዲያውም ከዚህ ቀጥሎ ከሞላ ጎደል የሚከተሉት ኩነቶችን በቅደም ተከተላቸው እንደምናይ ከወዲሁ መገመት ይቻላል።
- ጋዜጠኞቹ ይግባኝ ከጠየቁ፤ ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት የሥር ፍርድ ቤት ውሳኔን ያፀናል፤
- ዓለም ዓቀፉ ማኅበረሰብ ዲፕሎማሲያዊ ጥረቱን ያጠናክራል፤
- መለስ “በምንም ዓይነት ለውጭ ተጽዕኖ አንንበረከክም” የሚል መግለጫ ይሰጣል፤
- “የአገር ሽማግሌዎች” በጉዳዩ እንዲገቡበት ይደረጋል፤
- ስዊድናዊያኑ ጋዜጠኞች “ይቅርታ ጠየቁ” ተብሎ ይፈታሉ።
ይህ ነው የመለስ ዜናዊ ውሉ የጠፋበት ዘረኛ፣ ፊውዳላዊና ፋሽስታዊ የዳኝነት ሥርዓት።
ስዊድናዊያኑ ማርቲንና ፐርሰን እንደ ኢትዮጵያዊያኑ ጋዜጠኞች ሰቆቃ አይፈፀምባቸውም ይሆናል፤ ቢፈፀምባቸውም በኢትዮጵያዊያን ላይ እንደሚሆነው የከፋ አይሆም። ማርቲንና ፐርሰን እንደ ርዕዮት ዓለሙ በጨለማ ቤት ለሳምንታት አይዘጋባቸው፤ እንደ እስክንድር ነጋና ውብሸት ታየ አይረገጡ፣ አይሰደቡ፣ አይተፋባቸው ይሆናል። ያም ሆኖ ግን በኢትዮጵያዊያን ላይ እየደረሰ ያለውን ሰቆቃ በቅርበት እየታዘቡት ነው። ያዩትና የሰሙትን ሁሉ በአዕምሮዎቻቸው እየመዘገቡት ነው ብለን ተስፋ እናደርጋለን።
ግንቦት 7፣ እነዚህ ጋዜጠኞች እስካሁን ለከፈሉትና ወደፊትም ለሚከፍሉት መስዋትነት ከፍተኛ አክብሮት አለው። ነፃ ባለሙያዎች ናቸውና ያለአንዳች ቅድመ ሁኔታ መፈታት አለባቸው ብሎ ያምናል። ከዚህም ጋር ግን እንደነሱ የሚከራከርላቸውና የሚደራደርላቸው የሌላቸውን ኢትዮጵያዊያኑ ጋዜጠኞች ርዕዮት ዓለሙ፣ እስክንድር ነጋ፣ ውብሸት ታየ እና ሌሎችም እየደረሰባቸው ያለው ስቃይና መጨረሻቸው በእጅጉ ያስጨንቀዋል። ግንቦት 7፣ ኢትዮጵያ ጋዜጠኞች ቁም ስቅላቸውን የሚያዩባት አገር መሆኗ እንዲያከትም በጽኑ ይታገላል።
መለስ ዜናዊና ሎሌዎቹ የመረጃን ኃይል ጠንቅቀው ያውቃሉ። በረሃ በነበሩበት ጊዜ በስውር ያስገቧቸው ጋዜጠኞች ባቀረቧቸው ዘገባዎች መጠቀማቸውን ያስታውሳሉ። እነሱ ያኔ ያደረጉትን ሌሎች ዛሬ እንዳይደግሙት መንገድ መዝጋት ይፈልጋሉ።
- ለመሆኑ እነርሱ በረሃ በነበሩበት ወቅት ምን ያህል ጋዜጠኞችን በስውር ያስገቡ እንደነበር የሚታወቅ አይመስላቸውም?
- ከእነዚህ ጋዜጠኞች ብዙዎቹ ዛሬም በሕይወት ላይ ያሉ መሆናቸውን ዘነጉት?
- አንድ ነገር ወያኔ ሲፈጽመው ሰናይ፤ ሌላው ሌላው ሲያደርገው ውግዝ የሚሆነው ለምንድነው?
ግንቦት 7 ከእንዲህ ዓይነቱን የመረጃን አፈናና የጋዜጠኞች ስቃይን ማስቆም የሚቻለው የመለስ ዜናዊን ዘረኛ አምባገነን አገዛዝ አስወግደን በምትኩ ፍትህ፣ ነፃነት፣ ዲሞክራሲና እኩልነት የሰፈኑባት ኢትዮጵያን ስንገነባ ነው ብሎ ያምናል።
ስለዚህም መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ለዚህ ታላቅ ግብ ቆርጦ እንዲነሳ ጥሪ ያደርጋል።
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!!