History | ያልሰመረው የቤልጅየም ኢትዮጲያን የመግዛት ውጥን

(ወልደብርሃን ስሁል) የዛሬ መቶ ሰባ ዓመት አካባቢ አንዲት “ሚጢጢየ” አውሮፓዊት ሃገር ማንም ሳይቀድማት ኢትዮጵያን በጉልበት ይዛ ቅኝ ለመግዛት “ክተት ሰራዊት ምታ ነጋሪት ብላ” ቆርጣ ተሰናዳች። በቆዳ ስፋቷ አንድ ትልቅ ወረዳ እምታክል ናት። አፍሪካ ውስጥ ግን የራሷን መቶ እጥፍ የሚያክል ግዛት መቆጣጠር እሚያስችል አቅምና እብሪት ነበራት። ህልሟን ለማሳካት ፕሮጀክት ቀርፃ feasibility study አካሄደች። እቅዷና ጥናቷ ያነጣጠረውም በዘመነመሳፍንቷ ኢትዮጵያ ላይ ነበር። የቀይ ባህር አካባቢ ደከም ባለ አውሮፓዊ ሃይል እንዲያዝ ትሻ የነበረችው ታላቋ ብሪታንያም ይሁንታ ሰጠቻት፤ በወርራ ቅኝ ልትገዛን ቆርጣ ለተነሳችው ቤልጅየም! ቤልጅየም ለኢትዮጵያ ያሰበችው ፕሮጄክት ብሎንዲል ከሚባል እብሪተኛ ሰው የጀብድ ልክፍት ጋር የተቆራኘ ነበር። ግብፅ በወርኔር ሙዚንጀር፤ ጣልያን በፔትሮ አንቶኖሊ ምን እንዳደረጉን ጠንቅቀን እናውቃለን። ከነሱ በፊት ቀድሞ ስለተሰናዳልን የብሎንዲል Humanitarian Mission ግን ብዙ አናውቅም። ነገሩ ያስገርማል እንጂ አያስቅም። “ገድለ‐ብሎንዲል” በጥቂቱ እንዲህ ነበር፦ የቤልጂግ መንግስት መጀመርያ በ1841 ከፍተኛ በጀት መድቦ ብዛት ያላቸው የስለላ ወኪሎቹን ወደ ግብጽ አሰማራ። ወኪሎቹም “ለሳይንሳዊ ጥናት እና ለሰብአዊ ተልእኮ” በሚሉ ሽፋኖች ካይሮ ላይ ከትመው ስለ ኢትዮጵያ ጥናት ጀመሩ። ማንኛውንም ዓይነት መረጃ በዝርዝር እየቀራረሙ ከሚያቀርቡት ሪፖርት የቤልጂየም ንጉስ ቀዳማዊ ሊዮፖልድ “በውስጧ ሁከት የነገሰባት ኢትዮጵያን” በቀላሉ መውረርና መቆጣጠር እንደሚችል አመነ። ለወረራም ቋመጠናም የሰላዮቹ አስተባባሪ በአካል ወደ ኢትዮጵያ ሂዶ “ሰብዓዊ ተልእኮ” የሚል ስም ያለው ጉብኝት እንዲያካሂድ አዘዘው። ዋናው ተልእኮው ግን ለወረራ ምቹ ሁኔታ እንዲፈጥር እና ባስቸኳይ እሚተገበር የድርጊት መርሃ ግብር እንዲያዘጋጅ ነበር። […]