አቡጊዳ – በእድሜያቸዉ ዘመን ኢትዮጵያና ኤርትራ አንድ ሆነዉ ማየት እንደሚናፍቁ ዶር በረከተ ሃብተ ስላሴ ገለጹ

ዶር በረከተ ሃብተ ስላሴ ከጥቂት ወራት በፊት፣ የቆሰለች አገር ( Wounded Nation) የተባለዉን መጽሃፋቸዉን፣ በርካታ ኢትዮጵያዉያን በተገኙበት ፣ ኒዉዮርክ በሚጘኝ የባርስን ኤንድ ኖብልስ መጽሃፍት ቤት አስመርቀዋል። በዚሁ ወቅትም፣ በኤርትራ ስላለዉ ሁኔታ ሰፊ ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን፣ በዚያ ከነበሩ ወገኖችም ለቀረበላቸው ጥያቄዎች ግልጽ ምላሾች ሰጥተዋል።

ዶር በረከት ፣ አስመራ የተወለዱ የሕግ ባለሞያ ሲሆኑ፣ በአጼ ኃይለስላሴ ዘመን፣ የሃር ከተማ ከንቲባ፣ የጠቅላይ አቃቢ ሕግ፣ የአገር ዉስጥ ምክትል ሚኒስቴር እንዲሁም የከፍተኛዉ ፍርድ ቤት ዳኛ ሆነዉ አገልግለዋል። ደርግ ሲመጣ፣ ለኤርትራ ነጻነት የሚደረገዉን ትግል በመደገፍ፣ በዉጭ አገር በተለያዩ መድረኮች የሻእቢያን አቋም ያንጸባርቁ የነበሩ ሰው ናቸዉ። በተለይም በአሜሪካዉ ድምጽ ራዲዮ ጣቢያ ቀርበዉ ከፕሮፌሰር መስፍን ወልደማሪያም ብዙ ጊዜ ያደርጉት የነበረዉን ክርክር በብዙዎች ዘንድ የሚረሳ አይደለም። ፕሮፌሰር መስፋ ሻእቢያ «ተገንጣዩ ቡድን» በሚሉበት ጊዜ ዶር በረከት «የነጻ አዉጭ ታጋዮች» እንዲባል ይከራከሩ ነበር።

ኤርትራ ነጻ ከወጣች በኋላ፣ ዶር በከረት የኤርትራን መንግስት ሕገ መግስትን አርቃቂ ኮሚሽን ዉስጥ በመሆን ያገለገሉ ሲሆን፣ በአሁኑ ሰዓት የኢሳያስ መንግስት በሕዝቡ ላይ የሚያደርጋቸዉ ፍጹም አሰቃቂ የአምባገነንነት ተግባራትን በመቃወም ኤርትራን ለቀዉ በስደት ይኖራሉ።

በአሁኑ ወቅት የኤርትራ መንግስት በተባበሩት መንግስታት እቀባ የተደረገበት፣ ፍጹም አምባገነን የሆነ የኤርትራዉያንን ደም እየጠጣ ያለ ፣ በሽብር ተግባር ላይ የሚሰማሩ እንደ አልሻባብ ያለን ቡድን የሚደግፍና የሚያስታጥቅ ጨካኝ መንግስት መሆኑን ፣ አለም አቀፍ ገለልተኛ ተቋማትና የሰባአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ይናገራሉ።

በባርንስ ኤንድ ኖብልስ ፣ ዶር በረከት በኤርትራ ያለዉ ሁኔታ እጅግ በጣም አሳዛኝ ( Big disappointment) ብለዉታል። በኤርትራ የታየዉ፣ ተስፋ ያደረጉት ሳይሆን ከጠበቁትና ከገመቱት በታች እንደሆነ የገለጹት ዶር በርከት፣ ኤርትራን failed state የሚል ስያሜ ሰጥተዋታል።

በግብጽና በቱኒሲያ የታየው በኤርትራ ስለሚከስትበት ሁኔታ የተጠየቁት ዶር በረከት « ወጣት እኮ በከተሞች ዉስጥ የለም። ወጣት ሁሉ ያለዉ በሳዋ ነዉ። በትልቁ እሥር ቤት። የብሄራዊ ዉትድርና ተብሎ ይሄዳሉ። ግን ስልጠናዉ ለዘለላም ነዉ» ሲሉ አስተያተታቸዉን ሰጥተዋል። ወጣት ሁሉ እስረኛ በሆነበት ሁኔታ፣ በግብጽና በቱኒዚያ የታየዉ ሁኔታ በኤርትራ ሊኖር እንደማይችልም በማከል ፣ ሁኔታው እጅግ በጣም አሳዛኝ እንደሆነ ዶር በረከት በቁጭት ለማሳየት ሞክረዋል።

በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል ስላለዉ ሁኔታ ዶር በረከት ሲጠየቁ ፣ ለኢትዮጵያና ለኤርትራ ብቻ ሳይሆን ለማናቸዉም አገራት ዲሞክራሲና ተጠያቂነት መኖር እንዳለበት አስረድተዉ፣ በእድሚያቸው ዘመን ኢትዮጵያና ኤርትራ ያላቸዉን ልዩነቶች አልፈዉ በመሄድ፣ አንድ የሚሆኑበትን ጊዜ ማየት እንደሚናፍቁና ተስፋ እንደሚያደርጉ በባርንስ ኤንድ ኖብልስ ለተሰበሰቡ ኤርትራውያንና ኢትዮጵያዉያን ሳይገልጹ አላለፉም። «የኢትዮጵያ አካል ነበርኩ፤ ዛሬም ለማሳየት እንደሞከርኩት፣ ነገሩን በስፋት ካየነዉ በባህል በታሪክ ኢትዮጵያዉያኖች ነን» ሲሉም ምንም እንኳ ኤርትራ የራሷ መንግስት ቢኖራትም፣ ከኢትዮጵያ ጋር ኤርትርዉያን ያላቸዉን ዝምድና ትስስር አብራርተዋል።ዝርዝር ቪድዮ ለማየት ከዚህ ይጫኑ !