የወያኔ ፍርድ ቤት በሰላም ታጋዮችና ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ላይ የተፈበረከውን የፈጠራ ወነጀል ክስ አስመልክቶ የቀረቡትን የሃሰት ምስክሮች ቃል ሰምቶ እንደጨረሰ ተገለጸ
በዘረኛው መለስ ዜናዊ ቃል የሚመዘወረው የወያኔ ፍርድ ቤት በነ አንዱአለም አራጌና ሌሎች 24 ሰዎች ላይ የተፈበረከውን የፈጠራ ክስ በማስረጃ ለማጠናከር በውሸት እንዲመሰክሩ ስልጠና ወስደው የቀረቡትን 30 ሰዎች ምስክርነት ቃል አድምጦ ሌላ ተጨማሪ የኦዲዮና የቪዲዮ ማስረጃ ለማየት ተለዋጭ ቀጠሮ እንደሰጠ የደረሰን ዜና ገለጸ።
ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ላይ ተጀምሮ ማክሰኞ ታህሳስ 10/2004ዓ/ም የተጠናቀቀውን ይህንን የምስክሮች ቃል መስማት የፍርድ ቤት ውሎ የተከታተሉ ምንጮች እንደገለጹት፤ የአሁኑን የወያኔ የፈጠራ ክስ ድህረ ምርጫ 97 ከታየው የሚለየው ምስክሮች የተባሉት ሁሉ በሰጡት ምስክርነት መጸጸታቸውንና አንድ ሃይል ከኋላቸው ሆኖ የሚያስፈራራቸው መሆኑን መደበቅ አለመቻላቸው በግልጽ ይታይባቸው እንደነበረ መስተዋሉ ነው ብለዋል።
ከመሃላ መፈጸም ሥነሥር ዓት እስከ መጨረሻው የምስክርነት ቃል አንገታቸውን ደፍተውና በሃዘን ስሜት ውስጥ ሆነው ምስክርነት ሰጥተዋል የተባሉት አብዛኛዎቹ ምስክሮች ከተከሳሾች ጠበቃ ለቀረበላቸው መስቀለኛ ጥያቄ ይሰጡ የነበረው ምላሽ ቀደም ሲል የሰጡትን ቃል የሚቃረንና ተከሳሾች ጥፋተኛ ናቸው የተባሉበትን ጭብጥ የማያስረዳ በዚህም ምክንያት ዳኞቹ ሳይቀር የተሸማቀቁበት እንደነበረ ተዘግቦአል።
ወያኔ በቅርቡ አክልዳማ በማለት ለህዝብ እይታ ባቀረበው ድራማ ላይ ጥፋተኛ በመባል በቁጥጥር ሥር ዉለዉ በራሳቸውና በሌሎች ተከሳሾች ላይ የጥፋተኝነት ምስክርነት ቃል ሲሰጡ የነበሩት ከእስር ተለቀው የአቃቤ ህግ ማስረጃ በመሆን ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ የተደረገ ሲሆን ተመልካችን ያስገረመው የምስክርነት ቃላቸውን ከጨረሱ ቦኋላ በፖሊስ መኪና ተጭነው ከግቢው መውጣታቸው ነው።
እስከዛሬ በፍርድ ቤቱ ከቀረበው ክስና ማስረጃ ለመረዳት እንደተቻለው ወያኔ በሽብርተኝነት ክስ የመሰረተባቸው ታጋዮች በሙሉ ባለፈው መስከረም በህጋዊ መንገድ ሰላማዊ ሰልፍ ለመጥራት ፈቃድ ተጠይቆበት በነበረው ሰላማዊ ሰልፍ ላይ በአንድ ወይም በሌላ መንገድ ተሳትፈዋል የሚል ብቻ እንደሆነ ለመረዳት ተችሎአል።
የፍርድ ውሎውን የተከታተሉ አንድ የውጪ አገር ዜጋ በሰላማዊ መንገድ የተቃውሞ ሰልፍ መጥራት በሽብርተኝነት የሚያስከስስ መሆኑን ማየታቸው ለርሳቸውና ለአገራቸው መንግሥት ስለመለስ ዜናዊ ምንነት ለማወቅ የመጨረሻው ማስረጃ እንደሆናቸው ለዘጋቢያችን በሰጡት አስተያየት ገልጸዋል።