የሠራዊቱን የብሔር ተዋጽኦ ለማመጣጠን የምልመላ መስፈርቶች ዝቅ እንዲል ተደርጎአል ሲል የወያኔው የመከላከያ ሚኒስቴር ገለጸ

በህወሃት የበላይነት በሚመራው የአገሪቱ መከላኪያ ሠራዊት ውስጥ ያለው የአዛዥነት ቦታ ሙሉ በሙሉ ለማለት በሚያስደፍር መልኩ ከትግራይ ብሄር በመጡ ጎጠኞች መያዙን የግንቦት 7 ንቅናቄ ካጋለጠ ወዲህ፤ የብሄረሰብ ተዋጾ ለማመጣጠን በሚል የተለያዩ የማስመሰያ ጥገናዊ ለውጦች ሲነገሩ የቆዩ ቢሆንም ሲራጅ ፋጌሳ በተባለው የይስሙላ መከላኪያ ምንስትር ባለፈው ማክሰኞ ለወያኔ ፓርላማ የቀረበው የዘር ተዋጽኦ ሪፖርት በርካታ የአገሪቱን ፖለቲከኞች ያሳቀ ሆኖ መገኘቱን ዘጋቢያችን ከአድስ አበባ በላከው ሪፖርት ገለጸ።

በደደቢት በረሃ ተደራጅተው ለስልጣን የበቁት የህወሃት መሪዎች አብሮአቸው የታገለውን የህወሃት ታጋይ በሙሉ ከፍተኛ የመደበኛ ትምህርትና ወታደራዊ ሳይንስ ሥልጠና በሚጠይቁ ወታደራዊ መኮንነት ቦታዎች ሁሉ ላይ ከመቶአለቅነት እስከ ጀነራልነት ማዕረጎች በመሾም ሌሎች የአገሪቱ ተወላጆች በገዛ አገራቸው ባይተዋርነት እስኪሰማቸው ድረስ በበታቸኝነት ስሜት እንዲሸማቀቁ እየተደረገ ለተራ ወታደርነት የሥራ መደብ ስለ ብሄረሰብ ተዋጾ ማውራት የሚጠቅመው ነገር እንደሌለ ብዙዎች ይስማማሉ።

ገና 11 ኛ ክፍል ተማሪ በነበረበት ወቅት በረሃ የገባውና ወያኔን ትግል የተቀላቀለው ሳሞራ ዩኑስ በብሄራዊ ሙዚዬም ውስጥ የመታሰቢያ ሃውልት የቆመለትና በአገሪቱ የመጀመሪያው ባለሙሉ ጄነራል ማዕረግ ተሿሚ እንደሆነ ሲታወቅ እርሱ በበላይነት በሚያሽከረክረ የመከላኪያ ምንስትር ውስጥ ለብሄረሰብ ተዋጾ አስረጅነት ሲባል ለይስሙላ ከኦሮሞ ብሄረሰብ በምንስትርነት ማዕረግ የተሾመው ሲራጅ ፈጌሳ ሳሞራ ዩኑስ በማያውቅ ምንም ነገር የመወሰን መብት እንደሌለው ውስጥ አዋቂ ምንጮች ይናገራሉ።

በመከላኪያ ሠራዊት ውስጥ ሊተገበር የታቀደውን የብሄረሰብ ተዋጽኦ አስመልክቶ ከትናትና ወዲያ ማክሰኞ በወያኔ ፓርላማ ፊት ቀርቦ ያስረዳው የይስሙላ ምንስትር ሲራጅ እንደተናገረው፤ በመከላኪያ ውስጥ ዝቅተኛ ተሳትፎ አላቸው በተባሉት ክልሎች በምልመላ ወቅት እስከ ዞን ድረስ በመውረድ ወጣቱ ስለተቋሙ ግዳጅ እንዲረዳና ስለአገር መከላከል ግንዛቤ እንዲኖረው ከማድረግ ባሻገር፣ በሌሎች ክልሎች የሚጠየቀው የአሥረኛ ክፍል ትምህረት ማጠናቀቅ መመዘኛ አይሆንም ከመባል አልፎ ለነዚህ ክልሎች ተመልማዮች አምስተኛ ክፍል መድረስ በቂ ነው ተብሎአል።

እንደዘጋቢያችን ሪፖርት በርካታ ታዛቢዎችን ያሳቀው የወያኔ ድራማ በመከላኪያ ውስጥ ወደ ወታደራዊ መኮንንነት ማዕረግ ለመግባት በሚደረገው የሳይኮሜትሪክ ምዘና መነሻ 65 ከመቶ ነጥብ የነበረው ወደ 45 ከመቶ ዝቅ እንዲል ተደርጎአል መባሉ ነው። ከ10ኛ ክፍል በላይ ትምህረት ደረጃ እንደሌለው በግልጽ የሚታወቅ ሰው የአገሪቱ የመጀመሪያው ሙሉ ጄነራል በሆነበትና ከታች ከመቶአለቅነት እስከ ጀነራልነት ያሉት ማዕረጎች ላይ የተኮለኮሉት ሁሉ በተመሳሳይ የትምህረት ደረጃ ላይ ያሉ የአንድ መንደር ተወላጆች በሆኑበት አገር ለአዳዲሶቹ የወደፊት ሰልጣኝ መኮንኖች መስፈርት መበጀቱና ፈተናውን የትኛው መኮንን ሊያዘጋጀው እንደሚችል አለመታወቁ ወያኔ እያወራው ያለው የጥገና ለውጥ አይናችሁን ሸፍኑና ላሞኛችሁ የሚለው የተለመደው ቅጥፈት አካል ነው።

ለወያኔ ተወካዮች ምክር ቤት በቀረበው የመከላኪያ ሪፖርት ሌላው አስቂኝ እነመለስ መተካካት በሚሉት አሰራር በ2003/04 በጀት ዓመት በሦስት ዙር ቁጥራቸው 561 የሚሆኑ ከፍተኛ አመራሮች በመተካካት ሒደቱ እንዲቀነሱ ታቅዶ፣ በሁለት ዙር 13 ጄኔራሎች፣ 303 ኮሎኔሎችና ሌተና ኮሎኔሎች በድምሩ 316 አመራሮች ተተክተዋል መባሉ ነው።

በወያኔ የመተካካት ፖሊሲ ተቀንሰዋል የተባሉት 13 ጄነራሎችና የተቀሩት ባለማዕረጎች አገዛዙ በጥብቅ ሊቆጣጠራቸው ወደሚፈልገው ሌሎች የሲቪል መስሪያቤቶች ተዛውረው በመከላኪያ ውስጥ ከነበራቸው ጥቅማጥቅሞች የበለጠ እንዲያጋብሱ እየተደረገ መሆኑን እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ እንደሚያውቅ የወያኔ ገዢዎች የሚገነዘቡት አይመስልም።

ይህ በዚህ እንዳለ በመከላኪያ ውስጥ ያለውን ዘረኛ አወቃቀር በመቃወም በርካታ ወታደሮችና የበታች መኮንኖች ከሥራገበታቸው እየኮበለሉ እንደሆነ የግንቦት 7 ንቅናቄ መረጃ ምንጮች ገልጹ። በመከላኪያ ሠራውቱ ውስጥ ያለው ዘረኝነት አሁንም አልቀነሰም የሚሉ ምንጮች እንደምናገሩት ለምሳሌ በሰሜን ዕዝ ስር ካሉት 9 ክፍለጦሮች ውስጥ በሻምበል መሃመድ ከሚመራው 24ኛ ክፍለጦርና በአዛዥ ከፍያለው ከሚመራው 25ኛ ክፍለጦር በስተቀር የ7ቱም ክፈለ ጦር አዛዦች ትግሪኛ ተናጋሪዎች ናቸው። ትግሪኛ ተናጋሪ ያልሆኑት አዛዦች ይመሩታል የተባሉት የ24ኛና 25ኛ ክፍለጦርም ቢሆኑ የዘመቻ መኮንኑና የሎጀስቲክ ሃላፊነት ቦታዎች ላይ ያሉት እነርሱ ናቸው።

በዚህም የተነሳ እያንዳንዱ የጦር አባል ደስተኛ አይደለም የሚሉ ምንጮች ጦሩ ውስጥ ያለው ክፍፍልና በሥር ዓቱ ላይ ያለው ጥላቻ በሲቪሉ ህበረተሰብ ውስጥ ካለው የከፋ ነው ። የጦሩ አባላት በአገዛዙ ላይ ያላቸው ጥላቻ እንዲጨምር እያደረገ ያለው የሰራዊቱ አባላትን በፍርሃት ለማሽመድመድ ተብሎ በጊዜው በሚደረገው ግምገማ ላይ ሰዎች ለቀልድና ለጫወታ የተናገሩት ሳይቀር ወደፖለቲካ እየተመነዘረ የሚቀርበው ሂስ እንደሆነ የደረሰን መረጃ አመልክቶአል። እርስ በርስ መተማመን እንዳይቻል በተደርገበት የወያኔ ሠራዊት ውስጥ ማንም አባል እከሌ ይቀርበኛል ብሎ የሆዱን አውጥቶ ለማንም አንደማያጫውትና ይህ እራሱን የቻለ ማህበራዊ ቀውስ ስለፈጠረ ብዙዎች የአገልግሎት ጊዜያቸውን ጨረሰው የሚሰናበቱበትን ቀን በጉጉት የሚጠብቁ ናቸው።

በሰራዊቱ አለመረጋጋትና ደስተኛ አለመሆን የተደናገጡ የወያኔ ሹሞች ካለፈው ነሃሰ ጀምሮ ልዩ የደመወዝ ጭማሪ ያደረጉ ቢሆንም ያመጣው መሰረታዊ ለውጥ እንደሌለ ይነገራል። በአዲሱ የደመወዝ ጭማሪ የአንድ ተራ ወታደር ደመወዝ በወር 800 ስምንት መቶ ብር ሲሆን የአንድ መቶ አለቃ ደመወዝ በወር 1860 አንድ ሺ ስምንት መቶ ስልሳ ብር ደርሶአል። ከመቶአለቅነት ማዕረግ በላይ ያሉት አብዛኞቹ የህወሃት አባላት በመሆናቸው እነርሱን ለመጥቀም ሲባል የወንበር አበል በሚል ሰበብ በወር 200 ብር ሲከፈል እንደነበረ የገለጹት ምንጮች የመቀመጫ አበል ተብሎ የሚከፈለው ገንዘብ በወታደሩ መካከል ባስከተለው ተቃውሞ ምክንያት እንደተቋረጠ ገልጸዋል።

በወያኔ ጦር ውስጥ ያለው የዘር ስብጥር ተቃውሞ ያስነሳው ከ95 በመቶ በላይ የአዛዥነት ቦታ ላይ ተመድበው የሚገኙት ከአንድ ብሄረሰብ ማለትም ከትግራይ መሆኑ ሆኖ እያለ ወያኔ የዘረን ተዋጾ ለማድረግ ዕቅድ እንዳለው እየነገረን ያለው በተራ ወታደርነት ያለውን ዘርፍ ነው። እንደ አብዛኛው ኢትዮጵያዊ እምነት በተራ ወታደርነት ደረጃ ያለው የብሄረሰብ አስተዋጾ በመስፈርትነት መቀመጡ ምንም ትርጉም የለውም። መጻፍና ማንበብን ለመጀመሪያ ጊዜ አዲስ አበባ ከገቡ ቦኋላ የተማሩት የህወሃት የቀድሞ ታጋዮች ከሻለቃ ማዕረግ እስከ ጀነራልነት ተሹመው ባለበት ሁኔታ ለተራ ወታደር ምልመላ የ10 ኛ ክፍል ትምህረት ወይም ከዚያ በታች ያለው በመስፈርትነት መቀመጡ ወያኔ እየተከሰሰበት ያለውን ዘረኝነት ሊያሻሽል አይችልም በብዙዎች እምነት።