ህወሃትን መደገፍ በምንም መንገድ አማራጭ አይሆንም!!!
አንዳንድ ሰዎች ህወሃትን የምንደግፈው አማራጭ ስላጣን ነው ሲሉ ይደመጣሉ። እንዲህ ዓይነት አስተሳሰብ የሚመጣው ነገሮችን ከሥር መሰረቱ ለማየት አቅም ከማጣት ብቻ ሳይሆን የራስን ችሎታና እውቀት ፈልጎ ካለማግኝትም ጭምር የሚፈጠር እምነት ነው።
ህዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ የተባለው ዘረኛና ዘራፊ ድርጅት ኢትዮጵያዊያንን አማራጭ አሳጥቶና አጎሳቁሎ እርሱ ብቻ ደልቶት እየኖረ ነው።በእነዚህ ዘረኞችና ዘራፊዎች እጅ ያለች ኢትዮጵያ ፍትህ አጥታ፤ ህግ ዜጎችን ለማጥቂያ ጥሩ መሳሪያ ሆኖ፤ ጥቂቱ ብዙሃኑን ተጭኖ ብዙሃኑም ጥቂቶቹን ተሸክሞ ስቃይና መከራው በዝቶ እየኖረ ባለበት በዚህ ዘመን አማራጭ ስላጣው ዘረኝነትንና ዝርፊያን እደግፋለው ማለት አሳፋሪ ነው።
በመለስ ዜናዊና ቡድኑ እምነት መሰረት “ዜጎች ሁሉ እኩል ናቸው ነገር ግን ጥቂት ዜጎች ይበልጥ እኩል ናቸው” የሚል እንስሳዊ መርህ ይዘው ዜጎችን በመከፋፈል ተግባር ላይ ተጠምደው ብዙ ዓመታትን አስቆጥረዋል። አንዱን የህዝብ ክፍል አንተ እኮ “ወርቅ” ነህ ሲሉት ሌላውን ደግሞ “አህያ” እያሉ መሳደባቸው የሚታወቁበት መልካቸው ነው።አንዱን የህዝብ ክፍል አንስተው የሌላው ጠላት አድርገው ሲሰብኩ ትንሽም የሂሊና ወቀሳ የማይሰማቸው መሆኑን ማየት የሚችል አይቷል መስማት የሚችልም ሰምቷል። “የትግራይ ህዝብ ቀንደኛ ጠላት አማራ ነው” ብሎ ጽፎና መመሪያ አድርጎ የሚሰራ የክፉዎች ቡድን መሆኑንም ዘወትር ማስታወስ የሚገባን መሰረታዊ ነገር ነው። አንዱ የህዝብ ክፍል በሌላው እንዲጠላና እንዲራራቅ ለማድረግ የህዝቡን ግማሽ ጎን በቦንብ ለማስደብደብ፤ ገድሎ ገደል እንዲጨመሩ ለማድረግ ወደ ኋላ አለማለታቸውን አይተናል ሰምተናልም። እንዲህ ዓይነቱን ነፍሰ ገዳይ ቡድን አማራጭ ስላጣው እደግፋለው ማለት ፈጽሞ አሳፋሪ ነው።
መለስ ዜናዊ በዙሪያው ብዙ ሆድ አደሮችን ሰብስቧል። እነዚህ ሆዳቸው እስከሞላ ድረስ አገሪቷ ከገጸ ምድር ብትጠፋ ግድየላቸውም። ህዝብ ርስ በርሱ ቢተላለቅ እነርሱን የሚያስደነግጣቸው አይደለም። እንዲያውም እንዲያ ያለ ነገር እንዲፈጠር በዘረኝነት ልክፍት የተያዘው መለስ ዜናዊ የሚያዛቸውን ለመፈጸም የሚሸቀዳደሙ ናቸው። አእምሮአቸው ከሆዳቸው ዘሎ ማሰብ ባለመቻሉም አገሪቷ ለምና ያገኝችውን ገንዘብ እየዘረፉ በውጭ አገራት ባንክ ውስጥ ይደብቃሉ። ልጆቻቸውንና ዘመዶቻቸውንም አንደላቀው በውጭ አገራት ያስተምራሉ ያኖራሉ። የቀደሙ ዜጎች ያኖሩትን ድንበር እያፋረሱ የአባቶቻችን የደም መሬት የሆነውን ለባእዳን ይሰጣሉ። ይሸጣሉ። እንዲህ የሚያደርገውን ቡድን አማራጭ ስላጣሁ እደግፋለው ማለት ካሳፋሪነትም በላይ ነው።
የአገሪቷን ፍትህ ሥርዓት አዋርደው የግል መጠቀሚያቸው አድርገውታል። ዛሬ በአገራችን የህግ የበላይነት በመለስ ዜናዊ ስሜት ተተክቷል።የዚህ ሰው ስሜት ህግ በሆነበት አገር “እኔ ሰው ነኝ” ማለት አሸባሪነት ሆኗል። ”የመናገር ነጻነት ይከበር” ማለት በአገር ክዳት ወንጀል የሚያስከሥሥ ሁኗል። ”የሰብዓዊ መብት ይከበር” ማለት በስቅላት የሚያስቀጣ ወንጀል ሁኗል። ሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግ ማሰብና መጠየቅ መንግስትን በአመጽ ለመገልበጥ የሚደረግ ተግባር ነው ተብሏል። ኢትዮጵያ ውስጥ በሰላም ገብቶ ለመውጣት ስለመለስ ዜናዊ ቅንድብ ማማር መዝፈን እና የወያኔን ልማታዊ መንግሥትነት ማወደስ አስፈላጊ የሆነበት ደረጃ ላይ ተደርሷል። እንዲህ የፍትሁን ስርዓት አዋርደው የግል መጠቀሚያ ያደረጉ ኃይሎችን አማራጭ ስላጣሁ እደግፋለሁ ማለት ነውር ነው።
በአገራችን ውስጥ በተጨባጭ የሚታየው ጥቂት የትግራይ ገዥ ጉጅሌዎች ብዙሃኑን ተጭነው ብዙሃኑ ኢትዮጵያዊም እነርሱን ተሸክሞ ስቃይና መከራው በዝቶ መኖሩ ነው። እነዚህ ጥቂቶች ለንጽፅር ተብሎ በአንድ ወቅት አደባባይ በወጣው መረጃ በአንድ መንግስታዊ ተቋም ማለትም በአገሪቷ መከላኪያ ውስጥ ካሉ ስልሳ አንድ የጦር ጄኔራሎች ሃምሳ ሰባቱን የሚቆጣጠሩ ሆኖ የመገኘቱ ምስጢር ብዙሃኑን ረግጠው ለመኖር ካላቸው ቅዥት የተነሳ ነው። በዚህ ብቻ አያበቃም የአገሪቷ የድህንነት መስሪያ ቤት ሙሉ በሙሉ በአንድ አካባቢ ልጆች ቁጥጥር ስር መውደቁ ዜጎችን ለመጫንና ለማሰቃየት የተመቸ መንገድ ፈጥሮላቸዋል። በእነዚህ ጦር አዛዦችና የድህነቱ መሥሪያ ቤት ሹመኞች አማካኝነ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች ለስደት ተዳርገዋል። በየቦታው ተገለው የተጣሉትን ቤቱ ይቁጠራቸው። የተለያየ የፈጠራ ወንጀል ታፔላ ተለጥፎባቸውና የሃሰት ምስክር ተዘጋጅቶ ወህኒ የተወረወሩ ዜጎችን ቆጥረን አንዘልቀውም። መለስ ዜንዊ በድሆች ስም ለምኖ ያመጣውን ገንዘብ የገዛ አገሩን ዜጋ ለማስለል በአገር ውስጥና በውጭ አገራት ውስጥ ላሰማራቸው ሰላዮች ሲያውል ቅንጣት ታክል ቅሬታ አይሰማውም። ለመለስ ዜናዊ ከስልጣኑ የሚበልጥበት ምንም ነገር የለም። የህዝቡ መራብና መቸገር ለእርሱ ተረት ተረት ነው። እንዲህ ዓይነቱን የሚያይ ዓይን የሚሰማ ጆሮም የለውም። ”Animal farm” በተባለ መጽሃፍ ውስጥ ከዋነኞቹ ተዋኒያን መካከል መለስ ዜናዊ ናፖሊዮን የተባለውን ገጸ ባህሪይ የመስላል። እንዲህ ዓይነቱን እኩይ ግለሰብ አማራጭ ስላጣሁ እደግፋለው ማለት “ሁለት እግሮች መጥፎ አራት እግሮች ሁሉ ጥሩ”እያሉ ከሚያላዝኑ በጎች ጋር መሳ ለመሳ የሚያቆም አባባል ነው።
በመጨረሻም የሰው ልጆች ምርጫ አጥተው አያውቁም። ምርጭ ሞልቷል።ምርጫ ያሳጣንን ሃይል ምርጫ ስለጠፋ ከመደገፍ ይልቅ ይህንኑ ቡድን ወይም ሃይል ለማስወገድ መታገል የተሻለ ምርጫ ነው። እነ መለስ ዜናዊ ካሁን በኋላ ተመክረው የሚመለሱ አይደሉም። የአንድ ትውልድ እድሜ ያክል የኖሩበትን ልማድ ሲፈጽሙ የኖሩትን ዝርፊያ፤ ውሸት፤ ጭካኔ፤ ግድያ እና የሰው ልጆችን ማሰቃየት ይተዋሉ ማለት አይቻልም። መለስ ዜናዊንና ቡድኑን መደገፍ ለራሱ ክብር ከሚሰጥ ዜጋ የሚጠበቅ ተግባር አይደለም።ለራሱ ስብእና ክብር የሚሰጥ ዜጋ ምርጫ ያሳጡ ሃይሎችን በሚችለው ሁሉ ይታገላል እንጂ ምርጫ ስላጣሁ እደግፋቸዋለሁ አይልም።
የተከበራችሁ ወገኖቻችን መለስ ዜናዊንና ቡድኑን መደገፍ በምንም መልኩ ምርጫ አይሆንም። በዚህ ወቅት ዘረኝነትንና ዝርፊያን በቃ ማለት በእጅጉ የተሻለ ምርጫ ነው። ከልዩነቶቻችን ይልቅ አንድነቶቻችን ላይ እናተኩር። ተስፋ ከመቁረጥ ይልቅ ከነመለስ ዜናዊ ዘረኛና ዘራፊ ቡድን በኋላ ስለምትመሰረተው ኢትዮጵያ አጥብቀን እናስብ። ከደመናው ባሻገር የነጻነት ጎህ ሲቀድ ለማየት የአእምሯችንን ልቀት አንወስን። እነመለስ ዜናዊ “እኛ ከሄድን ኢትዮጵያ ትበታተናለች” የሚሉትን ሟርት “እኔ እያለሁ አገሬ አትበተንም” በሚል ከራስ መተማመን በሚመነጭ ውሳኔ እንንገራቸው። ኢትዮጵያ አገራችን ለሉአላዊነቷና ለዘላቂ ጥቅሟ ከመለስና ግብረአበሮቹ በላይ ጠላት እንደሌላት እናሳውቃቸው። የእነመለስ ጥረት እራሳቸው በፈጠሩት የእርስ በርስ ጦርነት ስጋት ውስጥ ወድቀን የነርሱን ሰላም አስከባሪነት በመሻት እስከወዲያኛው እንድንገዛላቸው ነውና ይህንን ምኞታቸውን እንደ ጠዋት ጤዛ ማርገፍ፤ እንደ ጉም ብን ብሎ እንዲበን ማድረግ ለፍትህ፤ ለእኩልነትና ለዲሞክራሲ የምንታገል ሃይሎች ሁሉ ሃላፊነት ነው።
ኢትዮጵያችን ለዘላለም ትኑር !!!!
ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ!!!