ዶር ብርሃኑ ነጋ በኢሳት ላደረጉት ቃለ ምልልስ መልስ- ግርማ ካሳ
ዲሴምበር 20 2011
«እነ መለስ ናቸዉ ሕግ። መለስ የፈለገዉን ነገር ሕገ ወጥ ነዉ ካለ ሕገ ወጥ ነዉ። ይህን አዉቀህ ምኑን ነዉ ታገል የምትለዉ? ምኑን ነዉ በሰላማዊ መንገድ ለዉጥ አመጣለሁ የምትለዉ ? እርሱ እኔ በፍጹም ትርጉም ያለዉ እዉነተኛ ለዉጥ ለማምጣት የሚደረግ እንቅስቃሴ ነዉ ብዬ አላምንም ….. ጊዜ ማጥፋትና እራስን መሸንገል ካልሆነ በቀር»
« ..ግን መገፋት ይችላሉ። በርግጥ ምርጫ ሊያጡ ይችላሉ። ምርጫ ለማሳጣት የግድ ጠመንጃ መሆን የለበትም። በተለያዩ መንገድ.፣በተለያዩ እንቅስቃሴዎች ፣ በመካከለኛዉ ምስራቅ እንዲሁም በሰሜን አፍሪካ እንዳየነዉ፣ ሕብረተሰቡ በፍጹም አልገዛም ብሎ መሳሪያ ሳይዝ ሊያስገድዳቸው ይችላል። በዚያ መልክ መኬድ አለበት ብዬ አምናለሁ። ግን መገደድ አለባቸዉ። በስልጣን ላይ ሊቆዩ እንዳማይችሉ ማወቅ አለባቸዉ። ያ ሲሆን ብቻ ነዉ ለዉጥ የሚመጣዉ»
ዶር ብርሃኑ ነጋ ከኢሳት ጋር ካደረጉት ቅለ ምልስ የተወሰደ
ከላይ የጠቀስኳቸዉ፣ እርስ በርሳቸዉ የሚቃረኑ ሁለት አባባሎች፣ ዶር ብርሃኑ ነጋ የግንቦት ሰባት ንቅናቄ መስራችና ሊቀመንበር፣ በቅርቡ ከጋዜጠኛ ሲሳይ አጌና ጋር በኢሳት የዳይስፖራ ቴሌቭዥን ካደረጉት ቃለ ምልልስ የተወሰዱ ናቸዉ። ሰላማዊ ትግል ጊዜ ማጥፋትና እራስን መሸንገል ነዉ ባሉበት በዚያዉ አንደበታቸዉ፣ ያለ ጠመንጃ ለዉጥ ማምጣት ይቻላል ይሉናል ዶር ብርሃኑ።
በተለይም የአንድ የፖለቲካ ደርጅት መሪ ሆነን፣ በቴሌቭዥን ቀርበን ትንታኔዎች በምናቀርብበት ጊዜ ምን እንደምንናገር፣ የምንናገረዉ ነገር ምን ሊያስከትል እንደሚችል ብናገናዝብ ጥሩ ይሆን ነበር ብዬ አስባለሁ።
በመጀመሪያ ደረጃ ዶር ብርሃኑ ነጋ የሰላማዊ ትግልን፣ ሕውሀት/ኢሕአዴግ ሲፈቅድ ብቻ ከሚደረግ እንቅስቃሴ ጋር ያምታቱት ይመስለኛል። ማህተመ ጋንዲ፣ ሕዝቡን ለነጻነቱ በሚያንቀሳቀሱበት ጊዜ፣ የቅኝ ገዢ እንግሊዞችን ሕግና ትእዛዝ እየጠበቁ አልነበረም። ሰላማዊ የሆነ የእምቢተኝነት ዘመቻዎች ነበር ያደርጉ የነበረዉ። ሮዛ ፓርክ ለነጮች ብቻ በተፈቀደ የአዉቶቢስ መቀመጫ ላይ ሲቀመጡ፣ የባለስልጣናትን ዘረኛ መመሪያና ሕግጋት ሲጥሱ ፣ ሰላማዊ ትግል ነዉ ያደረጉት። በግብጽና በቱኒዚያ የመንግስቶቻቸዉን አዋጆች ወደ ጎን አድርገዉ ዜጎች ሰልፎች ሲወጡ፣ ሰላማዊ ትግል ነዉ ያደረጉት።ሰላማዊ ትግል በአጭሩ ፣ ተኩሶ ሰዉ መግደልን ያላካተተ ፣ ለዉጥ ለማምጣት የሚደረግ ማናቸዉም አይነት እንቅስቃሴዎችን ያጠቃልላል። ስለዚህ ዶር ብርሃኑ «በሰላማዊ መንገድ ለዉጥ ማምጣት አይቻልም» የሚሉትን አባባል «አገዛዙ የሚፈቅደዉን እንቅስቃሴ ብቻ በማድረግ ለዉጥ ማምጣት አይቻልም» በሚለዉ አባባል ቢያስተካክሉት ጥሩ ሊሆን ይችል ነበር። እንጂ እንዲሁ በደፈናዉ የተሳሳቱና እርስ በርሳቸዉ የሚቃረኑ አስተያየቶችን በመስጠት፣ ሊታገል የተዘጋጀዉን ሕዝብ ግራ ማጋባት መልካም ነዉ አልልም።
ያ ብቻ አይደለም።« እኛ አልተሳካልንም፣ እኛ እነዚህና እነዚያን ስህተቶች አድርገን ነበር። ከኛ ተመክሮ ትምህርት ወስድችሁ፣ ከኛ ስህተት ተምራችሁ፣ ትግሉ ወደፊት ግፉት» መባል ሲገባ፣ «እኛ ሞክረን ሳይሳካለን ስለቀረ ፣ እኛ ታግለን ዉጤት ማምጣት ስላልቻልን ፣ ሌሎች የሚያደርጉት ጥረት አይሳካም» ብሎ መደምደም ፣ የሌሎችን ጥረት አሳንሶ ማቅረብ፣ የሽንፈተኝነት መልእክት ማስተላለፍ፣ ሰዉን ተስፋ ማስቆረጥ፣ የሚያፈርስ እንጂ የሚገነባና የሚያንጽ አይደለም።
ዉይይቴን ትንሽ ለጠጥ ላድርገዉና ዶር ብርሃኑ ስለ ግብጽና ቱኒዚያ ሲናገሩ ወዳቀረቡት፣ «ሰላማዊ ትግል አይሰራም» ከሚለዉ አባባላቸዉ ጋር በግልጽ ወደሚቃረን ትልቅ ቁም ነገር ልመለስ። የኢትዮጵያ ሕዝብ መሳሪያ ሳይዝ፣ ገዢዉን ፓርቲ አስገድዶ ለዉጥ ሊያመጣ እንደሚችል ነዉ በግልጽ ለማስረዳት የሞከሩት። በጣም ትክክለኛና በሙሉ ልቤ የምደግፈዉ አባባል ነዉ። በርግጥ የኢትዮጵያ ህዝብ ቀና ካለ፣ በምንም ሚዛንና መስፈርት አቶ መለስ የግፍ ቀንበር በእርሱ ላይ ጭነዉ ሊቀጥሉ አይችሉም።
እንግዲህ ትልቁ ጥያቄ ህዝቡ እንዴትና መቼ ነዉ የሚነሳዉ የሚለዉ ነዉ ? ዶር ብርሃኑ ለዚህ መልስ የላቸዉም። ከአንድ ሰዓት በላይ የፖለቲካ ትንታኔ ሲሰጡን አንገብጋቢና ወሳኝ እንዲሁም ተግባራዊ ለሆኑ ጥያቄዎች ብዙም የሚሉት አልነበራቸዉም። ይህም ምን ያህል የሚያራምዱት ፖለቲካ የከሰረ ፣ ከላይ ያማረ በዉስጥ ግን ፍሬያማና አቅጥጭ ጠቋሚ የሆነ ፖለቲካ እንዳልሆነ የሚያሳይ ነው።
በግብጽና በቱኒዚያ እንዲሁም ሰሞኑን በራሺያ እንቅስቃሴዎች የታዩት፣ በትዊተርና በፌስቡክ ነዉ። በግብጽ 46%፣ በቱኒዚያ 96% የሚሆነዉ ሕዝብ የኢንተርኔት አገልግሎት አለዉ። በግብጽና በቱኒዚያ እንደ አልጃዚራ የመሳሰሉ ከስምንት የሚበልጡ፣ አብዛኛዉ የአረብ ሕዝብ የሚከታተላቸዉ የቴለቭዥን ሳተላይቶች አሉ። በቀላሉ በኢንተርኔትን በቴለቭዥን በአጭር ጊዜ ዉስጥ ህዝብን ማንቀሳቀስና ማደራጀት ተችሏል።
በአገራችን ኢትዮጵያ የኢንተርኔት አገልግሎት ተጠቃሚ ከ 0.5 በመቶ በታች ነዉ። የሳተላይት ዲሽ ያለዉ ከአንድ በመቶ ያነሰ ነዉ። በግብጽና በቱኒዚያ የተደረገዉን አይነት አደረጃጀትና ቅስቀሳ ማድረግ አስቸጋሪ ነዉ። ታዲያ ዶር ብርሃኑ ነጋና ድርጅታቸዉ ግንቦት ሰባት፣ እንዴት አድርገዉ ነዉ፣ አሜሪካን አገር ተቀምጠዉ፣ ሕዝቡን ሊያደራጁ የሚችሉት? እንዴት አድርገዉ ነዉ ሕዝቡ እንዲነሳ የሚቀሰቅሱት ? ለዚህ ዶር ብርሃኑ ነጋ መልስ ያላቸው አይመስለኝም።
ምንም አይነት የተሻለ አማራጭ ሳያቀርቡ ፣ አገር ቤት ሰላማዊ ትግል እያደረጉ ያሉ፣ በሰላማዊ ትግል ምክንያት የታሰሩ፣ የተንገላቱ፣ ከሥራ የተባረሩ፣ ትልቅ መከራ የሚደርስባቸዉ ወገኖቻችን አኩሪ እንቅስቃሴን «ጊዜ ማጥፋትና እራስን ማታለል ነዉ » ማለታቸው የሚያስተዛዝብና የሚያሳዝንም ነዉ። ከአንድ የተማረ የፖለቲካ መሪ የምንጠብቀዉ አስተያየት አይደለም።
በአገር ቤት በቅርቡ በታላቁ ሩጫ እንዳየነዉ፣ ሕዝቡ ያለዉን ተቃዉሞ እያሰማ ነዉ። «ሳንፈልጋቸዉ ፤ ሃያ አመታቸዉ ! » እያለ ነዉ። በአገር ቤት የአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ በየሳምንቱ የፍኖት ጋዜጣን እያተመ ህዝቡ እንዲያነብ እያደረገ ነዉ። የፍኖት ጋዜጣ እንዴት ጠንካራና፣ ቀስቃሽ ጽሁፎችን ለአንባቢያን እንደሚያቀርብ አቡጊዳና ኢኤምኤፍ ላይ ሄዳችሁ ማንበብ ትችላላችሁ።
የፍትህ ጋዜጣ፣ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ደግሞ አዉራምባ ታይምስ ጋዜጣ፣ ሳይፈሩ፣ በሚያኮራ መልኩ፣ በድፍረት የገዢዉን ፓርቲ አምባገነንነት አጋልጠዋል። በዚህም ምክንያት የአዉራምባ ታይምስ ጋዜጠኛ ዉብሸት ታዬ ፣ የፍትህ ጋዜጣ ጸሃፊ ርዮት አለሙ ታስረዋል። በየአብያተ ክርስቲያናቱና ጸሎት ቤቶች ለሰላም ለፍቅር ለአንድነት ይጸለያል። ገዢዉ ፓርቲ አፋኝ ፖሊሶውቹን እንዲለወጥ ፣ ለብሄራዊ እርቅ እንዲዘጋጅ ከዉስጥም ከዉጭ የተለያዩ ተማጽኖዎችና ይቀርቡለታል፤ ግፊቶች ይደረጉበታል። እነዚህም ሁሉ በአገር ቤት እየተደረጉ ያሉ ወሳኝ የሰላማዊ ትግል አካላቶች ናቸዉ።
ሽብሬ ደሳለኝን፣ አረጋዊ ገብረ ዪሐንስን፣ ቢያንሳ ዳባን እንዲሁም ሕይወታቸዉን ያጡ በርካታ ወገኖቻችንን እናስታወስ። ከስድስት ወራት በላይ በጨለማ ቤት ተቀምጣ የስነ ልቦና ቶርቸር የደረሰባትን ብርቱካን ሚደቅሳን፣ እንዲሁም በአሁኑ ወቅት በማእከላዊና በአራቱ ማእዛናት ባሉ የአገራችን እሥር ቤቶች የሚማቅቁትን እናስታዉስ። በዚህ በሰላማዊ ትግል ዉስጥ ብዙዎች እጅግ ትልቅ ዋጋ እየከፈሉ ነዉ። እንዲሁ በቀላሉ እንደ እቃ እቃ ጨዋታ ጥለን የምንሄደው ነገር አይደለም። ፈረንጆች እንደሚሉት «We are in it to the finish» ።
በቅንጅት ጊዜ የነበረዉ እንቅስቃሴ፣ አራቱ የቅንጅት አባል ድርጅቶች ገና በቅጡ ከላይ እስከ ታች ሳይቀናጁ፣ የአመራር አባላቱ ሳይተማመኑና አንድ ሳይሆኑ ፣ በቂ የሆነ ድርጅታዊ መዋቅርና ዝግጅት ሳይኖራቸው የተከሰተ እንቅስቃሴ ነበር። መሪዎች ሲታሰሩ፣ ከታች ያለዉ በተዋቀረ መልኩ ትግሉን ሊመራ አልቻለም። በበቂ ሁኔታ ድርጅታዊ ሥራ አልተሰራምና።
ይህ በአሁኑ ወቅት በአገራችን ያለዉ የሰላማዊ ትግል አሁን ካለበት ደረጃ አልፎ ወደፊት ይገሰግስ ዘንድና በአገር ቤት ያሉ የሰላማዊ የፖለቲካ ድርጅቶች የጠነከረ አመራር መስጠት ይችሉ ዘንድ አቅማቸዉን የበለጠ ማጎልበት ይኖርባቸዋል። የጠነከረ እርምጃ ለመዉሰድ፣ ገዢው ፓርቲ የሚደነግጋቸዉን የአለም አቀፍንም ሆነ የኢትዮጵያን ሕገ መንግስት ለሚሽሩ፣ አፋኝ ዉሳኔች «እምቢ» ብሎ ሕዝቡ እንዲነሳ ለመቀስቀስና ለማታገል ጠንካራ መሆን ያስፈልጋል። ዝግጅት ያስፈልጋል። ድርጅታዊ ሥራ አስቀድሞ መስራት ያስፈልጋል።
እንግዲህ ጥያቄዉ እነዚህ አገር ቤት ያሉ ድርጅቶች፣ ሕዝቡን በስፋት ማንቀሳቀስ ይችሉ ዘንድ እነርሱን መደገፉና ማገዙ ይረዳል ? ወይንስ እንደ ዶር ብርሃኑ «ዋጋ የለዉም» ብለን ተስፋ በመቁረጥ አሜሪካንና አዉሮፓ ተክለን፣ ከሻእቢያ እግር ስር ተቀምጠን የሌሎች አገራትን ገድል ማውራት ?
ነገሮችን ከስሜት በፀዳ መልኩ ከሁሉም አቅጣጫዎች ማየት ያለብን ይመስለኛል። እኛ ምንም ሳናደርግ፣ የሌሎችን ትግል ከወዲሁ ማንቋሽሽ እጅግ በጣም ነዉር ከመሆኑ የተነሳ አገርንና ሕዝብን የሚጎዳ ነዉ ብዬ አምናለሁ።
አንዳንዶች «አንተስ ግንቦት ሰባትን ታንቋሽሽ የለም ወይ ?» ሊሉ ይችላሉ። ግንቦት ሰባት ትግሉን ለመርዳት የሚያደርጋቸዉን እንቅስቃሴዎች አንቋሽሼ አላውቅም። ለምን ቢባል ምንም አይነት እንቅስቃሴ አለ ብዬ ስለማላምን።
«የሰላም ትግል አይሰራም» ያሉን ዶር ብርሃኑ ነጋ፣ ቁምጣ ታጥቀዉ፣ በባሌ ጫካዎችና በጎንደር ተራራዎች የተነሱትን ፎቶግራፍ ቢያሳዩኝ፣ ከዚያ ሆነዉ በሳተላይት ስልክ፣ ቃለ መጠይቅ አድርገዉ የድጋፍ ጥሪ ቢያሰሙ፣ ነቀፌታ ሳይሆን አክብሮት ይኖረኝ ነበር።
ዜጎች መሯቸዉ ለመብታቸዉ ነፍጥ ቢያነሱ «ለምን?» ብሎ ለመጠየቅ እኔም ሆነ ማንም የሞራል ብቃት ሊኖረው አይችልም። ሴት ልጆቼ ወይንም ባሌበቴ ሲደፈሩ፣ ቤቴ ሲቃጠል፣ ማንም ወሮበላ እንደፈለገ ሲያስረኝ ሲፈታኝ ፣ በቃኝ ብዬ፣ እራሴንና ቤተሰቤን ለመከላከል ነፍጥ ባነሳ «በርታ» እንጂ ለምን ልባል አይገባም። ብረት አንስተዉ የግፍ አገዛዝን በቃ የሚሉ ወገኖቻች ላይ በጭራሽ አንዳችም አይነት ጥያቄም ሆነ ቅሬታ የለኝም። ሊኖረኝም አይችልም። ከመረጡ፣ የግፍ አገዛዝን በነፍጥ የመታገል የእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ሙሉ መብት ነዉ። እራሳቸዉ ሕወሃት/ኢሕዴጎች ያደረጉት ይሄንኑ አይደለም እንዴ ? እነርሱ ሲያደርጉት ጀግንነት ፣ ሌላዉ ሲያደርገዉ ሽብርተኝነት የሚሆንበት ምንም ምክንያት የለም።
እኔ ያለኝ ትልቁ ችግር፣ ነፍጥ ያነሱ ላይ ሳይሆን፣ ነፍጥ ሳያነሱ ስለነፍጥ ጠዋትና ማታ እያወሩ የሚያሰለቹን ላይ ነዉ።
የግንቦት ሰባት ንቅናቄ ከተቋቋመ ሶስት አመታት ሆኖታል። ለገዢዉ ፓርቲ ዜጎችን ለማሰሪያ ምክንያትና ሰበብ ከመሆን ዉጭ ፣ ግንቦት ሰባት አደረገ የምለዉ ነገር የለም። አራምደዋለሁ በሚለዉ ሁለገብ ትግል የተቆጣጠረዉ አንዲት ቀበሌ፣ የገደለዉ አንድ የሕወሃት/ኢሕአዴግ ባለስልጣን የለም ። በግንቦት ሰባት ተደረገ የሚባል ፣ የተጨበጠ፣ ጥቅም ያመጣ ቅንጣት የምትሆን ክንዋኔ የለችም። እንዴት ተደርጎ ነዉ ታዲያ የሌለን እንቅስቃሴ ልንቃወምና ልንተች የምንችለዉ ?
በዉጭ አገር ተቀምጠን፣ ሃምበርገራችንን እየገመጥን፣ በየዩኒቨርሲቲዉ እያስተማርን፣ በየአዉሮፓና አሜሪካ በሚደረጉ ራስን የሟሟቅ ስብሰባዎች ፑልፒቶችንና ጠረቤዛዎችን እየደበደብን፣ ስለጀግንነት፣ ስለ ጦር፣ ወያኔን ስለመጣል፣ በየዳያስፖራ ቴሌቭዥኖችና ራዲዮኖችን ለሰዓታታ እየለፈፍን፣ በባዶ መፎከራችን ላይ ነዉ ያለኝ ትልቁ ችግርና ነቀፌታ። አስመሳዮችና ግብዞች ነዉ እያስመሰለን ያለዉ። እኛን እያዩ እነ አቶ መለስ ይሰቃሉ እንጂ አይደነግጡም። አንድ ጊዜ አቶ መለስ የተናገሩት ነገር ነበር። «ስለጠመንጃ ማዉራት አንድ ነገር ነዉ። የባሩዱን ሽታ ማሽተት ሌላ ነገር ነዉ» ነበር ያሉት።
ይህን አይነት ትችት በዶር ብርሃኑ ነጋ ላይ ማቅረቤ፣ ምናልባት የተወሰኑ የፖለቲካ መሪዎችን በጭፍን የሚከተሉና የሚያመልኩ ግለሰቦችንና የድህረ ገጽ ባለቤቶችን ሊያስከፋ ይችል ይሆናል። ነገር ግን የዶር ብርሃኑ በሰላማዊ ትግል እንዲሁም አገር በት ባሉ ሰላማዊ ድርጅቶች ላይ፣ ያነጣጠረዉ የአደባባይ ጥቃት፣ ምላሽ ማግኘት ስላለበት ነዉ ብእራችንን ያነሳነዉ። እዉነት በመነጋገር ነገራችንን ፍርጥርጥ በማድረግ፣ የሚበጀኝን ከማይበጀን እየለየን ፣ በተቻለ መጠን ወደ አንድ አቅጣጫ ሁላችንም በአንድነት መድረስ የምንችልበትን ሁኔታ እንዲፈጠር ነዉ ይህ የተጻፈዉ።
በዚህ አጋጣሚ አሳማኝ የተቃዉሞ ነጥቦች ከቀረቡልኝ፣ ምንጊዜም ለመታረምና ለመገሰጽ ዝግጁ መሆኔን መግለጽ እወዳለሁ። «በሰለጠነ ፣ ጨዋነት በተሞላበት መልኩ እንወያይ። አንሰዳደብ። ስንዴዉን ከእንከርዳዱ እንለይ። እኔ የሰላማዊ ትግል ይሰራል። አገዛዙ በከፈተዉ በር አልፈን፣ ከሰሙንና ዝግጁ ከሆኑ ከአገዛዙ ጋር ዉይይት አድርገን፣ ካልተቻለም የተዘጋዉን በር ሰላማዊ በሆነ መንገድ እራሳችን አስከፍተን፣ መሳሪያ ሳንይዝ፣ የሰዉ ሕይወት ተኩሰን ሳናጠፋ፣ ቦምቦች ሳናፈነዳ፣ አገዛዙን አስገድደን ለዉጥ ማምጣት እንችላለን» ባይ ነኝ። «የሰለማዊ ትግሉ ትልቅ ሥራና ድርጅታዊ ግንባታ ስለሚያስፈልገዉ፣ ከሕዝቡ ጋር በአገር ቤት ያሉ የሰላማዊ ታጋዮችን እንደግፍ፤ አቅማቸዉን እንዲያጎለብቱ ከጎናቸዉ እንቁም» የሚል ጠንካራ አቋም አለኝ።
«አይ ተሳስተሃል» የምባልም ከሆነ፣ ዉጤት የሚያመጣ፣ በሕዝባችን ላይ የተዘረጋዉን ቀንበር የሚሰብር ማናቸዉም አይነት አማራጭ ከቀረቡልኝ ለማዳመጥ ዝግጁ ነኝ። ሰላማዊ ትግልን የምደገፈዉ፣ ሰላማዊ ትግል ለሚያራምዱ ለአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ ያለኝን ሶሊዳሪቲ የምገልጸዉ፣ አሁን ኢትዮጵያ ባለችበት ሁኔታ የሚጠቅመዉ፣ የሚያዋጣዉ፣ ዉጤትም ሊያመጣ የሚችለዉ እርሱ ብቻ ነው ብዬ ስለማመን ነዉ ፤ እንጂ ከሰላማዊ ትግል ጋር ስለቆረብኩኝ አይደለም።
ዶር ብርሃኑ ነጋ ከኢሳት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፣ በኤርትራ ጉዳይ ላይ እንዲሁም ስለኦነግ የተናገሩት ሰፊ ሃተታዎች አሉ። በነዚያ ዙሪያ የግሌን አስተያየቶች ይዤ ሌላ ጊዜ እመለሳለሁ። እስከዚያም ለሁላችንም ቸር ይግጠመን!