[አንድ ለቅዳሜ] የአደባባይ ምሑራኑ የት ገቡ?

ከሁለት ዓመት በፊት፤ ዝነኛው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ “ስታፍ ላውንጅ”። በወቅቱ ከሥራዬ በተጨማሪ የዩኒቨርሲቲው የድኅረ ምረቃ ተማሪ ስለነበርኩም ጭምር ከግቢው አልጠፋም ነበር። በንባብና በመጻፍ መካከል የቡና እረፍት ለማድረግ ስታፍ ላውንጅ እንደገባሁ በአንድ ጠረጴዛ ዙሪያ ወደ ተቀመጡት መምህራን እንድቀላቀል የተሰጠኝን የግብዣ ምልክት አክብሬ የጨዋታው ተሳታፊ ሆንኩ። ቦታው ዩኒቨርሲቲ በመሆኑ ብቻ የጨዋታው ርእሰ ጉዳይም ይሁን ይዘት የተለየ እንዲሆን መጠበቅ የዋህነት ነው። ትምህርት የቀመሱ ኢትዮጵያውያን የሚያደርጉት የቡና ላይ ጨዋታ በአብዛኛው መሠረታዊ ጠባዩ አይለወጥም። በየመካከል ሳቅ ጣል እየተደረገበት “የሐሳብ በየአይነቱ” ይነሳል፣ ይወድቃል። ሒሳብ ተወራርዶ አስተናጋጁ የቡና ስኒዎችን ሲሰበስብና ታዳሚዎቹ ለመሄድ ሲነሱ ግን አንዱንም ሐሳብ ቢሆን የምር የሚወስደው ሰው እምብዛም አይገኝም።

ጥቂት ዶክተሮች እና ጥቂት ወጣት መምህራን በተገኙባት ጠረጴዛችን ፖለቲካም፣ የኅብረተሰብ ለውጥም ወዘተ “ጨዋታን ጨዋታ እያነሳው” ተዳሰሱ። ተማሪ ብቻ ሳልሆን ጋዜጠኛም ስለሆንኩ ጭምር ሐሳቦቹን ላለመርሳት ስልኬ ላይ አጫጭር ማስታወሻ መውሰድ ነበረብኝ (የቡና ታዳሚዎቼን ማንነት ለመደበቅ ስል ርእሰ ጉዳዮቹንም እዚህ መጥቀስ አልተገባኝም፤ ይልቁንም ለዚህ ጽሑፍ ጭብጥ የሚረዳ አይደለም)።

በመጨረሻ ሁላችንም ወደየጉዳያችን ስናመራ “ሊጻፍባቸው ይችላሉ” ካልኳቸው ሐሳቦች አንዱን ካነሱት መምህር ጋራ በአንድ አቅጣጫ የምንሄድ ነበርን። አጋጣሚውን ካገኘሁ አይቀር በሚል በርእሰ ጉዳዩ ላይ ማንበብና ጋዜጣ ላይ ጥቂት መስመሮች መጻፍ እንደምፈልግ ነገርኳቸው። ምሁሩን ራሳቸውን “ጻፉልን” ብሎ መጠየቅ ቀላሉ ነገር ነበር፤ ሆኖም ከዚህ ቀደም እንዲህ አይነት ጥያቄ ደግሜ እንዳላነሳባቸው የገባሁትን ቃል ማክበር ነበረበኝ። አስገራሚው ነገር “የማነበውን ጠቁሙኝ” ለሚለው ጥያቄ ጭምር የሰጡኝ መልስ ነው። ሰውየው ጉዳዩን ሌሎች ሰዎች ባሉበት ስላነሳነው አሁን ብጽፍበት ለእርሳቸው ጥሩ እንደማይሆን ነገሩኝ። በጉዳዩ ላይ መጻፌንም ለወራት አቆየሁት። ይህ አጋጣሚ የአገራችን ፖለቲካዊ ምኅዳር ለምሁራን ምን ያህል አፋኝ እንደሆነባቸው ያስታውሳል፤ የዚያኑም ያህል ስለምሁሮቻችን ምንነትና ማንነት እንደገና እንዳሰላስል አስገድዶኝ ነበር።

ብዙዎቹ የኢትዮጵያ ምሁራን አደባባይ ወጥቶ መናገርን አጥብቀው ይጠላሉ። አንዳንዶቹ በራሳቸው የትምህርት ዘርፍ ጭምር ባላቸው እውቀት ስልማይተማመኑ እውቀታቸውን እንደ ጥንቆላ ክታብ ሳይገለጥ እንዲኖር የሚፈልጉ ናቸው። አንዳንዶቹ ደግሞ በራሳቸው ጠባብ የጥናት ዘርፍ የተመሰገኑ ቢሆኑም “ፖለቲካን” በተመለከተ ያላቸው አመለካከት በጣም የተዛባ ነው፤ ስለዚህም በሕዝብ አደባባይ ፈጽሞ ባለመገለጥ ከማኅበረሰባቸው የሚደበቁ ናቸው። አንዳነዶቹ ትምህርትን/መማርን እውቀትን እና በዚያም በኩል “እውነትን” የመፈለጊያና የማስፋፊያ መንገድ አድርገው አይመለከቱም፤ ምሁር በመሆንና ሾፌር በመሆን መካከል የሚታያቸው ልዩነት የሚያስገኝላቸው ክብርና ሀብት ብቻ ነው። ስለዚህም አደባባይ የሚወጡት ክብርና ገንዘብ የሚያስገኝላቸው ሆኖ ሲያገኙት እንጂ ስለሌላ የላቀ ዓላማ (መርህ፣ ፍትሕ፣ ነጻነት፣ ሳይንሳዊ እውነት ወዘተ) ሲሉ አይደለም። ጥቂቶቹ በትምህርት ዘርፎቻቸውም ይሁን ከዚያ ውጪ አስተዋጽኦ የማድረግ ማኅበረሳባዊ ሐላፊነት እንዳለባቸው ይረዳሉ፤ ሆኖም አደባባይ ወጥቶ ሕሊናቸውና እውቀታቸው የሚላቸውን በመናገር ማኅበረሰብን ለመቀየር ዋጋ መክፈል አይፈልጉም፣ ወይም ዋጋው ብዙ ሆኖ ይታያቸዋል፣ ወይም ከዚህ ቀደም የከፈሉት ዋጋ (ካለ) በቂ እንደሆነ ያምናሉ። ዝርዝሩ ራሱን የቻለ ጥናት የሚጠይቅ ነው።

ይህ እውነታ አሁን የተፈጠረ አይደለም፤ ቀድሞም የነበረ ነው። በዚህም ምክንያት “ተማሩ” የሚባሉትን ወይም ተማርን የሚሉትን ያህል የአደባባይ ምሁራን (Public Intellectuals) ለማግኘት አልታደልንም። ታዋቂው ጸሐፊ ኤድዋርድ ሴይድ (Representations of the Tntellectual) “ምሁሩ ማን ነው?” የሚለውን የብያኔ ጥያቄ ሲመልስ እንዲህ ይላል፤

“The intellectual is an individual with a specific public role in society that cannot be reduced simply to being a faceless professional… The intellectual is an individual endowed with a faculty for representing, embodying, articulating a message, a view, an attitude, philosophy or opinion to, as well as for, a public. And this role has an edge to it, and cannot be played without a sense of being someone whose place it is publicly to raise embarrassing questions, to confront orthodoxy and dogma (rather than to produce them), to be someone who cannot easily be co-opted by governments or corporations, and whose raison d’etre is to represent all those people and issues that are routinely forgotten or swept under the rug. The intellectual does so on the basis of universal principles: that all human beings are entitled to expect decent standards of behavior concerning freedom and justice from worldly powers or nations, and that deliberate or inadvertent violation of these standards need to be testified and fought against courageously.”

በሪትዝ ሐሳብ የሚስማሙት አለን ላይትማን የአደባባይ ምሁራንን በሦስት ይከፍሏቸዋል። ለላይትማን የአደባባይ ምሁር ማለት፣

“Such a person is often a trained in a particular discipline, such as linguistics, biology, history, economics, literary criticism, and who is on the faculty of a college or university. When such a person decides to write and speak to a larger audience than their professional colleagues, he or she becomes a “public intellectual.””

ደረጃ አንድ፡ በዚህ ደረጃ የሚመደቡት ምሁራን የሚጽፉትም ሆነ የሚናገሩት ስለራሳቸው ጠባብ የጥናት ዘርፍ ብቻ ነው። ይህም ለሕዝቡ ፋይዳ ያላቸውን ጉዳዮች በጥልቀት በማብራራት በኩል በጣም ጠቃሚ ነው። ሰዎቹ የጥናት ክልላቸውን ድንበር በምንም መልኩ ተሻግረው አይገኙም።

ደረጃ ሁለት፡ ወደዚህ ደረጃ የተሸጋገሩ ምሁራን ከራሳቸው ጠባብ የጥናት ዘርፍ ተነስተው ጉዳዩ ያለውን ማኅበረሰባዊ፣ ባህላዊ እና ፖለቲካዊ ፋይዳ አስመልክተው ይጽፋሉ፣ ይናገራሉ።

ደረጃ ሦስት፡ በዚህ ደረጃ የሚደርሱ ምሁራን እንደ ምልክት መቆጠር ይጀምራሉ። ከጥናት ዘርፋቸው የሰፋና የበለጠ ትልቅ ሐሳብን የሚወክሉ ግዙፍ ስብእና ይላበሳሉ። ስለዚህም ከጥናት ዘርፋቸው ውጭ ባሉ ነገር ግን የላቀ ዋጋ ባላቸው ማኅበረሰባዊ፣ ፖለቲካዊ ወዘተ ጉዳዮች ላይ እንዲናገሩ እና እንዲጽፉ ይጋበዛሉ። የሚሰጡዋቸው ሐሳቦችም የምር ይወሰዳሉ። ጸሐፊው አንስታይን በፖለቲካ፣ በትምህርት፣ በፍልስፍናና በመሳሰሉት ጉዳዮች ላይ ሳይቀር አስተያየቱን ይጠየቅ እንደነበር በምሳሌነት ያነሳሉ።

ይህ የምሁራን “ድንበር ዘለል” የአደባባይ ተሳትፎ ትንተና በሌላ ሊተካም ሆነ ሊሻሻል የሚችል ነው። ቁም ነገሩ ግን አይለወጥም፤ ምሁራን በማኅበረሳቸው ውስጥ የሚኖራቸው ሚና የተለያየ ደረጃ ያለው መሆኑ። እርግጥ አንድ የተማረ ሰው ከምንም ተነስቶ ወደ መጨረሻው ደረጃ ለመድረስ የሚያስችለው ውጫዊ ሁኔታ ከጊዜ ጊዜ፣ ከቦታ ቦታ ይለያያል። ይሁንና እጅግ ወሳኙ ግብአት የግለሰቦቹ ውስጣዊና ግላዊ እምነት፣ ፍላጎት እና ግብ ነው። ቀድሞውኑ የምሁራኑ መገለጫ ነባራዊውን/ያለውን እያጸደቁና እያደነደኑ መኖር ሳይሆን ለሰው ልጅ የተሻለ ሕይወት ለማምጣት ያለውን መለወጥ/መረበሽ ነውና ውጫዊ ሁኔታው ከጅምሩ አጋዣቸው እንዲሆን አይጠበቅም። ይህም ሸክሙን ከውጭ ወደ ውስጥ ይመልሰዋል።

የእኛ የሕዝባዊ ምሁራን እነማን ናቸው? በእኔ ዕድሜ (የላይትማንን ደረጃ ልጠቀምና) ወደ ሦስተኛው ደረጃ መድረስ ችለው የነበሩ የአደባባይ ምሁር ፕሮፌሰር መስፍን ብቻ ናቸው። አሁን ደግሞ ጊዜው አጭር ቢሆንም ዶክተር ዳኛቸው አሰፋ ናቸው። የፕሮፌሰር መስፍን ወደ ፓርቲ ፖለቲካ መግባት (በተለይም የቅርብ ጊዜው የውዝግብ ድራማ) የሚያስነሳው ጥያቄ ቢኖርም ሰውየው ከአደባባይ ምሁርነታቸው የወረዱ አይመስለኝም። ምናልባትም አጋጣሚው የአደባባይ ምሁራንን በፓርቲ ፖለቲካ የሚኖራቸውን ተሳትፎ እንድንቃኝ የሚጠይቅ ነው። ነጻነት ባለበት የምእራቡ ዓለም ያሉና የአደባባይ ምሁር (public intellectual) መባል የሚገባቸው ጸሐፊዎች፣ ተናጋሪዎችም አሉ፣ ቁጥራቸው የእድሉን ያህል አይደለም እንጂ።

ሪትዝን የመሰሉ ጸሐፊዎች የአደባባይ ምሁርነትን ያለውን/ገዢውን አመለካከትና አሰራር በመቃወም ጭምር መለካት እንዳለበት ያምናሉ። ይህም ተቃውሞው ርእዮተ ዓለማዊ፣ የፖሊሲ፣ የአፈጻጸም (አንዱን ወይም ሌላውን) ገጽታ እንደሚኖረው ግልጽ ነው። ይህ ማለት ግን የግድ የተቃዋሚ ፓርቲ ደጋፊነትን የሚጠይቅ ተደርጎ መወሰድ አይችልም፤ በመሠረቱ የገዢው ቡድን/አመለካከት ደጋፊ ሆኖም ለውጥን ማቀንቀን ይቻላል። የዚያኑ ያህልም ገዢውን ፓርቲ መቃወም ምሁራዊ አስተዋጽኦን/ደረጃን የሚቀንስ አለዚያም የተቃዋሚ ፓርቲ ታማኝ ደጋፊ ብቻ አድርጎ የሚያስቆጥር ሊሆን አይችልም።

እያወቁ እንዳላወቁ፣ እያዩ እንዳላዩ፣ እየሰሙ እነዳልሰሙ ሆኖ፣ በለሆሳስ ማንጎራጎር፤ በራስ ዝምታ ውስጥ መቀበር የዘመኑ ፈሊጥ ሆኗል። ይህም ቢሆን ከባድ የመሰላቸው ደግሞ “አንድ ቀንን” እየጠበቁ ንጉሡ መስማት የሚፈልጉትን እየዘፈኑ ቢያንስ ምትሐታዊ ውጫዊ ሰላም ለመፍጠር ይሞክራሉ። የቀሩት ደግሞ በንጉሡ ዙፋን ዙሪያ ተሰብስበው በየቋንቋቸው፣ በየሞያቸው “ሺህ ዓመት ንገሥ” ይላሉ፤ የሺህ ዓመቱ መንግሥት ስለፈጠራት/ስለሚፈጥራት ምድራዊ ገነት ምሁራዊ ቡራኬ ይሰጣሉ፤ “ከዚህ በላይ ምን ትፈልጋላችሁ?” ሲሉ ምሁራዊ ተሳልቆ ያሰማሉ።