በምግብ እጥረት ለተጠቁ ወገኖች 20 ሚሊዮን ዶላር ርዳታ ተጠየቀ

(ሙሉ ገ)

በምግብ እጥረት ለተጎዱ ዜጎች ከምግብ እርዳታ ውጪ 20 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር የእርዳታ ድጋፍ ያስፈልገኛል ሲል የግብርና ሚንስቴር ለለጋሽ አገሮች እና ለእርዳታ ድርጅቶች አስታወቀ።

ህዳር 15 ቀን 2003 ዓ.ም በቀድሞው አደጋ መከላከልና ዝግጁነት ኤጀንሲ መሰብሰቢያ አዳራሽ ከቀኑ በ10፡00 ሰዓት ላይ ለለጋሽ አገሮችና ለጋዜጠኞች በተሰጠው መግለጫ ላይ የግብርና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ምትኩ ካሳ የተረጂው ቁጥር ወደ ሁለት ሚሊዮን ሦስት መቶ ሺ ወርዷል ብለዋል፡፡  የአማራ እና ሌሎች ክልሎች ሪፖርትና ዳታ በወቅቱ ባለመድረሱ ይቅርታ የጠየቁት ሚንስትር ዴኤታ አቶ ምትኩ ካሳ ከሁለት ሚሊዮን ሦስት መቶ ሺህ ከተገመቱት ተረጂዎች ውስጥ፣ 29.2 በመቶ ከሶማሌ ክልል፣ 29 ከመቶው ከትግራይ ክልል እና 26.3 በመቶ ከኦሮሚያ ክልል መሆኑን አብራርተዋል፡፡

በ2002/03 ዓ.ም ምርት ዘመን በነበረው የተሻለና ለግብርና ሥራ እንቅስቃሴ አመቺ ሆኖ የተገኘ የበልግና የመኸር ዝናብን ተከትሎ በእርዳታ ፈላጊ አካባቢዎች ያለው የምግብ ዋስትና ሁኔታ በመጠኑ የተሻሻለ ቢሆንም፣ ገና የአማራና ሌሎች ክልሎች ዳታ በአግባቡ ባልተሰበሰበበት ሁኔታ በአገሪቱ የዕለት የምግብ እርዳታ ፈላጊ ቁጥር ቀንሶ ወደ 2 ነጥብ 3 ሚሊዮን ሕዝብ ዝቅ ብሏል ተብሎ በመንግሥት የተሰጠው የችኮላ ድምዳሜ ትልቅ ግነት እንዳለበት ይሰማኛል በማለት አዲስ ነገር ያነጋገራቸው የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የዜና ምንጭ ገልጸውልናል፡፡

እኝሁ በግብርና ሚኒስቴር በቅድሚያ ማስጠንቀቂያ ምላሽ ዳይሬክቶሬት ውስጥ የሚሠሩ የዜና ምንጫችን እንደነገሩን በተያዘው የፈረንጆች ዓመት በኢትዮጵያ በሴፍቲኔት ፕሮግራም ምግብ ለሥራ የታቀፉ ዜጎች ቁጥር በሦስት መቶ ሺህ መጨመሩን ገልጸውልናል፡፡

እንደ ዜና ምንጮቻችን ገለጻ “ በምግብ ለሥራ ፕሮግራም”  የታቀፉ የገጠር ነዋሪዎች ከ7 ነጥብ 5 ወደ 7 ነጥብ 8 ሚሊዮን ያሻቀበው ከዚህ በፊት በሴፍቲኔት ምግብ ለሥራ ፕሮግራም ታቅፈው የማያውቁ በአፋር እና በሶማሌ ክልሎች ያሉ ወረዳዎች በምግብ እጥረት በመጠቃታቸው ነው፡፡   በርካታ ሕዝብ በየዓመቱ ተጨማሪ የአስቸኳይ ጊዜ የዕለት የምግብ እርዳታ አቅርቦት ድጋፍ የሚፈልግ ነው ያሉን የዜና ምንጫችን፣ በተያዘው የፈረንጆች ዓመት (2010 እ.ኤ.አ) በተደረገ የዳሰሳ ጥናት 5 ነጥብ 2 ሚሊዮን ኢትዮጵያዊያን የዕለት እርዳታ ድጋፍ አቅርቦት የሚሹ ኾነው የተገኙ ናቸው ብለውናል፡፡

በኢትዮጵያ በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋዎች በተለያዩ ጊዜያት የዜጎችን ሕይወት የሚቀጥፍ ሲሆን፣ ከ1986 ዓ.ም ጀምሮ ብሔራዊ የአደጋ መከላከልና ዝግጁነት ፖሊሲ ሥራ ላይ ቢውልም ለውጥ ማምጣት ባለመቻሉ ከ2000 ዓ.ም ጀምሮ በግብርና ሚኒስቴር ሥር ተጠቃሎ ሥራውን እንዲያከናውን ተደርጓል፡፡