ሀገር ጥለህ መኮብለል የሚቢጀው ማንን ነው? ዲ/ን ሙሉጌታ ወልደገብርኤል
ሁልጊዜ የክፉዎች፣ ገፊዎች፣ የአመጸኞችና አስጨናቂዎች መዝገበ ታሪክ እያገለባበጥን ግድፈት፣ ክፋት፣ ሴረኝነትና አረመኔነት ማተት ብቻ ሳይሆን አንዳንድ ጊዜ ደግሞ (በተለይ በአሁን ሰዓት) ዓይን የማፍረጥና እጅ የመቆረጥ ያክል ቢያመንም፣ ባንፈልገውም የሚያስፈልገን፣ ጀሮአችን ይሰማው ዘንድ ባይወድም ነፍሳችን ማወቅ የሚገባትን፣ የሚበጀንና ህልማችንን እውን የሚያደርግ፣ የሚፈለገውንም ስፍራ የሚያደርሰን እስከሆነ ድረስ እርስ በርሳችን በግላጭ መነጋገሩ፤ ከዚህም አልፎ እንደሌሎች የአፍሪካ ሀገራትም ሆነ የዓረብ ማኅበረሰብ ለነጻነት ያደረጉትንና እያደረጉትን ያሉትን ተነሳሽነትና እንቅስቃሴ ይልቁንስ በከፋ የባርነት አገዛዝ አዘቅት ውስጥ የምንገኘውን ዜጎች የሚፈለገውን ያክል መሄድ ያልተቻለበትና አመርቂ ውጤት ልናስመዘግብ ያልቻልንበት በአንጻሩ በፖለቲካ ጥቃት ስም ጥቂት ግለ ሰቦች ኑሮአቸውን ሲያደላድሉና ተጠቃሚዎች ሲሆኑ ብዙሐኑ ሕዝብ ደግሞ ሰለባ የሚሆንበት ምክንያት ምንድ ነው? በማለት ላዛሬው ጣቶቻችንን በሌሎች ደንደስ ላይ ከማኖር አንስተን እንቅስቃሴዎቻችንን መመርመርና እርስ በእርሳችን በሰከነ መንፈስ መነጋገሩና ለችግሮቻችን መፍትሔ እናመጣ ዘንድ መመካከሩ ጸሐፊው ከእኛ በላይ ተጠቃሚ ሌላ ማንም ሊኖር አይችልም በሚል እምነት አጀንዳው ጥቂቶችን ባያስደስትም በዛሬው ዕለት መልዕክታቸው ግድፈቶችን ከመጠቆምና ከማሳየት በላይ መፍትሔ ይሆናል በማለት ያመኑትንም አካትተው ቀርቧል።
በቅድሚያ ግን ይህ ጥያቄ አዘል ጽሑፍ የኢኮኖሚ ጀንደረባ ከመሆን የተነሳ ለተሻለ የኑሮ ፍለጋ እንደ ጨው ለተበተነ ዜጋ የማይመለከት መሆኑን ለመግለጽ እወዳለሁ። በተጨማሪም የጽሑፉም ሆነ የጸሐፊው ዓላማና ጭብጥ ማንን ለመውቀስና ለመኮነን እንዳልሆነ ሁሉ የጽሑፉ አዘጋጅ ስለ ራሱ ርዕሱን በተመለከተ የአንባቢያን አእምሮ ሚዛን ለመጠበቅ ሲባል ለእግዚአብሔር ክብር በጥቂቱ አንዳንድ ቁምነገሮችን ለማውሳት ይወዳል። ይኸውም፦
የሰው ልጅ የብዛቱ ይህል ጸባያችንም እንዲሁ ነውና ርዕሱን በማየት ብቻ የጽሑፉን ሙሉ ይዘት ያነበቡት ያክል በመቁጠር በቅጽበት ድምዳሜ ላይ የሚደርሱ አንዳንድ ወገኖች “እግዚኦ – አቤት! ያለተነካ ግልግል ያውቀል!” ማለታቸው አይቀርም። እውነት ነው ለተቀማጭ ሰማይ ቅርቡ እንደሚባለው “ያልተካ ግልግል ያውቃል” ማለቱ አባባሉ በራሱ አንዳች ስህተት የለውም። እውነት ለመሆኑም የሚያጠያይቅ አይደለም። ሰው ስላልዋለበትና ስላላፈበት ህይወት/ነገር ብዙና ጥቂት ማለቱም የተለመደ ነው። መቀመጫውን አደላድሎ ሲያበቃ የቆመውን እንዲህ ቢያደርገው ኖሮ፣ አይ! አንዳፍታ አበላሸው፣ እናንተ ሰው የለም ወይ! … (የሰናፍጭ ቅንጣት ታክል ሞያ ሳይኖሮት (የዋሉበት እንደሆኑ ነው) በባለ ሞያ ትክሻ ላይ የሚዘረግፉትን ቃላቶችን እያሰቡ ይጨምሩብርት)
ዳሩ ግን ባለ ጦማሩ በዚህ ሁሉ አይታሙም። ያለ ጥርሳቸው አሸዋ ለመፍጨትም አይቃጣቸውም። ከመነካት ያለፈ ተሸራርፈው የቀረውን ጆሮና እግራቸውን ይዘው ወደ ጎረቤት አገር በማቅናት ከድልድይ ሥር ተጠለው ክፍውን ቀን አሳልፈው ሲያበቁ ዛሬ ደግሞ የስደት ጠባሳ ያረፈባቸውን ምልክት ሳይለቅ ሰዎች ከእህል ብዛት የተነሳ በዊልቸር ተቀምጠው በሚሄዱባት ምድር ላይ ኑሮአቸውን በማድረግ ከፊታቸው የሚጠብቃቸውን የሞትና የህይወት ፍልሚያ በግንባር ቀደምትነት ለመሰለፍ ራሳቸውን እያዘጋጁ/በቃርሚያ ይገኛሉ። (ባህላችን ስለራሳችን ብዙ ማለቱ ስለማይፈቅድልንና ሌላ ስምም ስለሚያሰጥ ጸሐፊው ርዕሱን ለመወያያ ሲያቀርቡ ባለሙሉ መብት መሆናቸውን በዚህ አጋጣሚ ለመግለጽ ይወዳሉ)።
ሐሜታ ወይንም ደግሞ ሌላ ነገር አይደለም ማጣቀሻ የማያስፈልገው ሐቅ ነው በማለት ወደ ቁምነገሬ ልዝለቅ። ቁምነገሩ ወዲህ ነው አንዳንዱ ቀድሞ ይኖርባት በነበረችውን ምድር “በሀገሩ” ሳለ ያላገኘውን በፖለቲካ ስም በደማቅ ሽኝትና በታላቅ ዝግጅት ሀገር ጥሎ ሲኮበልል ጭፈራ ቤት እያማረጠ እየዞረ ሲፈነጭ እዘዝ በገላዬ እየተባለ ነፍሱን ጥሎ ሲዘልና ሲቧርቅ፣ ሌሎቹም ሀገር ቤት ሳሉ ይቅር ሊኖሩበት የሚወረውርዋት ጠጠር የማይገባበትን የተንጣለለ ቪላ ገብተው ኖሮው ሲያበቁ ሌላው ደግሞ አፈር ላይ ወድቆ አቧውን አራግፎ ሲነሳ የቻሉበት ራሳቸውን ስደተኛ ብለው ሲጠሩ ሌላውም ተቀብሎ የሚሚያስተጋባ ከሆነ የስደት ትርጉምም እንዲህ ከሆነ ከእንግዲህ ወዲህ አማርኛ ቋንቋ ሁላ ላያግባባን ነው። ከዚህም በላይ ሐቁን ለማወቅ የሚፈልግ ቢኖር (አሁንም ለተሻለ ኑሮ የሚፈልሰውን ዜጋ አያካትትም) ስም ያላቸው “ፖለቲኮኞቻችን” አይደለም ራሳቸውን ስደተኛ ብለው ሊጠሩ ገና አጥንታቸው ከስጋቸው ተገናኝቶ እንዲህ ያለ አለም አለ እንዴ! እንደው አንዳንዱማ “ምን ነው እንዲህ ያለ ነገር መኖሩን ባውቅ/ቀደም ብሎ በተገለጠልኝ ኖሮማ በደርግ ዘመን ነበር የምወጣው በማለት በዕድሜው የሚጸጸት ገና እንደተወለደ ህጻን ልጅም ኑሮን መኖር የሚጀምሩት በስላቅ የስደት ምድር በማለት በሚጠሯት ከተማ እንደሆነ ነው።
ሌላው መጽሐፍ “በአንዲቱ ከተማም መከራ ቢያሳዩአችሁ ወደ ሌላይቱ ሽሹ” እንዲል ዘወር ማለቱ ባልከፉ የእኛ ነገር ግን ሥራችን ሁሉ በስሌት ማለት የትም በማያደርስ ብልጣብልጥነት በመሆኑ እሄው ምድሪትዋ ፍሬ አልባ በለስ ሆና መቅረትዋን በቂ ማሳያ/ምሥክር ነው። የኃይለ ቃሉ ባለቤትም ሆነ ተከታዮቹ ዘመነ መዋዕላቸው ሁሉ በሰበብ አስባቡ/ዕንቅፋት በገጠማቸው ቁጥር ውኃ ቀጠነ እያሉ ሲሰሹና ሲበረግጉ አልኖሩም እንጂ ከአንድም ሁለቴ ነገር ከረር ሲል ራሳቸውን ሲደብቁ ብሎም ወደ ሌላ ስፍራ ዘወር ዘወር በማለት ወደ ቀድሞ ቦታቸውን ተመልሰዋ። የፈለገውን ያህል ኃይል ቢሰለፍ መቆም በሚገባቸው ጊዜ ግን ደስታቸው ከሰው ደስታ ይልቅ መቶ ዕጥፍ በሚበልጥ ስብእና ተሞልተው ቀድሞ የሚያውቁትንና የተለማመዱትን ምክንያት አቅም በማሳጣት የሞት ጽዋ ተጎንጭተው ዘመናትን የሚሻገር ቃል ትተው አልፈዋል። ውድ አንባቢ ሆይ! በእጅዎ የያዙት ወይንም ደግሞ የሚመኙት መልካም ነገር አልዎት? እንግዲህ የሰው ልጆች የሚሹትንና የሚመኙትን ሁሉ የሞት ፍሬ ለመሆኑ ላንዳፍታ አይጠራጠሩ ከታላቅ ድል ጀርባ ታላቅ መስዋዕትነት አለና።
ግልጽና ቀለል ባለ አነጋገር ሀገሪትዋ/ሀገራችን አሁን ባለችበትና በምትገኝበት ነበራዊ ሁኔታ በስሜትና በሞቅታ ወደ ትግሉ መስምር አልያም በስህትት ካልተቀላቀሉ በስተቀር በዚህ ወቅት ሀገርንና ሕዝብን ጥለህ የሚያስኮበልል ምንም ዓይነት ምክንያት የለም። ለሁሉም ጊዜ አለው! ለመሸሽም፣ ዘውር ለማለትም ጊዜ አለው! ጸንተህ ለመቆም፣ እውነታውን ለመጋፈጥ፣ የሞት ጽዋውንም ለመጎንጨት ጊዜ አለው!! ታሪክ እንደሚነግረን ከዘውዳዊው አገዛዝ ጀምሮ ዓይናቸውን የከፈቱት ሁሉ ገና ለገና ይደርስብኛል በማለት ሳይሆን በተጨባጭ ከሚደርስባቸው ግፍና የመከራ ጽናት የተነሣ ሀገር ጥለው ተሰደዱ፣ ሄዱ፣ ወጡ ነው። ጥያቄው እከመቼ እየተሸሸ ይኖራል የሚል ነው? እንግዲህ በዚህ ትውልድ ሀገር ጥልህ በሚደረግ ጉዞ ተጎጂው ዘር የማይወጣላት ምድርንና ሕዝብ ሲሆኑ ተጠቃሚዎቹ ደግሞ ልበ ድንግጡ ብልሐተኛው ግለሰብና ሥርዓት አልባው መንግሥት ይሆናሉ። ይህ ማለት ብልሐተኛው ኑሮውን ሲቀይር አመጸኝውን ደግሞ ኸይ ባይ በሌለበት ሁኔታ ራሱን አደልድሎ ዕጣ ፍንታው ባርነት በሆነ ሕዝብ ጫንቃ ላይ ተጣብቆ ደም መጣጣቱ ይገፋበታል። ሽሽቱ ይህን እያወቅን ከሆነም ሕዝብ ማንን እየተከተለ እንዳለ ለማወቅ ይቻለው ዘንድ አካሄዳችንና አሰራራችንን ለሁሉም ግለጽ ይሁን።
ይህ ድምዳሜ የማይዋጥለት ማንም ቢኖር ግን በታላቅ አክብሮት እህቺ ነፍስ ከጎጇ ጨውና በርበሬ አልፋ ሕዝባዊ አጀንዳ ኖሯት ስለ ሀገር ጉዳይ ጨርሳ እንዳትጨነቅ፣ እንዳታስብ ነው የምትመከረው። ዓይኑን አፍጥጦ ጥርሱን አግጥጦ ለሚመጣ ወገብህን ሸጥ አድርገህ ታጥቀህ በተጠንቀቅ ቁመህ መጠበቅ ሳለ በተቃራኒው ለውጊያ ጦር ሜዳ ወርድህ ስታበቃ ለምን የጥይት ድምጽ ሰማሁ በማለት ለሚወሰደው እርምጃ ከተወጣ በኋላ ቢቻል ክፉና ደጉ አለማለትን መምረጥ (እጅህንና አፍህን መሰብሰብ) ካልሆነ ደግሞ ጸሐፊው ጨዋታውን አልቻልኩበትም፣ ሃሳቤን ቀይሬአለሁ፣ ጥይቴ አለቀብኝ፣ መሄድ የምችለው እስከዚህ ድረስ ብቻ ነበር፣ ትንፋሽ አጠረኝ፣ አቅም አነሰኝ፣ ተረዱኝ እወቁልኝም ይባላል ባይ ናቸው። (እነዚህና መሰል ለሎች በርካታ ምክንያቶች ከመጽሐፍ ቅዱስ የተገኙ ናቸው። ምንም አዲስ ነገር የለም!)።
ውድ አንባቢ ሆይ! የገባው ያለገባው ትልቁም ትንሹም አቅሙ በፈቀደው ስለ ዲሞክራሲና ስለ ፍትሕ አቤት ብሎ ሲያበቃ፤ በመጠኑም ቢሆን በተሻለ ዲግሪ የተሻለ ግንዛቤና መረዳት ያላቸው ግለሰቦች መቅረዛቸውን ከፍ አድርገው ከፊት ለፊት እየቀደሙ ድምጻቸውን እያሰሙ፣ ትግሉን ካልመሩትና ዛሬስ አንዳችን ይለይልን በማለት ተናንቀው ይህን ሕዝብ ካላሳረፉትና ካላተረፉት ይህን ማን ይድርገው/ያደርገዋል ነው? ለመሆኑ እስከ መቼ ነው የኢትዮጵያ ፖለቲካ የድብብቆሽ ፖለቲካ ሆኖ የሚቀረው? የኢትዮጵያ ሕዝብ ብቅ ብቅ በሚሉት ግለሰቦች ሙሉ ልቡን ሲጥል፤ ይህን እውነት መሆኑን ያዩ ደግሞ እየተሸበለሉ ኑሮአችውን ሲኖሩ ማን መልካሙን ውጊያ ይምራው ነው? እንግዲህ ከወላጅ እናቱና አባቱ እንዲሁም ከጉልበቱ ፍሬ የተገኙ ልጆቹም ሆኑ ከሚስቱ ይልቅ ሀገርንና ሕዝብን በማስቀደም እኔ አለሁ የሚል አንድ ሰው ካልተገኘ በስተቀር ለማስታወሻ ይሁኖት ብጫ መልአክ መጥቶ ኢትዮጵያን ነጻ አያወጣትም። አኩና!!
ጽሑፌን ከማጠቃለሌ በፊት ግን ስለ ምን ዓይነት/እንዴት ያለ ምክንያት እያተትኩ እንዳለሁ በድጋሜ ነገሬን በግርድፉና በምሳሌ እንደሚከተለው ላስረዳ ድመት ወተት ስተሰርቅ/ለመስረቅ ስታደባ ዓይንዋን ጨፍና ነው ምን ነው ቢሉ? በእርስዋ ቤት (አዕምሮ) የእኔ ዓይን እደተጨፈነ የሚያያኝም ሰው ዓይን ይጨፈናል ብላ ስለ ምታምን ነው። ሰውና እግዚአብሔር የሚያውቀው የተገለጠ ደንቃራና ኋላቀር የኢትዮጵያ ፖለቲካ ምክንያት ተደርጎ ከሀገር ጥለህ መፍለስና ምንም ዓይነት ምክንያት አያስፈልገውም። እግዚአብሔርንና ራሳችንን ብቻ የምናውቀው ውስጣዊ ፍላጎታችንና ምኞታችንን በምክንያት አሳምረንና አሸብርቀን ለማቅረብ የደፈርን ዕለታ ግን ነገረ ዓለማችን ሁሉ ከዚሁ ሁነኛ የድመትዋ ምሳሌ የተለየ አይሆንም። ዕድሉ ቢገጥመው ይቅር ነፍስ ያለው ሰው ሳር ቅጠሉም ከኢትዮጵያ ምድር ነቅሎ ለመፍለስ ምክንያት አለው። ደግሞስ የሚደረደረው ምክንያት ማንን ለማሳመን ነው? የኢትዮጵያ ሕዝብ እንደሆነ የማንም ምክንያት የሚሰማበት ጆሮ እንደሌለው የምንስተው አይመስለኝም። እናማ! ከነገራችሁን ካሳያችሁንና ካስተማራችሁን እኛም ታላላቆቻችንን (በዕድሜ) መጠበቅ ከባህላችን ይዘን ከእናንተ መማራችን፣ ማየታችንና አሰራችሁን መከተላችን አይቀር የነጻነት ዋጋ በመውጣት ሳይሆን በመግባት አሁንም በቃል ብቻ ሳይሆን በሥራ ሆናችሁ አሳዩን። ከዚህ ውጭ ግን በለስ/ ቁልቋል የወይን ፍሬ ያፈራ ዘንድ አይቻለውም።
መዝሙረኛው ልጁን ሲመክር ልጄ ሰሎሞን ሆይ እግዚአብሔር ልብን ሁሉ ይመረምራል የነፍስንም አሳብ ሁሉ ያውቃል እንዲል እንዲሁም የዕብራውያን መጽሐፍ ጸሐፊ በዕብራውያን መጽሐፍ 4፣12 ላይ “የእግዚአብሔር ቃል ሕያው ነውና፥ የሚሠራም፥ ሁለትም አፍ ካለው ሰይፍ ሁሉ ይልቅ የተሳለ ነው፥ ነፍስንና መንፈስንም ጅማትንና ቅልጥምንም እስኪለይ ድረስ ይወጋል፥ የልብንም ስሜትና አሳብ ይመረምራል” እንዲል ይልቁንስ ይመረምራ ሲል ለማለት ያክል ወይንም ደግሞ ሥነ ፅሑፍ ለማሳመር የገባ ቃል እንዳይደለና እንዳልተባለ ብቻ ሳይሆን ለራሳችንን ከሀብታችንም ሆነ ካለን ትምህርት የተነሣ የፈለግነውን ስፍራ እንስጥ ዛሬም በዚህ ህያው ቃል መመርመራችን አይቀርም። እንደው አንዳንድ ጊዜ አገር ሰላም ነው ብለን በምራመደው እርምጃ ሳይቀር ተመዝነን ቀለን እንዳንገኝ እግዚአብሔር ይጠብቀን። የጌድዮን ሠራዊት የሚጠጣ ውኃ አገኘሁ በማለት ውኃ ለመጠጣት ሲንደፋደፍ ሠራዊቱ መቼ በሚዛን ፊት ራሱን እንደጣለ አወቀ ነውና። ከሚጠጣ ውኃ ያለፈ ወራጁ ኃያል፣ ጽንዑንና ተዋጊን ከፍርፋሬ ለቃሚውን፣ ፈሪና ልበ ድንጉጥን የሚለይ ሚዛን መሆኑን ማን አውቆ ኖሯል?
በመጨረሻ ለድህረ-ገጾች በአጠቃላይ ለመገናኛ ብዙሑን የምለው ነገር ቢኖር የተከሰተውን ሁሉ ዜና ተገኘ ተብሎ ሽፋን ከመስጠትና ነገሮችን ያለልክ ከማራገብ በፊት አንዳንድ ዘገባዎች የባለጉዳዩ አማናዊ ገጽታ/ገመና የሚያሳዩ ሆነው ሲገኙ በአደባባይ የራስን ጉድ ከመግለጥ በፊት በሚገባ ይታሰብበት ዘንድ ለማሳሰብ እወዳለሁ።
ዲ/ን ሙሉጌታ ወልደገብርኤል
[email protected]
19th Dec. 2011
Atlanta, GA