ማን እያሸነፈ ነዉ ? “ቅንጅት” ወይንስ ሕወሃት/ኢሕአዴግ ?” ግርማ ካሳ

[email protected]

የአንድነት ፓርቲ በቅርቡ ባደረገዉ ጠቅላላ ጉባዔው ፣ ዶር ነጋሶ ጊዳዳን የድርጅቱ ሊቀመንበር አድርጎ መርጧል። ይህን አስመልክቶ አጭር አስተያየት የሰጠዉ አፍቃሪ ኢሕአዴጉ አይጋ ፎረም፣ የቅንጅት ነገር እንዳበቃለት ይናገራል።

“With Gebru Asrat leading ARENA and Dr Negasso leading UDJ, MEDREK may finally shed its “tseguri hemeq” inherited from Kinjit! It will also mean EPRDF will have a formidable opposition that can talk the way it talks come next time! That is if(it is a big if) the two leaders choose to do so! Oh what a turn of events for Kinjit!” ሲል ነበር አይጋ ፎረም የቀለደዉ።

አይጋ «ቅንጅት» ሲል ስለማን መናገሩ እንደሆነ ብዙም የማዉቀዉ ነገር የለኝም። ነገር ግን የአንድነት ፓርቲ፣ ዶር ነጋሶን በሊቀመንበርነት በመምረጡ ከቅንጅት የወረሳቸዉ እሴቶችን እንዳራገፈ አድርጎ ሊነግረን ይፈልጋል። የአንድነት ፓርቲም ኢሕአዴግን እየመሰለ እንደሆነም ለማሳየት ይከጅለዋል።

ስለቅንጅት በምንናገርበት ጊዜ ከሶስት አቅጣጫዎች አስተያየቶችን ልንሰጥ እንችላለን። በብሄራዊ ምርጫ ቦርድ እዉቅና በማግኘቱ አንጻር ነገሮችን ካየናቸዉ፣ ያኔ የአራት ድርጅቶች ስብስብ የነበረዉ ፣ በምርጫ ተወዳድሮ ታሪካዊ ዉጤት ያስመዘገበዉ ቅንጅት የለም ማለት ይቻላል። ኢሕአዴግ የቀድሞ የቅንጅት አመራር አባላትን አስሮ፣ ቅንጅት የሚለዉን ስም በገንዘብ ለገዛቸዉ ሎሌዎቹ፣ ሕግ ወጥ በሆነ መንገድ ሰጥቶ፣ በአሁኑ ወቅት “ቅንጅት” በሚል ድርጅት ስር፣ ሕዝብ ተሰባስቦ እንዳይንቀሳቀስ አድርጓል። አሁን በምርጫ ቦርድ «ቅንጅት» ተብሎ የሚታወቀው በተግባር የኢሕአዴግ ሌላዉ ክፍል የሆነዉና በአቶ መለስ የሚታዘዘዉ የአየለ ጫሚሶ ቡድን ነዉ።

«ቅንጅት» ማለት የቅንጅት መሪዎች ማለት እንደሆነ አድርጎ የመዉሰድ ሁኔታም ሊኖር ይችላል። «ቅንጅት» ማለት በርግጥ የቅንጅት መሪዎች ማለት ከሆነ፣ በእርግጥ «ቅንጅት» ሞቷል ማለት ይቻላል። ለምሳሌ ያኔ አንጋፋ የቅንጅት መሪ የነበሩ የት እንዳሉ ልጥቀስ፡

1. ኢንጂነር ኃይሉ ሻዉል (የቅንጅት ሊቀመንበር) ፡ ከቃሊቲ እሥር ቤት መፈታት በኋላ፣ በቅንጅት ዉስጥ ለተፈጠረዉ ከፍተኛ የመበጣበጥ ምክንያት በመሆን ትግሉን ክፉኛ የጎዱ ሰዉ ናቸዉ። በቅንጅት ዉስጥ ያደረጉት ስህተቶች ሳያንሳቸዉ አሁን ደግሞ በመኢአድ ዉስጥ ችግርና ዉዝግብ እየፈጠሩ ነዉ። ሰማኒያ አመት ሊሞላቸዉ እንደሚችል አስባለሁ። ጡረታ ወጥተዉ፣ ፖለቲካዉን ለወጣቶች አሳልፈዉ ለምን እንደማይቀመጡ አይገባኝም።

2. ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ (የቅንጅት ተቀዳሚ ምክትል ሊቀመንበር) ፡ ለሁለት ጊዜ ወደ ቃሊቲ ከወረደች በኋላ ፣ በአሁኑ ወቅት በዋሺንግተን ዲሲ የከፍተኛ ትምህርት እየተከታተለች ናት። በመሆኑ ለጊዜዉ በፖለቲካዉ ትግል ዉስጥ እምብዛም እየተንቀሳቀስች አይደለም።

3. አቶ ልደቱ አያሌዉ (የቅንጅት ምክትል ሊቀመንበር) ፡ ቅንጅቱ ብዙ ገፍቶ ሳይሄድ ከቅንጅት በመዉጣት፣ ሶስተኛ መንገድ በሚል ኢዴፓ የተሰኘዉን ድርጅት እየመራ ሲታገል ቆይተዋል። በአሁኑ ወቅት እርሱም ለከፍተኛ የትምህርት እድል በለንደን ይገኛል።

4. አቶ ሙሉነህ እዮዔል (የቅንጅት ዋና ጸሃፊ) ፡ የፖለቲካ ጥገኝነት ጠይቆ፣ ነዋሪነቱን በአሜሪካን አድርጎ ፣ ግንቦት ሰባት ተብሎ በሚታወቀዉ ድርጅት ዉስጥ እየተንቀሳቀስኩኝ ነዉ ይላል።

5. ዶር ብርሃኑ ነጋ (የአዲስ አበባ ከተማ ተመራጭ ከንቲባ) – የሰላማዊ ትግል አይሰራም በሚል፣ ግንቦት ሰባት የተሰኘን ድርጅት መስርተዉ እርሳቸዉም እንቀሳቀሳለሁ እያሉ ነዉ። ነዋሪነታቸዉን በአሜሪካ አድርገዉ በዩኒቨርሲቲ መምህረነትም ያገለግላሉ።

6. ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማሪያም (የቅንጅት አባት ይባሉ የነበረ) ፣ ዶር ያቆብ ኃይለ ማሪያም (የቅንጅት የዉጭ ግንኙነት ሃላፊ)፣ ዶር በፈቃዱ ደግፌ (የቅንጅት የፋይናንስ ሃላፊ)፣ እንዲሁም በርካቶች መጽሃፍት ከመጻፍ፣ አንዳንድ ጽሁፎችን በጋዜጦችና በድህረ ገጾች ከማቅረብ ዉጭ ከፖለቲካዉ ወጥተዋል ማለት ይቻላል።

እንግዲህ ያኔ የቅንጅት አመራር የነበሩ ወገኖች፣ አሁን የት እንዳሉ በምናይበት ጊዜ ፣ በርግጥ ቅንጅት ማለት መሪዎቹ ማለት ከሆነ፣ ቅንጅት የለም፣ ቅንጅት ሞቷል ወይንም ቅንጅት ተሰዷል ማለት ይቻላል።

ነገር ግን ቅንጅት ማለት በምርጫ ቦርድ እዉቅና ማግኘት፣ ወይንም ግለሰቦች ማለት አደደለም። ቅንጅትን ያኔ ቅንጅት ያስኘዉ በምርጫ ቦርድ መታወቁ ወይንም የሚመሩት ግለሰቦች ሳይሆን፣ ይዞ የተነሳዉ አጀንዳዎቹ ነበሩ። ቅንጅት ሕዝቡ ለኢትዮጵያዊነቱ፣ ለአንድነቱ፣ ለነጻነቱ፣ ለክብሩ የሚያደርገዉን ትግል የሚያመላክት ንቅናቄ ነዉ። ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ያኔ እንዳለቸዉ ቅንጅት መንፈስ ነዉ።

ለዚህም ነዉ፣ እነ አቶ ኃይሉ ሻዉል የሕዝብን ሃላፊነት ሲጥሉ፣ እነ ዶር ብርሃኑ ነጋ ስደትን ሲመርጡ ፣ ገዢዉ ፓርቲ በሚቆጣጠረዉ ምርጫ ቦርድ የቅንጅትን ስም ለአያለ ጫሚሶ ቡድን ሲሰጥ፣ ያኔ በቅንጅት ስም ሲደረግ የነበረዉ የኢትዮጵያዊነትና የዲሞክራሲ ትግል፣ በአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ ሥር የቀጠለዉ። የሕዝብ የዲሞክራሲ ጥማት መቼም ሊሞት አይችልም። የሕዝብ የእኩልነት፣ የፍትህ፣ የመልካም አስተዳደር ጥያቄ መቼም ቢሆን ሊታፈን አይችልም። ቅንጅት ማለት ይሄ ነዉ።

ዶር ነጋሶ ጊዳዳ የቅንጅት ወራሽ የሆነዉን የአንድነት ፓርቲን ለመምራት ሲመረጡ፣ እርሳቸዉ የኢሕአዴግን ፖለቲካዎች አልፈልግም ብለው፣ አንድነት ወደ ሚያራምደዉ የ«ቅንጅት» ፖለቲካ በመምጣታቸው ነዉ። ዶር ነጋሶ የአንድነት መሪ ሲሆኑ፣ የአንድነት ፓርቲን (ማለት የቀድሞ የቅንጅት) መርህዎችና እሴቶችን በመቀበላቸዉ ነዉ። ለምሳሌ የአንድነት ፓርቲ ካስቀመጣቸዉ ራእዮቹ መካከል የተወሰኑትን ልጥቀስ ፡

• የአንድነት ፓርቲ አሁን ያለዉን በዘር ላይ የተመሰረተ ከፋፋይና ጎጂ የፌደራል አወቃቀር ይቃወማል። የድርጅቱን የፖለቲካ ፕሮግራምና ራእይ ባቀፈዉ ሰነድ በ4.1.3 .ሀ «የፌደራል አወቃቀሩ እንደ ሁኔታዉ መልከዓ-ምድራዊ አቀማመጥን፣ የሕዝብ አሰፋፈርን፣ አስተዳዳራዊና የልማት አመችነትን፣ ቋንቋን ባህልን፣ ታሪክንና ሌሎች ማህበራዊ ትሥሮችን መሰረት ያደረገ ይሆናል” የሚል እናነባለን። ፍጹም በዘር ላይ ብቻ ካታኮረዉ፣ ከፋፋይና ጎጂ ከሆነዉ ፣ አሁን ካለዉ ከሕወሃት ፌዴራል አወቃቀር የተለየ የፌደራል አወቃቅር ነዉ ።

• አንቀጽ 4.3 ሀ «ለመንግስት አገልግሎት የሚዉል ካልሆነ በቀር ማንኛዉም የገጠር መሬትና የከተማ ቦታ የኢትዮጵያዉያን የግል ሃብት ይሆናል” ሲል አንድነት ፓርቲ ኢሕአዴግ ከሚያራምደዉ መሬት የመንግስት ነዉ ከሚለዉ ፖለቲካ የተለየ ፖለቲካ ነዉ።

• ሕወሃት/ኢሕአዴግ ኤርትራን ያስገነጠለ፣ ኢትዮጵያን የባህር አልባ አድርጎ ለጅቡቲ ቱጃሮች አገራችንን ጥገኛና ባሪያ ያደረገ ነዉ። እስከአሁን ድረስ የሕወሃት/ኢሕአዴግ ፖሊሲ አሰብ የኢትዮጵያ እንዳልሆነች ነዉ። የአንድነት ፓርቲ በፕሮግራሙ ስለ ወደብ ሲያትት ኢትዮጵያ የወደብ ባለቤት መሆን እንዳለበት በግልጽ ያስቀምጣል። «ከኢትዮጵያ አብይ የዉጭ ጉዳዮች በቀዳሚነት የሚታየዉ የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄ ሰላማዊና ፍትሃዊ በሆነ መንገድ እንዲረጋገጥ ጽኑ ዲፕሎማሲያዊ ትግል ይደረጋል” ይላል አንቀጽ፡4.7.መ።

እንግዲህ ይህን አይነት ኢትዮጵያዊ የፖለቲካ አጀንዳ ይዞ የሚንቀሳቀስ ድርጅትን፣ ኢሕአዴግን እንደመሰለ አድርጎ አይጋ ፎረም ሲጽፍ ፣ መሳቂያ ከመሆን በስተቀር ብዙ የሚቀይረዉ አተሳሰብ ይኖራል ብዬ አላስብም።

«ቅንጅት» አልሞተም። የቅንጅት መንፈስ አልጠፋም። የኢትዮጵያ ሕዝብ መብቱንና ነጻነቱን፣ ክብሩንና አንድነቱን ለማረጋገጥ፣ የተሸከመዉን የግፍ አገዛዝና የመከራ ቀንበር ከአናቱ ላይ ለማራገፍ፣ ከመቼዉም በበለጠ የቆረጠበትና የተዘጋጀበት ጊዜ ነዉ።

ሕወሃት/ኢሕአዴግ ፣ ጦር ሃይሉን፣ የደህንነት ክፍሉን፣ ሜዲያዉንና ኢኮኖሚዉን በመቆጣጠሩ የገጸፈና ለዘላለም የሚኖር፣ በሌላ አባባል ያሸነፈ አድርገዉ እነ አይጋ ፎረም ሊጽፉ ይችላሉ። ነገር ግን ከጊዜ ወደ ጊዜ እያየን ያለነዉ የሕወሃት/ኢሕአዴግ የከሰረ የዘር ፖለቲካ ተቀባያነቱ እየወደቀ ሲሄድ፣ በቅንጅት ጎልቶ የወጣዉ የኢትዮጵያዊነት መንፈስ የበለጠ እያበበና ኢትዮጵያዉያን በዘር አንከፋፈልም ብለዉ በአንድነት ሲሰባባሱ ነዉ። በዜጎች ዘንድ ያለዉን የአስተሳሰብ ትግል፣ የዜጎችን ልብ የመማረክ ትግል ካየን፣ እያሽነፈ ያለዉ የኋላ ቀሩ የሕወሃት/ኢሕአዴግ የዘር ፖለቲካ ሳይሆን የ«ቅንጅት» የኢትዮያዊነት ፖለቲካ ነዉ !

«ቅንጅት» ሞቷል እያሉ፣ ሕዝብ ይዞት በተነሳዉ መሰረታዊ የዲሞክራሲና የአንድነቱ ጥያቄ ላይ ከማሾፍ፣ ልቦና ገዝቶ ከወዲሁ ለሕዝብ ጥያቄ ምላሽ በአስቸኳይ መስጠቱ ይበጃል።