ያለፈው ወር የመለስ የሹመት እስክስታ የማይሸፍነው የትግራይ ገዥ ጉጅሌ ፍጹማዊ ዘረኛ አማባገነናዊነትና ዘራፊነት
ያለፈው ወር የመለስ የሹመት እስክስታ የማይሸፍነው የትግራይ ገዥ ጉጅሌ ፍጹማዊ ዘረኛ አማባገነናዊነትና ዘራፊነት
ግንቦት 7 – የኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ ትንታኔ ህዳር 13 2003 ዓ.ም
ሰሞኑን መለስ ዜናዊ አዳዲስ ሚኒስትሮችንና አምባሳደሮችን መሾሙን ነግሮናል። በዚህ ጽሁፍ የምናተኩረው ሹመቱ ላይ አይደለም። ትኩረታችን በዚህ ሹመት አማካይነት ዘረኛው አምባገነን መለስ ዜናዊ ሊያስተላልፍልን በፈለገው መልእክት ላይ ነው።
መልእክቶቹ ግልጽ ናቸው። የተሾሙትን ግለሰቦች የዘር ጀርባ ተመልክተን “ሹመቱ ምንም አይነት የትግራይ ዘረኛነት የለበትም” እንድንል ነው።
መለስ ዜናዊና ዘረኛ ስርአቱን የሚደግፉ ጀሌዎቹ ሊነግሩን የሚፈልጉት “ትግራዋዩ ስዩም መስፍን ከውጭ ጉዳይ ተነስቶ በቦታው የደቡቡ ሃይለማሪያም ደሳለኝ መተካቱና በሌሎችም የሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች በርካታ የደቡብ ሰዎች መመደባቸው ስርአቱ ዘረኛ አለመሆኑን የሚያሳይ ነው” የሚል መልእክታቸውን ነው።
ወያኔዎች ይህን መልእክታቸውን ልብ እንድንል በየሚድያው ካቀረቡት የሰሞኑ የሚንስቴሮችና ቀጥሎም የአምባሳደሮች የሹመት የስም ዝርዝር ጋር ትኩረታችንን ለመሳብ በማሰብ አንድ የፕሮፓጋንዳ ነጥብ ሲያሰተጋቡ ነበር። በአገዘዙ ስር ባሉ ጋዜጦችና ድረ-ገጾች ላይ ከተሿሚዎች የስም ዝርዝር ጋር ሸጎጥ ተደርጋ የወጣች መሰሪ ፕሮፓጋንዳ እንደሚከተለው ትነበባለች።
“ከዚህ በላይ ስማቸው የተዘረዘሩትን ሚኒስቴሮች ወይም አምባሳደሮች ለመሾም የተወሰደው መመዘኛ ችሎታና ችሎታ ብቻ ነው” ትላለች።
የመልእክቱ አላማ ግልጽ ነው። ሰዎቹን ስንሾም ዘረኛነትን፣ በሌላ ቋንቋ ትግሬነትን፣ መስፈርት አላደረግንም ለማለት ነው። ወያኔ በዘረኛነቱ ከሃገሬው አልፎ በውጭ መንግስታትም እየታወቀ መምጣቱ ትንሽ ያሳሰበው ለመሆኑ ፍንጭ ነበሩና መልእክቱ ለሃገሬውም ብቻ ሳይሆን ለመጽዋቾቹ ፈረንጆችም ጭምር እንደሆነ ግልጽ ነው።
“የፖለቲካ ታማኝነትን መስፈርት አላደረግንም” የሚል መልእክት ለማስተላለፍ ተፈልጎ የተጻፈ ነው ብለን እንዳንተረጉመው ተሿሚዎቹ በሙሉ የጌቶቹ ፓርቲ – ህዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ – ጠፍጥፎ የሰራቸው፣ ሎሌ ድርጅቶች ታማኝ ካድሬዎች ናቸው። በስም ዝርዝሩ ውስጥ የመለስ መጋለቢያ ጌኛ ካድሬ ሳይሆን በችሎታው ብቻ የተሾመ ሰው የለም። በመሆኑም መልእክቱ ዘረኛነትና ሹመት የተለያዩ መሆናቸውን ለማሳመን የሚጥር እንደሆነ ግልጽ ነው።
እየተነገረን ያለው “ሰዎች የተሾሙት በፖለቲካ ታማኝነታቸው አይደለም” የሚለውን ቢክዱትም ሊካድ የማይችል ሃቅ ለመሸፈን አልነበረም:: መልእክቱ “ትግሬነትን ለከፍተኛ ሹመት የሚያበቃ መስፈርት ማድረግ አቁመናል” የሚል ነው። ይህ በራሱ መልእክቱን አስገራሚ ያደርገዋል። አንዱ የመልእክቱ አላማም፣ ዋንኛው ባይሆንም፣ “ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርን የሚያክል ቁልፍ መስሪያ ቤት ሳይቀር የትግራይ ተወላጅ ባልሆነ ሰው እንዲያዝ አድርገናል” ነው።
እኛ እዚህ ላይ ሃይለማሪያም ደሳለኝ ከደቡብ ይምጣ እንጅ በመንፈሱም ሆነ በድርጊቱ ከትግራይ ጌቶቹ የበለጠ ትግራዋይ ነው ማለት አያቅተንም። ይህ እንግዳ ነገር አይደለም። በሃገራችን ከጣልያንም በላይ ጣልያን የሆነ፣ “እኔ የሃያሉ አሽከር” በማለት በጣልያን ስም የሚምል ባንዳ ነበር። የኦሮሞን እና የአማራን ህዝብ፤ እንዲሁም የደቡብና ሌሎችንም ሀዝቦች ለዘመኑ የትግራይ ገዥዎች በባርነት እያስረገጡ ሆዳቸውን የሚሞሉ፤ በወያኔ ጌቶቻቸው ስም የሚምሉ በርካታ ከሃዲዎች ባሉበት ሃገር ደሳለኝ ደሙ ደቡብ ልቡ ትግራዋይ ነው ብንል ማጋነን አይሆንም። ይህን አባባል የሰነዘርነውም ያለ በቂ ማስረጃ አይደለም።
ከጥቂት ወራት በፊት የመተካካቱን ጉዳይ አንስተው መለስና በጣት የሚቆጠሩ ዘረኛ ሴረኞቹ በረከት ሰምኦንንና የደህንነቱን ሃላፊ ጌታቸው አሰፋን ጨምሮ ስብሰባ አድርገው ነበር። የመተካካቱ ጨዋታ የትግራዩን ገዢ ጉጅሌ የስልጣን የበላይነት በማይነካ መልኩ እንዲከናወን እነማንን መሾም እንደሚገባ ለመመካከር የተደረገ ስብሰባ እንደነበር የግንቦት 7 ንቅናቄ ከብአዴኖች አካባቢ መረጃ ደርሶት ነበር። ከደቡቡ ሃይለማሪያምና ከሌሎችም የሚኒስትርነትና የአምባሳደርነት ሹመት ጀርባ ያለው ሃቅ ይህ ነው። በወያኔ ምርጦች ስብሰባ ላይ የአንድ ሰው ስም ለሹመት እንዲታጭ ሲቀርብ መለስ ዜናዊና የቅርብ ባለደረቦቹ በተደጋጋሚ፦
“ሰውየው ጸረ-ትግሬ አለመሆኑን በደንብ ታውቃላችሁ ወይ?” የሚል ጥያቄ ያነሱ እንደነበርና የደህንነቱ ሃላፊ ጌታቸው አሰፋ በሚጠቆሙት ግለሰቦች ላይ ያለውን መረጃ እያቀረበ የተሿሚዎቹ ምርጫ እንደተከናወነ ሰምተናል። በረከት ስምኦን አንዱ እርሱ ለሹመት ያቀረበው የብአዴን አባል የሆነ የጎንደር ተወላጅ ጸረ ትግሬ ነው በሚል ፍረጃ ወያኔዎቹ ያልተቀበሉት በመሆኑ ቅር ተሰኝቶ፣ ስለስብሰባው ሂደት ለብአዴን ጓደኞቹ የተናገራቸው ቃላት መለስና በዙሪያው የሰበሰባቸው ዘረኛ የትግራይ ተወላጆች የገዛ ጥላቸውን ከማያምኑበት ደረጃ ላይ መድረሳቸውን የሚያመላክት ነው።
“ሰዎቹ ሳርና ቅጠሉ ሳይቀር ጸረ ትግሬ ይመስላቸው ጀምሯል” ነበር በረከት ሰምኦን ያለው:: እነመለስ አንድ ሰው ከመሾማቸው በፊት ጸረ-ትግሬ ላለመሆኑ መረጃ ስጡን ብለው ሲወተውቱ የከረሙት ተሿሚው ሰው በአይኑ አይቶት የማያውቀውን ደሃ የትግራይ ገበሬ ይጠላል ወይ የሚል ስጋት ስላደረባቸው እንዳልሆነ ግልጽ ነው። ጥያቄው ይሰነዘር የነበረው ሊሾም እየታጨ የነበረው ሰው፣ የትግራይ ገዢ ጉጀሌ በጁ ባግበሰበሰው የሃገር ሃብትና ስልጣን ላይ ቅሬታ ያደረበት፣ ስለ መለስና በዙሪያው ስላሰባሰባቸው ሰዎች ሲያስብ አይኑ የሚቀላ ነወይ ለማለት ነበር። እንግዲህ በዚህ መመዘኛ አልፈው የመጡ ሰዎችን ነበር “በችሎታቸው ከዘር መድሎ ውጭ መደብናቸው” የተባልነው።
ይህም አልበቃ ብሎ ለነሃይለማሪያም ደሳለኝ ሞግዚት እንዲሆን የዘረኛው ስርአት አገልጋይና የመለስ ዜናዊ የቅርብ ወዳጅ የሆነው ብርሃነ ገብረክርስቶስ በውጭ ጉዳይ ሚንስቴር መስሪያ ቤት ውስጥ በሚኒስቴር ዴኤታነት መመደቡ ተነግሮናል። ሚኒስትሩ ብርሃነ ወይስ ሃይለማሪያም ለሚለው ጥያቄ መልሱ ግልጽ ነው። ብርሃነ ነው ለስራ ጉዳይ ወደ ሚኒስቴር ደሳለኝ ቢሮ የሚሄደው ወይንስ ሚኒስትሩ ሃይለማሪያም ወደ ሚኒስቴር ዴኤታው ወደ ብርሃነ ቢሮ የበታቹን ሊያናግር ይሄዳል? የዚህም ጥያቄ ምላሽ ግልጽ ነው።
ከወያኔ አሰራር እንደምናውቀው የስልጣን የበላይነት የችሎታና የሹመት የበላይነት ውጤት ሳይሆን የዘር ትስስር ነው። ትንሿ የወያኔ ካድሬ ትልቁን የኦህዴድንና የብአዴንን ካድሬ ስታዝና ስታንቀጠቅ እንደኖረች እናውቃለን። አንድ የትግራይ ሃምሳ አለቃ አንድን ከትግራይ ዘር ያልመጣን ጄነራል እንደሚያሽቆጠቁጥ ግልጽ ነው። ሰለዚህ ዛሬ በየመስሪያ ቤቱና በኤምባሲው ከተመደቡት የሌላ ዘር ጭምብል ካጠለቁ ሰዎች ጀርባ በየሚስኒቴር መስሪያ ቤቱም ሆነ በየኤምባሲው ፈላጭ ቆራጮቹ ከመለስ ምርጥ ዘር የተመረጡ በተለያዩ ክፍሎች የተመደቡ በአደባባይ የሚንስተርና የአምባሳደርነት ሹመት ያልተሰጣቸው የትግራይ ሚኒስቴሮችና አምባሳደሮች ናቸው።
ስለሰሞኑ ሹመት ሌላም ሌላም ማለት ይቻላል።
መለስ ዜናዊ ለምን አብዛኛዎቹን ተሿሚዎች ከደቡብ አደረገ? ለምን የመለስ ውቃቢ ከበኩር ተለጣፊዎቹ፣ ከብአዴንና ከኦህዴድ ላይ ተነሳ? ለምንስ ወደ አዲሶቹ የደቡብና የሌሎች አናሳ ብሄረሰቦች ተለጣፊ ድርጅቶች ሄደ? የመለስን ዘረኛ የከፋፍለህ ግዛ ፖሊሲ በማንተራሰ ለነዚህ ጠያቄዎች በቂ ምላሽ መስጠት ይቻላል። ይሁንና ከሰሞኑ ሹመት ጋር የተያያዘው ቁም ነገር ይህ ሰላልሆነ እንዘለዋለን። ዋናው የሹመቱ ቁም ነገር መለስና በስልጣንና በነዋይ ሱስ የደነዘዙ ዘረኛ ማህበርተኞቹ የኢትዮጵያን ህዝብ አይንህን ጨፍንና እናሞኝህ የሚል የንቀት መልእክት ያስተላለፉበት መሆኑ ነው።
የሰሞኑ የወያኔ ሹመት ሰዎችን በችሎታቸው ነው የመደብነው የሚል መግለጫ ተለጥፎበት የወጣው ስለአዲሶቹ ተሿሚዎች ተብሎ አይደለም። የነባር ተሿሚዎችንና አዳዲስ የትግራይ ተወላጆችን ሹመት ለማሳመር ነው።
ቅድም እንደገለጽነው ዘረኛው መለስ “ሰዎቹን በሃላፊነት ላይ ያስቀመጥኩት በችሎታቸው ነው” እያለን ነው። ይህ ማለት “መከላከያው፣ ደህንነቱ፣ ቁልፍ የሆኑ የኢኮኖሚ አውታሮች በትግራይ ተወላጆች እጅ ተይዘው እንዲቀጥሉ የምናደረገው እነዚህ ሰዎች በዘራቸው ትግራዋይ ስለሆኑ ሳይሆን በችሎታቸው የላቁ ስለሆኑ ነው” ለማለት ነው።
በጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሮ ውሰጥ ቁልፍ በሆኑ የኢኮኖሚ፣ የማህበራዊና የደህነነት ጉዳዮች ላይ ዘረኛውን መለስ ዜናዊን የሚያማክሩት በሙሉ የትግራይ ተወላጆች ናቸው። በመሆናቸውም የሃገሪቱ የፌደራል ቋንቋ የሆነውን አማርኛ ቋንቋ ሳይጠቀሙ በሃገር ጉዳይ ላይ መክረው ውሳኔ መስጠት ይችላሉ። በመሃላቸው ትግርኛ የማይናገር ሰው የለምና። ይህ የሚያሳየው ወሳኝ የሆነው የሀገሪቱ ስልጣን እንዴት ዘረኛ በሆነ መንገድ የተሰባሰበ መሆኑን ነው። በመከላከያ ሚኒስቴር ውስጥ የመከላከያ ሰራዊቱ አዛዥ ሳሞራ የኑስና የሰራዊቱን ከፍተኛ ስልጣን የያዙት 7 ከፍተኛ የጄነራልነት ማእረግ ያላቸው ባልደረቦቹ የሚያደርጉት ስብሰባ የሀገሪቱን ፌደራል ቋንቋ መጠቀም አያስፈልገውም። ወያኔ ስልጣን ላይ ከወጣ ከሃያ አመት በኋላም በትግርኛ ብቻ ተነጋግረው የሚያበቃበት ሁኔታ ዛሬም እነደቀጠለ ነው። እንዲሁ በተመሳሳይ ከአርባ በላይ የሚሆኑ የሀገሪቱ ከፍተኛ ጀነራሎች በሃገር መከላከያ ጉዳይ ላይ ውይይት ለማድረግ የሀገሪቱን የስራ ቋንቋ አማርኛን መጠቀም አያስፈልጋቸውም። ጉዳያቸውን በትግርኛ ጀምረው በትግርኛ መጨረስ የሚችሉበት ሁኔታ የሚያሳየው ዘረኛነት የሰራዊቱ የከፍተኛ ስልጣን መያዢያ መስፈረት ሆኖ መቀጠሉን ነው። በደህንነት ጉዳይም መስሪያ ቤቱን በሙሉ እንዳሻቸው ከሚያዙት የትግራይ ተወላጆች በተጨማሪ አዲሱን የጠቅላይ ሚኒስትሩን የደህንነት ጉዳይ አማካሪ፣ የቀደሞውን የትግራይ ክልል ፐሬዚደነት አለቃ ጸጋዬን ጨምሮ በሙሉ የተያዘው በትግራይ ተወላጆች ነው።
ከዚህም በተጨማሪ የወያኔ ዘረኞች ከፍተኛ ጥቅም የሚገኝባቸውን ማናቸውም ሃብት የሚያፈሩ ተቋማት ውስጥ ቁልፍ የሆኑ ቦታዎች እንደያዙና ዘረኛ በሆነ መንገድ በመጠቃቀም ከፍተኛ ሃብት እየዘረፉ ያለበት እውነታ አልተቀየረም። ይህ አልበቃ ብሎ በሚቀጥሉት አመታት ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ያስገኛሉ ተብሎ የታሰቡትን የመብራት ሃይልና የስኳር ኮርፖሬሽን መስሪያ ቤቶች በቀንደኛው ዘረኛ በመለስ ዜናዊ እጅ ተጠቃለው እንዲገቡ መወሰኑ ከአዲሱ ሹመት ጋር የቀረበ ዜና ነበር። ይህ የሚፈጸመው በአገዛዝ ስርአቱ ውስጥ የትግራይ ምርጦች የያዙትን የኢኮኖሚ የበላይነት ለማስረገጥ ሆን ተብሎ እንደሆነ መታወቅ ይኖርበታል።
መለስ ዜናዊ አባይ ጸሃዬን ከሚኒስትርነት አንስቶ የስኳረ ኮርፖሬሽን ሃላፊ ሲያደርገው አባይን እያዋረደ ሳይሆን ራሱን ጠቅሞ አባይ ጸሃየንም ለመጥቀም ነው። የዘረኞቹን የበላይነት እያስጠበቀ ነው። ስኳር በሚቀጥሉት ጥቂት አመታት እስከ 500 ሚሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሪ የሚያስገኝ የንግድ ዘርፍ እንደሚሆን በሚተነበይበት ወቅት የትግራይ ተወላጅ ያልሆነን ሰው በዛ ቦታ ላይ መመደብ ለመለስ ዜናዊና ለዘረኛ አጋሮቹ የማይታሰብ ነው። የውጭ ጉዳይና የተቀሩትንም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች በሙሉ ለደቡቦች አስረክቦ መለስ ዜናዊ የጦር ሃይሉን፣ ደህንነቱንና ወሳኝ የሆኑትን የሃገሪቱን የሃብት ምንጭ ተቋማት በዘር ልጅነታቸው በመለመላቸው የትግራይ ተወላጆች ይዞ እስከቀጠለ ድረስ የዘረኛው የትግራይ ገዥ ጉጅሌ የፈላጭ ቆራጭነትና የዘራፊነት ጀንበር እንደማይጠልቅ ያውቃል።
መለስ ዜናዊና የትግራዩ ገዢ ጉጅሌ በተጠናወታቸው የህዝብ ንቀት በሽታ የተነሳ ያልገባቸው የኢትዮጵያ ህዝብ ጉልበትና ሃብት የስልጣን ምንጭ እንደሆነ ጠንቅቆ የሚያውቅ መሆኑን ነው። ዛሬም መለስ ዜናዊ በሃገሪቱ ውስጥ ያለውን ወሳኝ የሃብት ምንጭ ከትግራይ ዘር ባሰባሰባቸው ምርጦች እጅ እንደተቆጣጠረ ነው። መለስ ዜናዊ ህዝብን ሲሻው ሊያሳድድ፣ ሊያስርና ሊገድል የሚችል ሰራዊቱንና ደህንነቱን በሙሉ በዘር ባደራጃቸው የትግራይ ተወላጆች እጅ እንዳስያዘ ነው። ይህን ሰራዊት መለስ “ጃስ” ቢለው በአንድ ቀን ማታ ሃይለማሪያም ደሳለኝንና የተለጣፊ ድርጅቶችን መሪዎች ቁርጥምጥም አድርጓቸው እንደሚያድር ይታወቃል።
እንዳውም የቅርብ ጊዜው ሹመት የሚያሳየው የዘረኛነትን መላላት ሳይሆን በተቃራኒው መለስ ዜናዊ ሃብትንና ጉልበትን የበለጠ በትግራይ ተወላጅነታቸው በተመረጡ ባለሟሎቹ እያስያዘ እንደሆነ ነው። መለስ ዜናዊ በትራንስፎርሜሽንና በመተካካት ፖለቲካ ስም ሽህ ግዜ ሲያስካካ፣ ሽህ ሃይለማሪያም ደሳለኞችን ለላንቲካ ቢደረድር የስርአቱ ዘረኛነት ከግለሰቦች መቀያየር ተሻግሮ ተቋማዊ ሆኗልና የሚቀየር ነገር አይኖርም:: “የዘረኛነት ዛር ከመለስ ዜናዊና ከሚመራው ጉጅሌ ይወጣል” ማለት “ወሃ ሽቅብ ሊፈስ ይችላል” ከሚል ከንቱ አባባል ልዩነት አይኖረውም። ዘረኛነት የሚያከትመው በወያኔ መቃብር ላይ ብቻ እንደሆነ ሃገሬው ከተረዳው ሰነበተ። የሰሞኑ ሹመት “ከሃፍረተ- ቢስ የዘረኞች ብልጣብልጥነት የተለየ ትርጉም የለውም” የምነለው ለዚህ ነው።