መለስ ዜናዊ በግብጽ ላይ ያስተላለፈው ማስጠንቀቂያ እራሱን እንደ አገር-ወዳድ ዜጋ ለመቅረጽ የሚያደርገው ሙከራ አካል ነው ተባለ
ዘረኛው አምባገነን መለስ ዜናዊ ግብጽ ከኢትዮጵያ ጋር ጦርነት ባታስብ ይሻላታል ሲል በብዙዎች ዘንድ አነጋጋሪ የሆነ ማስጠንቅቂያ መስጠቱ እራሱን እንደ አገር-ወዳድ ኢትዮጵያዊ ለማስቆጠር ከሚያደርጋቸው ሙከራዎች ውስጥ አንዱ ነው ተብሏል።
ዘረኛው አምባገነን ማክሰኞ እለት ለሬውተርስ የዜና አውታር በሰጠው ቃለ መጠይቅ፥ “ኢትዮጵያን ለመውረር የሞከረ ማንኛውም ሃይል ከሞት ተርፎ ታሪኩን ለመናገር ደርሶ አያውቅም። ግብጾችም ከዛ የተለዩ ሊሆኑ አይችሉም፤ ያንንም የሚያውቁ ይመስለኛል፤” ሲል ደስኩሯል። ግብጽ በበኩሏ ይህ የመለስ ንግግር አስገራሚ እና ያልተጠበቀ እንደሆነ በመግለጽ፤ ጦርነት ውስጥ የመግባት ፍላጎት እንደሌላት ገልጻለች።
መለስ ዜናዊ በአንድ በኩል ከግብጽ የኢኮኖሚ እርዳታ እየጠየቀ አብሬሽ ቆማለሁ እንደሚል እና በሌላ ጎን ደግሞ ከተቀሩት የአባይ ተፋሰስ አገራት ጋር ሆኖ ግብጽን በማስፈራራት ሁለቱን ጎን ሲጫወት መቆየቱ ይታወቃል። በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ኢትዮጵያ ውስጥ ድጋፍ ለማግኘት ሲል “የውጭ ጠላት” ዘፈኑን አጠናክሮታል።
የዝግጅት ክፍላችንን ያናገሩ አንድ የፖለቲካ ተንታኝ፤ መለስ ዜናዊ ለግብጽ የሰጠው ማስጠንቀቂያ፣ እራሱን እንደ ኩሩ እና አገር ወዳድ ዜጋ በመቅረጽ፤ ለኢትዮጵያ ያለውን ስር የሰደደ ጥላቻ ለመደበቅ እና ድጋፍ ለማግኘት የሚያደርገው ሙከራ ነው ብለዋል።