በክፍላተ ሃገራት ኮንዶሚኒየሞች ገዢ አጥተው የከብቶች ማደሪያ እየሆኑ ነው

የወያኔ አገዛዝ ያለ በቂ ጥናት በተለያዩ ከተሞች ያስገነባቸው ኮንዶሚኒየሞች ዋጋ ማጣታቸውን ከአዲስ አበባ የደረሰን ዘገባ አመልክቷል።

የግንቦት 7 ዘጋቢ አጠናቅሮ በላከልን መረጃ መሰረት፥ በፍቼ፣ በአምቦ፣ በወላይታ ሶዶ እና ሌሎች ከተሞች ተገቢው ቅድመ ጥናት ሳይካሄድ ከ1998 አመተ ምህረት ጀምሮ የተገነቡት ኮንዶሚኒየሞች የአህዮች እና የከብቶች ማደሪያ ሆነዋል። ቤቶቹን እንዲገዙ የተጠየቁት የአካባቢው ሰዎች፣ ዋጋቸው ከጥራት ደረጃቸው ጋር ሲነጻጸር እጅግ ውድ በመሆኑ እና በርካሽ ዋጋ የተሻሉ ቤቶችን ለማግኘት ስለሚችሉ ፈቃደኛ አለመሆናቸው ታውቋል።

ዘረኛው አገዛዝ በጠንካራ መሰረት ላይ ያልቆመ የ”እድገት” ፕሮፓጋንዳውን ለመግፋት እና ለባለስልጣናቱ የዘረፋ እድልን ለመፍጠር ሲል የህዝብን ንብረት በግዴለሽነት ሲያፈስ መቆየቱ ይታወቃል። ባለፉት ጥቂት አመታት በአገሪቱ ዙሪያ በተካሄዱ ግንባታዎች ላይ ከበርካታ ወራት በፊት አሰሳ ያካሄዱ ባለሙያ አብዛኛው ግንባታ በችኮላ የተሰራ እና ከጥቂት አመታት በኋላ ከጥቅም ውጪ እንደሚሆን ድምዳሜ ላይ መድረሳቸውን የዝግጅት ክፍላን ምንጭ ገልጸዋል።