የወያኔ አገዛዝ የሃይማኖት ተቋማትን ማራከሱን ቀጥሏል፤ ቄሶች ለስለላ ስራ መመደብ ጀምረዋል

ዘረኛውና አምባገነናዊው የወያኔ አገዛዝ፣ ቤተ እምነቶችን የማርከስ ስራውን ቀጥሎ፣ ቄሶችን ለስለላ ስራ ማሰማራት መጀመሩን የግንቦት 7 ድምጽ ዘጋቢ ከአዲስ አበባ ባስተላለፈው መረጃ አሳውቋል።

ወያኔ ስልጣን እንደተቆጣጠረ፥ “የአብዮታዊ ዴሞክራሲያችን ግቦች እና ቀጣዩ እርምጃ” በሚል ርእስ ባወጣው የውስጥ ጽሁፍ ላይ፣ አብዮታዊ ዴሞክራሲን ለማንሰራፋት ቀስ በቀስ በቁጥጥር ስር ሊውሉ ከሚገባቸው ተቋማት ውስጥ ቤተ እምነቶችን ማስቀመጡ ይታወቃል። በዚህም አኳኋን፥ በተለይ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያንን አመራር በራሱ ሰዎች እጅ አስገብቶ ሲንቀሳቀስ ከመቆየቱ በተጨማሪ፤ ባለፉት አምስት አመታት በቤተእምነቶች እና በሃይማኖት መሪዎች ላይ የሚያደርገውን ጫና እና ጣልቃ ገብነት እያጠናከረ ሄዷል።

የግንቦት 7 ድምጽ ሪፖርተር ከአዲስ አበባ ምንጮችን ጠቅሶ በላከው ዘገባ፥ አገዛዙ ሊገባባቸው ወዳልቻለው ማህበረሰባት ቄሶችን ለስለላ መላክ እንደጀመረ ገልጿል። ይህ ከተፈጸመባቸው አካባቢዎች ዘጋቢያችንን ያናገሩ ዜጎች፥ በሚኖሩበት አካባቢ ያለው ህብረተሰብ እስካሁን እነዚህን ግለሰቦች ለይቶ አውቆ ለመጠንቀቅ እንደቻለ አስረድተው፤ በተቀረው የአገሪቱ ክፍል ያለው ህዝብ ግን ይህንን የአገዛዙን እኩይ ተግባር አስቀድሞ ሊገነዘብ እና ሊጠነቀቅ ይገባል ብለዋል።