ኒው ዮርክ ታይምስ ከዘገባዬ ጎን እቆማለሁ አለ

ታዋቂው የአሜሪካ ጋዜጣ ኒው ዮርክ ታይምስ ሃይሌ ገብረስላሴ ከወያኔ አገዛዝ ጫና እየደረሰበት ነው በሚል የሯጩን ማኔጀር ጠቅሶ ያወጣውን ዘገባ አላጥፍም ማለቱ ተዘገበ።

“ሌትስ ራን ዳት ካም” የተባለ የእስፖርት ዜና ድረ-ገጽ፣ ሃይሌ ገብረስላሴ እና ማኔጀሩ ጆስ ሄርመንስ በወያኔ ቁጥጥር ስር በሚገኘው የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን – ኢቲቪ – ላይ ቀርበው የጋዜጣውን ዘገባ መካዳቸውን በማመልከት ለጋዜጣው ጥያቄ መላኩን ዘግቧል። ድረ-ገጹ ቀደም ብሎ ባወጣው ዜናም፣ ጋዜጣው የሃይሌ ማኔጀር ከነገረው ነገር ውጪ አለመዘገቡን እንዳረጋገጠ ገልጿል።

ኒው ዮርክ ታይምስም ባወጣው ዘገባ፥ ዝነኛው አትሌት ሃይሌ ገብረስላሴ ከዘረኛው እና አምባገነናዊው የወያኔ አገዛዝ በሚደረግበት ከፍተኛ የፖለቲካ ጫና ስር እንደሚገኝ ማጋለጡ ይታወሳል። የሯጩ ስልክ እንደተጠለፈ እና ማስፈራሪያ እየተደረገበት እንዳለ ሆላንዳዊ ማኔጀሩን ጆስ ሄርመንስን በመጥቀስ የገለጸው ዘገባ፤ አትሌቱ ጡረታ ስለመውጣቱ በድንገት ያደረገው አዋጅ ጫናው ከፈጠረበት የስሜት መረበሽ የመጣ ሳይሆን እንደማይቀር አትቷል።

በርካታ የፖለቲካ ተንታኞች፥ ሃይሌ እና ጆስ ሄርመንስ የኒው ዮርክ ታይምንስን ዘገባ እንዲክዱ በወያኔ አገዛዝ ጫና ሳይደረግባቸው እንዳልቀረ ግምታቸውን እየገለጹ ነው።