ልጅትና እንጀራ በታምራት ከድንጋያማ ተራሮች ግዛት

ልጅት
ሸሞንሟኒት
ከማጀቷ ወጥታ ጎተራዋን ከፍታ
ጥቂት የጤፍ ነዶ ተሸክማ መጥታ
ከእስራቱ ፈትታ ዛላውን ዘርግታ
በልቅልቅ ወለል ላይ አጋድማ አስተኝታ

በእግሮችዋ ከርብታ በዱላ ነርታ
በድምፅ አስፈራርታ

ወደ ላይ አጉና
ትቢያውን አቡንና

ለንፋሱ ሰጥታ ገለባውን ከልታ
እብቁን አንስታ በወንፊቷ ነፍታ
ፍሬውን ለይታ

ደግሞም ዝቅ ብላ ነጠላዋን ጥላ
አንጥሳና ስላ
የባጀችበትን ጤፍዋን በጀርባ አዝላ

ማጀት ተመለሰች
ወፍጮዋን አበስች

ውቢት
ሸሞንሟኒት ያቺ የኔ ቅንድባም
ያች የሴቶች አውራ ያች ጎራዳ ” ልባም ”

በእንብርክኴ ሆና ጤፉን በእጇ ዘግና
ወፍጮው ላይ በትና

መጅ ከእናት አጋጭታ በዜማዋ አግባብታ
ያንን የጤፍ ፍሬ አንጀቱን አውጥታ

ከትክታ ጨፍልቃ ደቁሳ ደቌቁሳ
ዘር የመሆን መብቱን ነፃነቱን ድሳ

ፍንክቱን አንጓላ ሽርክቱን አቂላ
ለሌላ ዙር ድቀት ስሌት ስታሰላ

ብናኙን አባብላ
በዜማዋ አታላ
ዱቄቱን ደባብሳ
በውሃ ለውሳ

ሲቀጥን አዋዝታ ሲወፍር አምታታ
ለቀናት ዘግታበት ለቀናት አግታ

የቀን ብርሃን አጥቶ ከውሃ ተጋጭቶ
በውሃ ተጣብቆ በውሃ ተጣልቶ
ማንነቱን ሽሮ እሱነቱን ትቶ
ተመርሮ ተከፍቶ አቅርሮ አንብቶ
መከራውን አይቶ
ነጻነቱን ሲመኝ ከቡሃቃው ወጥቶ
ሊጥነቱን ረስቶ

ልጅት
ሸሞን ሟኒት መች የዋዛ ሆና
ጊዜዋን መጥና

ጊዜዋን አስልታ ምድጃዋን ገፍታ
እንጨቱን ነካክታ እሳቱን አስብታ
ምጣድዋን አስምታ ቡኮዋን አስፍታ
አክንባሎ ደፍታ

እንጀራ አ(ደ)ረገችው ዋትታ በስሌት
የሰው መምመዘኛው እሱ ነው ቢሏት

‘እንጀራ አይደለም ወይ ለሰው ቁም ነገሩ
አላስቀምጥ ያለው ሰውን በየአገሩ’

የሚል ብሂል ሰምታ
ውቢት ሸሞንሟኒት አስልታ ገምታ

ጊዜዋን አጥፍታ ጊዜዋን ሰውታ
ምድጃዋን ገርታ እንጨቱን ነካክታ
እሳቱን አስብታ ምጣዱን አስምታ
ቡኮዋን አስፍታ አክንባሎ ደፍታ

እንጀራ ጋገረች ተጨንቃ በውል
ሰው በእንጀራ ብቻ ይኖር ይመስል

ታምራት
ከድንጋያማ ተራሮች ግዛት
November 10 -2010 ( ህዳር 2003 ዓ ም )