አምባሳደር ግርማ ብሩ በአትላንታ – ግርማ ካሳ

([email protected])

«የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፑብሊክ የዲያስፖራ ረቂቅ ፖሊሲ» በሚል ርእስ፣ በኅዳር ወር 2004 ዓ.ም ፣ በኢትዮጵያ የዉጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት የተዘጋጀ 24 ገጾችን የያዘ አንድ ሰነድ አነበብኩኝ።

«የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ከትዉልድ ሀገሩ ጋር ያለዉን ትሥሥር በማጠናከር በአገሩ ልማት ሰላምና ዲሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ጠንካራ ተሳታፊ ሆኖ፣ ራሱን ጠቅሞ ትዉልድ አገሩንም በመጥቀም፣ በጋራ ለማደግ የሚያስችል አመቺ ሁኔታ መፍጠርና በዉጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዉያንን መብትና ጥቅም ማስከበር» የሚለዉ የዚህ የዲያስፖራ ፖሊሲ አጠቃላይ ዓላማ እንደሆነ ሰነዱ ይገልጻል።

በዚህ ሰነድ የተተነተኑት በርካታ ጉዳዮች በጣም ጠቃሚ የሆኑ ጉዳዮች ናቸው ብዬ አምናለሁ። በዳያስፖራ የሚኖሩ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ትዉልደ ኢትዮጵያዊያን፣ በርግጥ በአገራቸዉ ጉዳይ ላይ በንቃት የሚሳተፉበትን ሁኔታ ለማመቻቸት መነሳት፣ በመርህ ደረጃ ሊደገፍ የሚገባዉ ነዉ።

አንዱ ዳያስፖራዉ ሊደግፈው የሚገባ ጉዳይ የአባይ ግንባታ ጉዳይ ነዉ። የአባይን ግድብ ለመገንባት በሚል፣ ላለፉት በርካታ ወራት፣ የኢሕአዴግ ባለስልጣናት የተለያዩ ስብሰባዎችን እያደረጉ እንደሆነ ሰምተናል። ከዚህ ከተማ ይሄን ያህል ገንዘብ ተሰበሰ፣ ይሄን ያህል ተዋጣ ይባላል።

በሌላ በኩል ደግሞ ስብሰባዎችን የሚቃወሙ፣ ሰብሰባዎችን ለመሳተፍ የመጡ እንዳይገቡ ሲከለከሉም በስፋት እያየን ነዉ። በዳያስፖራዉና በአገዛዙ መካከል መቀራረብ ሳይሆን ግጭቶች በተለይም በርካታ ኢትዮጵያውያን ባሉበት ከተሞች እየተመለከትን ነዉ። ምንድን ነዉ ችግሩ ?

እንደ አንድ ትዉልደ ኢትዮጵያዊ አባይ እንዲገነባ ትልቅ ፍላጎት አለኝ። በአገሬ ኢንቨስት ማድረግ እፈልጋለሁ። አገሬን መርዳት እፈልጋለሁ። አገሬን እወዳለሁ።

ነገር ግን እንደ እኔ አይነት አስተሳሰብ ያላቸዉ ወገኖች « እናንተ ኢትዮጵያዊያን አይደላችሁም ! የእናንተን እርዳታ ኢትዮጵያ አትፈልግም ! አናንተ የኢትዮጵያ መንግስትን የሚወክለዉ ፣ የኢትዮጵያ ኤምባሲ በሚጠራዉ ስብሰባ መካፈል አትችሉም» ከተባልን እንዴት ሆኖ ነዉ ታዲያ ከዳያስፖራዉ ጋር መቀራረብ የሚቻለዉ ?

በአትላንታ በቅርቡ በኢትዮጵያ ኤምባሲ የተጠራ ስብሰባ ተደረጎ ነበር። እንደነ ዳንኪረኛ ሰለሞን ተካለኝ የመሳሰሉ ሰዎች በአዳራሹ ሲወጡ ሲገቡ፣ በርካታ በእድሜ ባለጠጋ የሆኑ፣ አንቱ የሚባሉ፣ የተከበሩ አባቶች፣ ወረቀት አልያዝችሁም ተብለዉ እንዳይገቡ ሲከለከለሉ፣ ሲብጠለጠሉ ታዝቢያለሁ። ኢትዮጵያዉያንን ላነጋገር ብለዉ አምባሳደር ግርማ ብሩ በኢትዮጵያ ህዝብ ገንዘብ አትላንታ ድረስ መጥተዉ፣ ኢትዮጵያዉያን አትገቡም ተብለዉ ሲከለከሉ ማየት በርግጥ ዉስጥን የሚያደማ ነዉ። እነርሱ ኢትዮጵያዊ እኛ ባእዳን !

በአገር ቤት ንብረቶችና ቢስዘን ያላቸው ስማቸዉን እንዲያስመዘግቡና አሻራ እንዲሰጡ ከዚህ በፊት ታዘዉ እንደነበረ የሚታወስ ነዉ። እነዚህ ሰዎች ፈለጉም አልፈለጉም በጥቅም ስለተያዙ፣ ገዢዉን ፓርቲ የመንቀፍ ሙሉ ነጻናት አይሰማቸዉም። በተቃዋሚ ሰልፎች፣ በተለያዩ ተቃዋሚዉ በሚያዘጋጃቸው ስብሰባዎች መገኘት አይችሉም። ለምን ? ስማቸዉ ስለተመዘገበ፣ ማን እንደሆኑ ስለሚታወቅ ፣ ቤታቸዉ እንዳይወሰድባቸው፣ ቢዝነሳቸዉ እንዳይዘጋባቸዉ ይፈራሉ። እንደነዚህ አይነት ሰዎችን ብቻ ነዉ በራሱ የማይተማመነዉ ገዢዉ ፓርቲ ለስብሰባ የሚጠራዉ።

ኢትዮጵያ ዉስጥ ሕግ የበላይ አይደለም። ኢትዮጵያ ዉስጥ ሕግ ማለት አቶ መለስ ዜናዊ ማለት ነዉ። በማናቸዉም ጊዜ፣ በፈለጉት ሁኔታ ፣ አቶ መለስ ወይም ባለቤታቸዉ ቀዳማዊ እመቤት አዜብ፣ በመንገድ ሲያልፉ የተመለከቱት ቢዝነስ ካለ በአንድ ቃል ትእዛዝ ማዘጋት ይችላሉ።

ኢትዮጵያ ዉስጥ ቤት የሰሩ፣ ቤት የሚሰሩ፣ ቢዝነስ ያላቸዉ ፣ ከትንሹ እስከ ትልቁ ከአቶ መለስ ፍቃድ ዉጭ ምን ሊያደርጉ አይችሉም። «እረ እኔ ምን አገባኝ .ደግም አንድ ነገር ያድርጉኝ እንዴ !» ብለዉ ክፈሉ የተባሉትን እየከፈሉ፣ ኑ ሲባሉ እየመጡ፣ አንገታቸዉ ደፍተዉ፣ እያጎበደዱ የሚኖሩ ናቸዉ። አንዳንዶች በዚህ ጉዳይ ላይ ሊከራከሩኝ ይችላሉ። ነገር ግን እዉነታዉ ይሄ ነዉ።

አንድ መዘንጋት የሌለብን ነገር ቢኖር ፣ እነዚህ ሰዎች በመጀመሪያ ደረጃ በቁጥር ጥቂቶች ናቸዉ። በሁለተኛ ደረጃ ገንዘብ አዋጡ እየተባሉ ግፊት የበለጠ በተደረገባቸዉ ቁጥር፣ ተማረዉ፣ በአገር ቤት ያላቸዉን ንብረት ሽጠዉና ቢዝነሳቸዉ ዘግተዉ ሊያርፉት ይችላሉ። እኔ በምኖርበት ከተማ፣ ከምሬት የተነሳ አገሬን ልጥቀም በሚል የከፈቱትን ቢስነዞቻቸዉን ዘግተዉ ከኢትዮጵጵያ የመጡ ኢትዮጵያዉያንን አውቃለሁ።

ስለዚህ እንደዚህ አይነት ሰዎችን አሰባስቦ ዳያስፖራዉን አቀፍን ብሎ መናገር ትንሽ የሚያስኬድ አይመስለንም። እራሳቸዉን ባያታልሉ ይሻላቸዋል።

ይልቅስ ከላይ በጠቀስኩት ሰነድ ላይ ያሉ መሰረታዊና ጠቃሚ ነጥቦች ተግባራዊ እንዲሆኑ ከተፈለገ መሰረታዊ እርምጃዎችን ኢሕአዴግ መዉሰድ ይኖርበታል።

በርግጥ ኢሕአዴግ እራሱን መርምሮ ተገቢዉን እርምጃ ከወሰደ፣ በሰነዱ የዘረጋቸዉን ነጥቦች ያለ ምንም ችግር መፈጸም ይችላል። ሰነዱ ላይ ሰዎች ችግር ይኖራቸዋል ብዬ በጭራሽ አላምንም። አገሩን መርዳት የማይፈልግ ኢትዮጵያዊ የለም። አባይ እንዳይገነባ የማይፈልግ የለም። በአገራችን ኢንቨስት ማድረግ እንፈልጋለን። ነገር ግን ኢንቨስትመንታችንን ሕግ ወጥ ከሆነ ድርጊት የሚንከባከብ፣ የሕግ ከለላ ያስፈልገናል። በአጭሩ አባባል የሕግ የበላይነት መኖር አለበት።ሕግ ከአቶ መለስ፣ ከኢሕአዴግ በላይ መሆን አለበት። የፍትህ ስራዓቱ በአስተማማኝ ሁኔታ ገለልተኛ መሆን አለበት። ይሄ አንዱ ነጥብ ነዉ።

በአገራችን ጉዳይ ላይ አብረን እንድንሰራ ከተፈለገ፣ ሌላ የሚያስፈልገዉ ክብራችንን ስብእናችንንና ነጻነታችንን የመጠበቁ ሁኔታ ነዉ። ይህም የሚረጋገጠዉ በአገራችን የሚኖረዉ ወገናችን መብቱ፣ ክብሩ፣ ስብእናዉ ሲጠበቅለት ነዉ። በአገራችን ያሉ ወገኖቻች በግፍ እየታሰሩ፣ በፍርሃትና በሰቀቀን እየኖሩ፣ የአንድ ድርጅት አባላት ወይንም ከአንድ ጎሳ የመጡ ባላመሆናቸዉ አንገታቸዉን እየደፉ ባሉበት ሁኔታ፣ እንዴት አድርገን ነዉ፣ ሕሊናችን ፈቅዶልን አብረን ልንሰራ የምንችለዉ ? ጥቅም የገዛዉ፣ ሕሊና የሌለዉ ሊያደረገዉ ይችላል ፤ አብዛኛዉ በዉጭ አገር የሚኖረዉ አገሩን የሚወድ ኢትዮጵያዊ ግን አያደርገዉ።

ኢሕአዴግ በርግጥ ዳያስፖራዉ ለአገሩ ትልቅ አስተዋጾ ያመጣል ብሎ ካሰበ፣ በርግጥ ከዳያስፖራዉ ጋር ታርቆ ዳያስፖራዉን ማሳተፍ ከፈለገ በመጀመሪያ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር ይታረቅ እላለሁ። በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ የዘረጋዉ የፍርሃትና የሰቆቃን ቀንበር ማንሳት አለበት። ህዝቡን ማሸበሩን ማቆም አለበት።

ስለልማት ቢያወራ፣ ስለግንባታዎች ቢያወራ፣ ብሄራዊ እርቅ፣ መግባባት፣ ሰላም በሌለበት ሁኔታ የትም መድረስ አይቻልም። ዛሬ የአባይ ግድብ ቢገነባ ነገ እኮ በጥቂት ዲማሚቶች ድምጥ ማጡ ሊጠፋ ይችላል። ዋናውና ለሁሉ ነገር መሰረት የሆነዉ ግንባታና ሥራ፣ ኢትጵያዉያንን የማቀራረብና የማያያዝ ሥራ ነዉ። እኛ እንደ ወንድማማቾች ስንተያይና ስንከባበር ነዉ፣ የአባይ ግድብ ብቻ ሳይሆን ሌላም ሌላም መገንባት የምንችለዉ።

ብዙዎች በአቶ መለስና በኢሕአዴግ፣ ተስፋ ቆርጠዉ፣ እነርሱ ካልጠፉ በቀር መፍትሄ የለም የሚል ጠንካራ አቋም ወስደዋል። በዚህ አቋማቸዉ የት እንደሚደርሱ ባላወቅም፣ ወደዚህ አቋም ያደረሳቸዉ ገዢው ፓርቲ እራሱ እንደሆነ ግን አወቃለሁ።

የሰዉ ልጅ ድንጋይ አይደለም። አይምሮ አለዉ። ዛሬ ያላየዉን ነገ ሊያይ ይችላል። ሊለወጥ ይችላል። ከስህተቱ ሊታረም ይችላል። በዚህም ምክንያት ነዉ ተስፋ የማልቆርጠዉ። የሰላም ድምጼን በማሰማት አራት ኪሎ ላሉ ባለስልጣናት “እረ ልብ ግዙ “” ማለቴን እቀጥላለሁ። ሊሰሙ ይችላላሉ፤ ላይሰሙ ይችላሉ። ያ የነርሱ ዉሳኔ ነዉ። የኔ ድርሻ ግን መናገር ነዉ።