በኢትዮጵያ ከሚገኘው የቃል ኪዳኑ ታቦት ጋር በተያያዘ ከፍተኛ የሆነ ሴራ እየተጠነሰሰ መሆኑ ተዘገበ
የኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቭዥን ኢሳት ባወጣው ዘገባ በኢትዮጵያ ከሚገኘው የቃል ኪዳኑ ታቦት ጋር በተያያዘ በዘረኛው የወያኔ አገዛዝ ከፍተኛ የሆነ ሴራ እየተጠነሰሰ መሆኑ መረጃዎች ማመልክታቸውን ገልጹአል።
እግዚአብሄር ለሙሴ ጽፎ የሰጠው የቃል ኪዳኑ ታቦት የሚገኝበት ቦታ ለሺ አመታት አለምን ሲያነጋግርና የበርካታ የታሪክ ተመራማሪዎችን ቀልብ ስቦ ቆይቷል፤ ያለው ኢሳት ታዋቂው ጋዜጠኛና የታሪክ ተመራማሪ የሆኑት ግርሀም ሀንኮክ ከ8 አመታት በፊት ” ዘ ሳይን ኤንድ ዘ ሲል” በሚለው መጽሀፋቸው የቃል ኪዳኑ ታቦት ኢትዮጵያ ውስጥ እንደሚገኝ የሚጠቁም መጽሀፍ አሳትመዋል ካለ ቦኋላ በመጽሀፋቸውም የካቶሊክ እና የአይሁድ እምነት ተከታዮች አውሮፓውያን ታቦቱን ፍለጋ ወደ ኢትዮጵያ በተደጋጋሚ መመላለሳቸውን መጠቆማቸውን አውስቱአል።
እንደ ኢሳት ዘገባ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የታሪክ ባለሙያዎች፣ ፖለቲከኞችና የሀይማኖት መሪዎች፣ ለቃል ኪዳኑ ታቦት ልዩ ትኩረት በመስጠት፣ ዘረኛው አገዛዝና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ታቦቱን ለአለም ህዝብ ይፋ በማድረግ እውነተኛነቱን እንዲያረጋግጡ ግፊት ሲያድረጉ ቆይተዋል፡። የአለም ህዝብ ትኩረት በታቦቱ ላይ በአረፈበት በአሁኑ ጊዜ፣ የአገዛዙ ቁንጮ መለስ ዜናዊ ይህን እድል በመጠቀም ታቦቱን ለጉብኝት በማቅረብ ወይም በድብቅ በመሸጥ ከፍተኛ የሆነ ገንዘብ ለማግኘት አንድ አደገኛ እቅድ እያቀደ ለመሆኑ ፍንጮች መታየት ጀምረዋል።
ቀደም ብሎ በአንትሮፖሎሎጂስቶች ዘንድ ድንቅ የታሪክ ግኝት ተደርጋ የምትቆጠረውና ኢትዮጵያ የሰው ልጆች መገኛ ናት የሚለውን ማእረግ እንድትጎናጸፍ ያስቻለቸው ሉሲ ወይም ድንቅነሽ ፣በመለስ ዜናዊ ትእዛዝ ወደ አሜሪካ እንድትወጣ መደረጉ የሚታወቅ ሲሆን ድንቅነሽ ከአገር ስትወጣ በርካታ ኢትዮጵያውያንና የታሪክ ባለሙያዎች ከፍተኛ የሆነ ተቃውሞ ማሰማታቸው ይታወሳል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ በርካቶች መለስ እንደተመነው ከሉሲ ጉዞ በቂ ገንዘብ ሊያገኝ እንዳልቻለ ይገልጻሉ። ሉሲን ወደ አሜሪካ ለመላክ የተወሰደው እርምጃ ትልቅ ስህተት እንደነበር የሚናገሩት እነኝሁ አስተያየት ሰጪዎች የተገኘው ገንዘብ አነስተኛ መሆን ብቻ ሳይሆን ፣ ከእንግዲህ ሉሲ ወደ ኢትዮጵያ አትመለስም የሚለው ስጋት እንደሚያሳስባቸው ይጠቁማሉ።
የቃል ኪዳኑን ታቦት በተመሳሳይ መልኩ ለኢግዚቢሽን ወይም ለሽያጭ ለማቅረብ እየተወጠነ ያለው ሴራ ኢትዮጵያ በምንም ገንዘብ ሊተመን የማይችለውን ውድ ሀብቷን እንድታጣ ያደርጋታል ያለው ኢሳት የወያኔው ቀኝ እጅ አቡነ ጳውሎስ “ታቦቱን ለአለም አሳያለሁ” የሚል መግለጫ ከሰጠ በሁዋላ፣ ወዲያውኑ ከምመናን ከፍተኛ ተቃውሞ ሲያጋጥመው “የጣሊያን መገናኛ ብዙሀን ቃለምልልሴን አዛብተው አቅርበዋል” የሚል ማስተባበያ መስጠቱን አውስቱአል።
በጊዜው የካቶሊክ የሀይማኖት አባቶች የቃል ኪዳኑን ታቦት አይተው ለማረጋገጥ የሚፈቀድላቸው ከሆነ ለአቡነ ጳውሎስ 25 ሚሊዮን ዶላር ለመስጠት ቃል እንደተገባላቸው ተዘግቧል ያለው ኢሳት ገንዘቡ የሚለግሰው “ዳኮስታ ፋውንዴይሽን” በተባለው የኢጣሊያ የኢንዶውመንት ድርጅት በኩል ሲሆን ፣ አቡነ ጳውሎስ ገንዘቡ ” በቫቲካን የሚገኘውን አይነት ሙዚየም በአክሱም ከተማ ለማሰራት ይውላል ብሎ” ተናግሮ ነበር ብሉአል።
ኢሳት ቀጥሎም በአቡነ ጳውሎስና በሮማ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ባለስልጣናት መካከል እንደ ድልድይ ሆነው በማገልገል ላይ የሚገኙት በኢትዮጵያ ያደጉት ጣሊያናዊው ጁሊዮ ቢሰሪ ወይም አክሊለ ብርሀን መኮንን የሚባሉት ባለሀብት ናቸው ያለ ሲሆን አቡነ ጳውሎስ ከፖፕ ቤኔዲክት 16ኛ ጋር ሲገናኝ ከአጀቡዋቸው መካከል እኝህ ባለሀብት አንዱ ናቸው። እንዲሁም ጁሊዮ ቢስሪን ወይም አክሊለ ብርሀን መኮንንን ከዘረኛው መለስ ዜናዊና አዜብ መስፍን ጋር የሚያገናኙት ደግሞ ፣ የስዩም መስፍን የጋብቻ ዘመድ የሆነው ቆንስጠንጢኖስ በርሄ ነው ብሉአል።
ቆንስጠንጢኖስ በርሄ ፣ጁሊዮ ቢሴሪ ወይም አክሊብርሀን መኮንን፣ ጊዮን ሆቴልን በ512ሚሊዮን ዶላር ለመግዛት ተስማምቶ የመጀመሪያውን 210 ሚሊዮን ዶላር መክፈል ተስኖት ግዢውን እስካቆመበት ጊዜ ድረስ የባለሀብቱ የኢትዮጵያ ወኪል ሆነው በኦፊሴል አገልግሉአል።
ቆንስጠንጢኖስ በርሄ መለስ ዜናዊን ከውጭ አበዳሪ ድርጅቶች፣ ከቻይና ፣ ከህንድ እና ከሌሎችም አገሮች ጋር የሚያገናኝ ሰው መሆኑ የሚነገርለት ሲሆን አቡነ ጳውሎስ ላለፉት ሁለት አመታት ጉዳዩ ትኩረት እንዳይሰጠው አድርገውት የቆዩ መሆኑንና ፣ ሰሞኑን ደግሞ ለቫቲካን ባለስልጣናት የገቡትን ቃል ተግባራዊ ለማድረግ “የቤተክርስቲያኑ ጣሪያ” ያፈሳል የሚል ሰበብ እንዲነገር ማስደረጋቸውን የውስጥ አዋቂዎች ይናገራሉ።
የቃል ኪዳኑ ታቦት የሚገኝበት ቤተክርስቲያን ጣሪያው ቢያፈስ እንኳን ጉዳዮ በድብቅ ተይዞ ህንጻው እድሳት ይደረግለታል እንጅ ፣ በምንም ተአምር ዜናው ለአለም ህዝብ ሊገለጥ አይገባውም ሲሉ አዋቂዎች ይናገራሉ።
አሁን በጣሪያ ማፍሰስ ሰበብ ፣ የቃል ኪዳኑን ታቦት ለአለም ለማሳየት የሚደረገው ሩጫ በጊዜ ካልተገታ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክ ቤተክርስቲያንን ታሪክ ስር መሰረት ያናጋዋል የሚሉ አስተያየቶችም ቀርበዋል።
ህዝብን በቋንቋና በባህል ለማጋጨት ወያኔ ለ20 አመት የሸረበው ተንኮል አለመሳካቱን ከተረዳበት ምርጫ 97 ወዲህ ተከባበረውና ተቻችለው የኖሩትን ሁለቱን ታላላቅ ሃይማኖቶች ምዕመናን እርስ በርስ ለማጋጨት አንዴ መጽሃፍ ቅዱስን ሌላ ጊዜ ደግሞ ቅዱስ ቁራንን የሚያዋርዱና የሚያንቋሽሹ ሰዎችን በማሰማራት በተለያዩ ቦታዎች ለሰው ህይወት መቀጠፍ ምክንያት የሆኑ ግጭቶችን በ እጅ አዙር ማስነሳቱ ይታወቃል።
ከዚያም አልፊ ሙስሊሙን እርስ በርስ ለማከፋፈል እየተካሄደ ካለው ግልጽና ቀጥተኛ ጣልቃ ገብነት በተጨማሪ በኦርቶዶክስ ምዕመናን ዘንድ ትልቅ ክብርና ስፍራ የሚሰጠውን ጽላት በግላጭ አደባባይ በማውጣት ለማራከስና ከቱርስቶች ገንዘብ ለመሰብሰብ መዘጋጀቱ ብዙዎችን እያስቆጣ ነው።