ዘራፊው የወያኔ አገዛዝ እየመዘበረ ያለው የህዝብ ሃብትና ንብረት እጅግ እያሳሰባቸው መሆኑን በዓለም ባንክ ተቀጥረው በማገልገል ላይ የሚገኙ ኢትዮጵያዊ ገለጹ

በቅርቡ በዘረኛውና ዘራፊው የወያኔ አገዛዝ ባለስልጣናትና ባለሟሎቻቸው እየተመዘበረ ከኢትዮጵያ የሚወጣው ከፍተኛ ገንዘብ እጅግ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱንና ኢትዮጵያዊያንም ዘራፊው ወያኔ የሚያካሂደውን ምዝበራ እንዲያቆም እንዲነሱ አንድ በዓለም ባንክ ተቀጥረው በማገልገል ላይ የሚገኙና ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የዓለም አቀፉ ባንክ ሰራተኛ አሳሰቡ። በባንኩ ውስጥ ለረጂም አመታት ያገለገሉት እኚሁ ታውቂ ኢኮኖሚስት እንደገለጹት የወያኔው አገዛዝ ያለማንም ሃይ ባይና ተቃዋሚ የሃገሪቱን አንጡራ ሃብትና ንብረት እንዲህ እንደፈለገው እየዘረፈ ሲወስድ ኢትዮጵያዊያን በዝምታ መመልከታቸን የታሪክ ተጠያቂዎች እንደሚያደርገን ልንረዳ ይገባል ብለዋል።

ባለፈው ሳምንት ግሎባል ፋይናንሺያል ኢንተግሪቲ በመባል የሚታወቀው ዓለም አቀፍ ተቁአም፣ በፈረንጆች አቆጣጠር በ2009 ዓም ብቻ ከአገራችን ተሰርቆ በህገወጥ መንገድ ወደውጪ ባንኮች የገባው ገንዘብ መጠን 3 ነጥብ .26 ቢሊዮን ዶላር መድረሱንና እስከ 2008 በነበሩት አመታት ተዘርፎአል ተብሎ በተባበሩት መንግሥታት የልማት ድርጅት ይፋ ከሆነው 8 ነጥብ 4 ቢሊዮን ዶላር ጋር ሲደመር በ9 አመት እድሜ ውስጥ በዘረኛው የወያኔ አገዛዝ በሕገወጥ መንገድ ከአገራችን በዝርፊያ የወጣው ገንዘብ መጠን አሥራ አንድ ነጥብ ሰባት ቢሊዮን ዶላር መድረሱ ተጋልጦአል።

ዓለም አቀፉ ተቋም ባወጣው በዚሁ ጥናታዊ ሪፖርቱ እንደ ኢትዮጵያ ካሉት ድሃ ሃገራት የሚመዘበረው ህልቆ መሳፍርት የሊለው ገንዘብ የሚባክንበት ዋነኛው ምክንያት ከሙስና ጋር እንደሚያያዝ፣ ቀሪው ደግሞ ከአገሮች የገቢና የወጪ ንግድ ውስጥ በሚፈጸም ሕገወጥ አሠራር መሆኑን ገልጾ ከኢትዮጵያ እ.ኤ.አ. በ2009 እኤአ. ብቻ በሕገወጥ መንገድ የተመዘበረው ከ3 ነጥብ .26 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገንዘብ አገሪቱ እ.ኤ.አ. በ2009 ከወጪ ንግድ ካገኘችው ከሁለት ቢሊዮን ዶላር በእጅጉ የሚበልጥ ነው ብሎአል፡፡

ዘረኛው የወያኔ አገዛዝ ስልጣን ከተቆጣጠረ ቦኋላ ቀደም ሲል በመንግሥት ይዞታ ሥር የነበሩ የማምረቻና የማከፋፊያ ድርጅቶች በሙሉ ያለምንም ጫረታና ተፎካካሪ በሽያጭ ሥም ወደ ኤፈርት ንብረትነት እንዲዘዋወር በማድረግ ላለፉት 20 አመታት በአገሪቱ ውስጥ የተገነቡ መሠረተ ልማቶች ፤ህንጻዎች፤ መንገዶች፤ ት|ቤቶች፤ ሆስፒታሎች ወዘተ ግንባታ ያለምንም ተቋራጭ ሥራውን ተኮናትሮ እንዲሰራ በማድረግ የአገሪቱን ሃብት ያለምንም ተፎካካሪ በብቸኝነት ተቆጣጥሮታል። ህወሃት በኤፈርት ሥም የሚቆጣጠረው ሃብት መጠን ቢገለጽ በዝርፊያ ከአገር ወጥቶአል የተባለውን የገንዘብ መጠን በብዙ መቶ እጥፍ እንደሚበልጥ ይገመታል።

ይህንኑ ሃቅ በአንድ ወቅት ኩባንያውን ኤፈርት በሃላፊነት ይመራ የነበረው ከቀንደኞቹ የወያኔ መሪዎች አንዱ የሆነው አቦይ ስብሃት ለአሜሪካ አድምጽ ሬዲዮ በሰጠው ቃለመጠይቅ ማረጋገጡ አይዘነጋም።

በዘረኛውና አምባገነኑ መለስ ዜናዊ የሚመራው ሃገር አጥፊ ቡድን ወደ ስልጣን ከመጣበት ጊዜ ጀምሮ በተለያዩ ጊዚያቶች ከሃገር ወጥቶ ወደ ውጪ ሃገራት በሚገኙ የተለያዩ ባንኮች መጠኑ እጂግ ከፍተኛ የሆነ ገንዘብ እየተዘረፈና እየተከማቸ እንደሆነ በተደጋጋሚ ስንዘግብ መቆየታችን አይዘነጋም። የሙስና እናት በመባል የምትታወቀው የመለስ ዜናዊ ባለቤት አዜብ መስፍን ከአንድ አመት በፊት በአንዲት ቀን ግብይት ብቻ ከ 1. 5 ሚሊዮን ይሮ በላይ ወጪ ማድረጉአን አንድ ታዋቂ የስፔን ጋዜጣ ማጋለጡ ይታወሳል።