የአንድነት ፓርቲ ጠቅላላ ጉባኤውን በተሳካ ሁኔታ ማካሄዱንና የፓርቲውን አመራሮችንም በዲሞክራሲያዊ መንገድ መምረጡን አስታወቀ

አንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ለሁለት ቀናት ጠቅላላ ጉባኤውን ካደረገ በሁዋላ፣ የፓርቲውን ሊቀመንበር፣ የብሄራዊ ምክር ቤት እና የኦዲትና ኢንስፔክሽን አባላትን መርጧል።የቀድሞውን ፕሬዚዳንት ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳን በሊቀመንበርነት የመረጠው ጉባኤ፣ ለብሄራዊ ምክር ቤት ከመረጣቸው 40 ሰዎች መካከል በእስር ላይ የሚገኘውን አቶ አንዱአለም አራጌን ጨምሮ ዶ/ር ሀይሉ አርአያ፣ ዶ/ር ንጋት አስፋው፣ አቶ አስራት ጣሴ፣ አቶ ተመስገን ዘውዴ፣ አቶ ግርማ ሰይፉ እና አቶ ስዬ አብርሃ ይገኙበታል።

ጠቅላላ ጉባኤው ስብሰባውን ሲያጠቃልል ባወጣው መግለጫ፣ ገዢው ፓርቲ ህገወጥ በሆነ መንገድ ያሰራቸውን አመራሮች አቶ አንዱአለም አራጌንና አቶ ናትናኤል መኮንንን ጨምሮ ሌሎች የፓርቲውን አባላትና የህሊና እስረኞች እንዲፈታ ጠይቋል።

ፓርቲው የመጪውን ዓመታት የትግል ጉዞ የእድሳትና የማንሰራራት ዘመን በማለትም ሰይሞታል።

በሌላ በኩል ደግሞ በስልጣን ላይ ያለውን ፓርቲ በምርጫ ማስወገድ አይቻልም ሲሉ ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ ተናግረዋል።

ዶ/ር ነጋሶ የቪኦኤ የእንግሊዝኛ ዘጋቢ ከሆነው ፒተር ሄይንላይን ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ እንደገለጡት፣ አሁን የተዘረጋው የፖለቲካ ስርአት ምርጫ ለማካሄድ አመቺ ባለመሆኑ ያለው ብቸኛ አማራጭ ሥልጣን ላይ ያለውን ሃይል በትግል ማውረድ ብቻ ነው።

“አምባገነኖች ለረጅም ጊዜ እንደማይኖሩ አይተናል፣ የሆነ ጊዜ ህዝቡ ተነስቶ በቃችሁ ይላል። በዚህ ዓመት ላይሆን ይችላል። በሚቀጥለውም ዓመት ላይሆን ይችላል። ነገር ግን የሆነ ሰአት ላይ ህዝቡ ተቆጥቶ ይነሳል። ለውጥ የሚመጣውም በዚህ መልክ ነው።” ያሉት ዶ/ር ነጋሶ ኢህአዴግ ብለው የጠሩት ህወሃት ኮሚኒስታዊ አስተሳሰቡን አለመተውን በዚህም ምክንያት ራሱን ትክከለኛ እና ብቸኛ ሀይል አድርጎ በማስቀመጥ ለረጅም ጊዜ በስልጣን ላይ ለመቆየት ህልም እንዳለው አልሸሸጉም።

የአንድነት ፓርቲ ሁለት ኮከብ መሪዎቹ ከግንቦት7 ጋር በማበር በሚል የወያኔ ፈጠራ ውንጀላ በጸረ ሽብር ስም እስር ቤት እንደሚገኙ ይታወቃል።

አንዱአለም አራጌ እና ናትናኤል መኮንን ሰላማዊ ትግሉን ወደ ፊት በመግፋት ገዢውን ፓርቲ ከፍተኛ ስጋት ውስጥ ከትተውት እንደነበር የአደባባይ ምስጥር ነው።