መለስ ዜናዊ የአፍሪካን የአካባቢ ጉባኤ ለመምራት የሞራል ብቃት የለውም ሲሉ አንድ ደቡብ አፍሪካዊት ጸሀፊ ገለጡ

ጃኒስ ዊንተር የተባሉት ጸሀፊ ደይሊ መቨሪክ በሚባለው የደቡብ አፍሪካ ጋዜጣ ባወጡት ጽሁፍ፣ በደርባን የተካሄደው ኮፕ 17 የአካባቢ ጥበቃ ጉባኤ፣ ድንቅ የተባለ ስምምነት አድርጓል። በጸሃፊዋ አመለካከት የስምምነቱ ዋና ድል ተብሎ የተቆጠረው ደግሞ፣ የአካባቢ ጥበቃ ለማካሄድ የተፈቀደው ገንዘብ ነው።

የአፍሪካ ህብረት አምባገነኖች ዋና ተደራዳሪያቸው አድረገው ከ2 አመት ገደማ በፊት የሰየሙት ዘረኛውና አምባገነኑ መለስ ዜናዊ በጉባኤው ላይ ለአካባቢ ጥበቃ ተብሎ የተመደበው ገንዘብ አዲስ ገንዘብ አለመሆኑን ይልቁንም ከዚህ ቀደም ለእርዳታ ተብሎ ከተያዘው ላይ የሚሰጥ መሆኑን በመጥቀስ ሀብታም አገሮች ከፍተኛ ገንዘብ እንዲመድቡ ተማጽኖ አቅርቦ እንደነበር ተገልጾአል።

“ምንም እንኳ “ይላሉ ጸሀፊዋ ሲቀጥሉ” አፍሪካ በአየር ለውጥ ምክንያት ዋናዋ ተጎጂ አገር ብትሆንም፣ የተፈቀደው ገንዘብ ግን አምባገነኖችን በስልጣን ላይ ለማቆየት መዋል እንደሌለበት ማረጋገጥ ያስፈልጋል።

መለስ ዜናዊ በአገሩ ውስጥ የሰብአዊ መብቶችን የረገጠ፣ ጋዜጠኞችን፣ የፖለቲካ ተቃዋሚዎችን በጸረ ሽብርተኝነት ስም ለእስር የዳረገ፣ በምርጫ 97 ወቅት 199 ሰዎችን የገደለ፣ የእርዳታ እህልን ለፖለቲካ ድጋፍ መግዢያ ያዋለ፣ በቅርቡ ይፋ በሆነው የግሎባል ፋይናንሻል ኢንተግሪቲ ሪፖርትም ባለፉት 9 አመታት ከኢትዮጵያ የተዘረፈ 11 ነጥብ 7 ቢሊዮን ዶላር ወደ ውጭ መውጣቱ የተረገጋጠ በመሆኑ የአፍሪካን የአየር ለውጥ ጉባኤ የመምራት የሞራል ብቃት የለውም ብለዋል ጸሃፊዋ።

ይህ ገንዘብ መለስ ዜናዊን በመሳሰሉ የአፍሪካ አምባገነኖች እጅ የሚወድቅ ከሆነ ከዚህ ቀደም እንደተደረገው ሁሉ፣ አሁንም ገንዘቡ የአምባገነኖችን የስልጣን እድሜ ለማራዘሚያነት ሊውል ይችላል።

መለስ ሁለት አሀዝ የኢኮኖሚ እድገት እንዳገኘ አድርጎ በማስወራት የምእራብ አገሮችን ስሜት ለመያዝ መቻሉን የገለጹት ጸሀፊዋ፣ የመለስ ዜናዊ ሁለት አሀዝ እድገት እስከዛሬ በታዋቂ ኢኮኖሚስቶች አለመረጋገጡንና ነገር ግን በአለፉት 20 አመታት ኢትዮጵያ ያስመዘገበችው እድገት ከ5 በመቶ እንደማይበልጥና ይህም የዕድገት አሀዝ ባለፉት ተከታታይ አመታት አፍሪካ ካስመዘገበቺው አጠቃላይ 6 በመቶ እድገት ጋር ሲተያይ አነስተኛ መሆኑን ጠቁመዋል።

በኢትዮጵያ ውስጥ የእርዳታ ገንዘብ በተገቢው መንገድ ስራ ላይ መዋሉን የሚቆጣጠር ነጻ የሲቪክ ተቋማት በሌሉበት ሁኔታ ገንዘብ መፍቀድ ማለት እነመለስ ዜናዊ እንዲዘርፉትና ገንዘባቸውን ወደ ውጭ እንዲልኩ የሚያደርጉበትን ሁኔታ ማመቻቸት ነው።

ጸሀፊዋ ለጋሽ አገሮች ገንዘቡን በትክክል የሚቆጣጠሩበትን ስርአት ሳይዘረጉ ገንዘቡን መለቀቅ እንደሌለባቸው አስጠንቅቀዋል።