ጉራማይሌ
በኑረዲን – ከመርካቶ
አገራችን ኢትዮጵያን በረጂም ዘመን ታሪኳ ዉስጥ አያሌ ነገስታት፤ሁለት ፕሬዚዳንቶችና አንድ ጠ/ሚኒስትር መርተዋታል። የእነዚህ መሪዎች በህዝብ መወደድና እነሱ ለህዝብ ያላቸዉ ክብር እንደየመልካቸዉ ይለያያል ሆኖም ብዙዎቹ መሪዎቻችን ኃይለኝነታቸዉ እንዳለ ሆኖ ብዙ የሚወደድ ባህሪይ ነበራቸዉ። ከሞላ ጎደል ብዙዎቹ የቀድሞ መሪዎች አገራቸዉን የሚወዱና ከራሳቸዉ ጥቅምና ዝና ይልቅ የአገራቸዉን ክብርና አንድነት የሚያስቀድሙ ነበሩ። ዛሬ ያልተጣለ ዕጣ ወጥቶላቸዉ አገራችንን የሚመሩት አቶ መለስ ዜናዊ ከቀድሞ መሪዎቻችን ጋር የሚጋሩት አንድ ነገር ቢኖር “መሪ” የሚለዉ ቃል ብቻ ነዉ። በተረፈ አቶ መለስ ኢትዮጵያን አይወዱም፤ ህዝብን ይንቃሉ፤ የአገር አንድነት ያፈርሳሉ፤ዘረኛ ናቸዉ፤ ተሳዳቢ ናቸዉ፤ ዉሸታምና ቂመኛ ናቸዉ። በአጠቃላይ አቶ መለስ ብዙ ነገር ናቸዉ። የእሳቸዉን አንግዳ የሆነ ባህሪይ በአንድ ጽሁፍ ማቅረብ የሚቻል አይመስለኝም፤ ለዚህ ነዉ ዛሬ ሁሉንም ጠባያቸዉን ቀላቅዬ “ጉራማይሌ” ብዬ ብቅ ያልኩት።
ትዝ ይለኛል እናቴ በልጅነቴ “ሀሁ” ስታስቆጥረኝ ወደ ፊደሉ አላይ እያልኩ ሳስቸግራት …. “ልጄ አይንኮ ካላዩበት ግንባር ነዉ” ትለኝ ነበር። አዎ አይን ካላዩበት ግንባር ነዉ። ጆሮም ቢሆን ካልሰሙበት መልኩን አሳምሮ እንደ ትልቅ ወንፊት ከአንገት በታች ከመኮፈስ ሌላ የሚፈይደዉ ምንም ፋይዳ የለም። አገራችን ኢትዮጵያ ዉስጥ ደግሞ ጆሮ መልክ ያሳምራል የሚባለዉ ከሰዉዬዉ ፊት ጋር ተመጣጥኖ ሲቀመጥ ነዉ እንጂ እንደ ኮባ ቅጠል ሰፋ ብሎ ከተንዠረገገማ ጭራሽ የዕድሜ ልክ ቅጽል ስም ያስሰጣል እንጂ ለመልክም ቢሆን አይበጅም። ደሞ ዛሬ ምነዉ ጆሮ ጆሮ አሰኘህ ትሉኝ ይሆናል። ወገኖቼ አትፍረዱብኝ – “የቸገረዉ እርጉዝ ያገባል የባሰበት እመጫትዋን” እንደሚባለዉ እኔም ብሶብኝ ነዉ ጆሮ ደግፍ እንደያዘዉ ሰዉ ጆሮ ጆሮ የሚያሰኘኝ እንጂ ወድጄማ አይደለም። የአገር መሪ ናቸዉ ብዬ እንደ ሞዴል የማያቸዉ ጠ/ሚኒስቴር መለስ ዜናዊ በሬዲዮ ስሰማቸዉ ስድብ፤ በቴሌቪዥን ስመለከታቸዉ ስድብ በጋዜጣም ሳነባቸዉ ነገረ ስራቸዉ ሁሉ ስድብ ብቻ ሆነብኝና ሬዲዮኑንም፤ ጋዜጣዉንም ቴሌዥኑንም ተዉኩላቸዉና አላነብብ አልሰማ ነገር ኮሌጅ የጨረሰ መሀይም ሆኜ ቀረሁ። ዝንተ አለሙን አይነ ስዉር ሲመራዉ ሰጥ ለጥ ብሎ የሚመራ አይናማ ዕጣ ፊደሉ አይነ ስዉር መሆን ነዉና ኮሌጅ የጨረሰ መሀይም መሆኔ ብዙም አልገረመኝም። ይልቁን እኔን የገረመኝና እንዳረረ ማሽላ የሚያንጫጫኝ ባለፈዉ ሰሞን እኚሁ ጉደኛ ጠ/ሚኒስቴር ፓርላማ ዉስጥ ያቺን ሁሌም ወደ ሌላ ሰዉ እንጂ ወደራሳቸዉ ዞራ የማታዉቀዉን ሌባ ጣታቸዉን ወደ ፓርላማዉ አባላት ቀስረዉ ያደረጉት ንግግር ነዉ። ጠ/ሚኒስትሩ እንዲህ ነበር ያሉት – “የኢትዮጵያ መንግስት ማየትና መስማት የተሳነዉ መንግሰት አይደለም፤ ማየትና መስማት የሚችል መንግስት ነዉ” እኚህ ችኮና ከራሳቸዉ ዉጭ ማንንም የማይሰሙ ጠ/ሚኒስቴር እዉነትም የሚሰማ ጆሮና የሚያይ አይን ቢኖራቸዉ ኖሮ የሃያ ሰባት አመቱ ወጣት የኔነህ ገብሬ እሳቸዉ ሆን ብለዉ በፈጠሩት ዘረኛ ስርዐት ዉስጥ ከመኖር ሞት ይሻላል ብሎ እራሱን በእሳት አቃጥሎ መሞቱን ሰምተዉ እራሳቸዉን ይመረምሩ ነበር። ወይ ጉድ! እኔ ነኝ ነገር የማይገባኝ ዕብድ እንጂ ጠቅላይ ሚኒስቴር መለስ ዜናዊማ የህዝብ ጆሮ ለመዝጋት አንጂ ህዝብን ለመስማት መች ተፈጠሩና ነዉ!
እኔ አስከማዉቃቸዉ ድረስ ጠ/ሚኒሰትር መለስ ዜናዊ ጆሯቸዉ ወለል ብሎ የሚከፈተዉና አሳቸዉም እያንዳንዷን ድምፅ የሚሰሙት ይህ አላግባብ ከሃያ አመት በላይ የተቀመጡበት የስልጣን ወንበር ሲነቃነቅ ብቻ ነዉ። ክቡር ጠ/ሚኒስቴር አቅጯን ልንገርዎት – እንኳን ሌባ ጣትዎን ሰዉነትዎ ላይ ያሉትን ጣቶች ሁሉ እንደቀሰሩ ቀመዉ ይቀሯታል አንጂ ይህ መነቃነቅ የጀመረዉ ወንበር መሰበሩ አርሶና እረስዎ የፈጠሩት ዘረኛ ስርዐትም መፈራረሱ አይቀርም። በእርግጥ የኢትዮጵያ መንግስት የሚሰማ መንግስት መሆኑን መናገር ከፈለጉ የህዝብን ድምፅ ይስሙ፤ የህዘብ ድምፅ ደሞ “በቃ” ነዉ የሚለዉ። በቃ!
ክቡር ጠ/ሚኒስትር. . . እርሶና መንግሰትዎ ማንንም እንደማትሰሙ እኔም እርሶም በሚገባ እናዉቃለን። እስኪ በሚወዱት ይዤዎታለሁ። የዛሬን ብቻ ይስሙኝ- ምነዉ ጠ/ሚኒስትር! አንዳንዴ ዋልድባም ይዘፈናልኮ!! ለሁሉም አርሶ ባይሰሙኝም እኔ አንዳንዴም ቢሆን እሰማዎታለሁና የቅርብ ግዜ ክፋትዎን ላስታዉሶት። የአገራችንን መሬት ለባዕዳን ሲቸበችቡ አይተን ምነዉ ስንሎት የሰጡን ምክንያት ከቴክኖሎጂ ሽግግሩ የሚገኘዉ ልምድና ከመሬቱ ሽያጭ የሚገኘዉ ገቢ የደሀዉን ገብሬ ህይወት ይለዉጣል የሚል ነበር። ክቡር ጠ/ሚኒስትር . . . እዉነትም የሚሰማ ጆሮ ያሎት ከሆነ በቅርቡ ኦክላንድ የጥናት ማዕከል ጋምቤላን አስመልክቶ ይፋ ያደረገዉን መረጃ የሰሙ ይመስለኛል። ማዕከሉ ጋምቤላ ድረስ ተጉዞ ባሰባሰበዉ መረጃ መሠረት ከእርሶ የሚሰማና የሚያይ ጆሮ ካለዉ መንግሰት መሬት ተረክበዉ እርሻ ከጀመሩ የአገር ዉስጥ ባለ ሃብቶች ዉስጥ ከአንዱ በቀር ሁሉም የትግራይ ተወላጆች ናቸዉ። አደራ ጠ/ሚኒስትር ይህንን የተናገሩት መኢዴፓ፤ አንድነት፤ ኦነግ ወይም ግንቦት ሰባቶች ሳይሆኑ ኦክላንድ የጥናት ማዕከል ነዉ። “ጉድ ሳይሰማ መስከረም አይጠባም” ይላል የአገሬ ሰዉ . . . . ደሞ ምን ጉድ ሊያሰሙን ይሆን የኛ ጠ/ሚኒስትር? ያ ጉደኛ ፓርላማዎ እንደለመደዉ ኦክላንድ የጥናት ማዕከልንም “ሽብርተኛ” ብሎ ፈረጀዉ እንዳይሉኝና እንዳያስቁኝ። ለመሆኑ በኦክላንድ የተነሳ ወዳጅዎ አሜሪካንንም የሽብርተኞች ተባባሪ ብለዉ ይሰይሟት ይሆን? ወይስ የጥናት ማዕከሉ አስመራ ዉስጥ ግብር ከሚበሉትና በአኬልዳማ ቊጥር ሁለት ድራማ ዉስጥ ከሚካተቱት “ፀረ ኢትዮጵያ” ሃይሎች ዉስጥ አንዱ ነዉ? ክቡር ጠ/ሚኒስትር ለመሆኑ እየሰሙኝ ነዉ? የሚሰሙኝ ከሆነ እባክዎ መልስ ይስጡኝ!
ክቡር ጠ/ሚኒስትር. . . የእርሶ ነገርኮ ሲቀምሱት የሚመር ሲሰሙት የሚገርም ነዉ። ለመሆኑ ለምለም መሬት ባዩ ቁጥር ወለል ብላ የምትታዮት ትግራይ ብቻ ናት እንዴ? የሚገርመዉ ነገረ ስራዎ ሁሉ እንደ አገር መሪ ሳይሆን “ከራቀህ ሳብ” “ቀረብ ሲል ሸብ” እንዳለዉ ሌባ ነዉ። ወልቃይት ጠገዴ ለትግራይ ቅርብ በመሆኗ ከጎንደር ሳብ አድርገዉ ትግራይ ዉስጥ ሸጎጧት። ጋምቤላ ግን ሳብም ሸብም ለማድረግ አልመች አለችዎት መሠለኝ ባለሐብቶችን ከትግራይ እየጎተቱ ያሰፍሩባት ጀመር። ምነዉ ክቡር ጠ/ሚኒስትር? ኧረ እየተስተዋለ! ሌላ ሁሉ ቢቀር ይህ በልጅነትዎ የተጠናወቶት ዘረኝነት እንዳለ ሆኖ ምነዉ ኦሮሞዉን፤ አማራዉን፤ ጉራጌዉን፤ሱማሌዉንና ይህንን ብሔር፤ብሔረሰብና ህዝብ እያሉ የሚጠሩትን ህብረተሰብ አንዳንዴ አይንዎ ቢመለከተዉ? ወይስ የኢትዮጵያ ህዝብ ቁጥሩ ስንት ነዉ ተበለዉ ቢጠየቁ እርሶም ያንን በቀድሞዉ ንጉሳችን ላይ የምንቀልደዉን አይነት መልስ ሊሰጡን ነዉ?
ክቡር ጠ/ሚኒስትር . . . መቼም የእርሶ ጉድ ብዛቱና የሰማይ ስፋቱ መጠን የለዉምና እስኪ እሱን ትቼ አንድ የቆየ ነገር ላስታዉሶት! ለመሆኑ አንድ አገራቸዉን የሚወዱ የትግራይ ተወላጅ ወያኔን አንዲቀላቀሉ የቀረበላቸዉን ጥያቄ አስመልክቶ ከእርሶ ጋር ያደረጉት ምልልስ ትዝ ይሎታል? ምናልባት በስራ ብዛት የተነሳ ረስተዉት ከሆነ እስኪ እኔ ላስታዉሶት! ጉዳዩ አንዲህ ነዉ። እርሶ እንግሊዝ አገር ስልክ ይደዉሉና ኢትዮጵያዊዉን ምሁር አብረን እንስራ ብለዉ ይጋብዟቸዋል። ምሁሩም – ለመሆኑ ይህ አንተ የምትመራዉ የአናሳዎች አገዛዝ በዚህ መልኩ ሃምሳ አመት የሚቆይ ይመስልሃል ብለዉ ጥያቄዎን በጥያቄ ይመልስሎታል። ክቡር ጠ/ሚኒስትር በዱሪዬ ቋንቋ ሲሳደቡ በአይኔ በብሌኑ አይቻለሁ፤ የኢትዮጵያን ታሪክ ሲንቁና ሲያንቋሽሹ በጆሮዬ ሰምቻለሁ ፤አብሮ አደግ ጓደኞቼ በእርሶ ትዕዛዝ ሲገደሉ ተመልክቻለሁ። ሆኖም ለእኝያ እንግሊዝ አገር ለሚኖሩት ኢትዮጵያዊ ምሁር እንደመለሱት መልስ የእርስዎን ማንነት እዉስጥ አንጀትዎ ድረስ ዘልቆ ያሳየኝ ምንም ነገር የለም። ክቡር ጠ/ሚኒስትር . . . የኢትዮጵያ ህዝብ የእርሶን ማንነት ተረድቶ ለመብቱና ለነፃነቱ ትግል ከጀመረ የቆየ ቢሆንም እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ እንደኔ ሆዱ ቆርጦና አንደ የኔነህ ገብሬ በህይወቱ ተወራርዶ እንዲታገልዎ ስለምፈልግ ያንን የእርሶን የዘፈቀ ዘረኝነት በግልፅ የሚያሳየዉንና አንግሊዝ አገር ለሚኖሩት ምሁር የመለሱትን አሳፋሪ መልስ ከነጥያቁዉ አንዳለ ማስቀመጥ እፈልጋለሁ።
ሀሎ – ኢትዮጵያ በእድገት ጎዳና በመገስገስ ላይ ናትና ለምን ወደ አገርዎ መጥተዉ ይሀንን የጀመርነዉን ጉዞ ከግቡ አያደርሱም?
ስለ እድገትና መረጋጋት ከማዉራታችን በፊት አንድ ጥያቄ ልጠይቆት . . . . ለመሆኑ ይህ እርሶ የሚመሩት የአናሳዎች አገዛዝ በዚህ መልኩ ለሃምሳ አመት የሚቀጥል ይመስሎታል?
“አይመስለኝም ! ሆኖም ሃምሳ አመት በማይሞላ ግዜ ዉስጥ የትግራይን ህዝብ እንደ አይሁድ ህዝብ ማድረግ እችላለሁ”
ክቡር ጠ/ሚኒስትር. . . እንግዲህ ይታዮት እርሶ በአንድ በኩል የድፍን ኢትዮጵያ መሪ ነኝ ይላሉ፤ በሌላ በኩል ደግሞ ጥረትዎ ሁሉ ትግራይን እስራኤል ለማድረግ ነዉ። ምነዉ ጠ/ሚኒስትር? እኛ የተቀረነዉ ኢትዮጵያዉያን ከህዳሴዉ ወተት ስልባቦቱ ከፌዴራሊዝም እኩልነት ዘፈኑ ብቻ ነዉ እንዴ የሚደርሰን? ለመሆኑ የትግራይ ዉድቀት ወድቀቴ የትግራይ ልማት ልማቴ መሆኑን ያዉቃሉ? ዬኔ ችግርኮ እኩል አለመታየታችንና እኩል የልማት ዕድል አለማግኘታችን ነዉ እንጂ እገሌ መራኝ አልመራኝ አይደለም። ክቡር ጠ/ሚኒስትር. . . እርሶና ፓርቲዎ ሽብር፤ሽብርተኛ፤ባግዳድና አኬልዳማ እያላችሁ ያሰኛችሁን ድራማ ስትሰሩ ትከርሟታላችሁ አንጂ እኛ ኢትዮጵያዉያን እኩልነታችን ተረጋግጦ የአገራችንን የፖለቲካ ሥልጣን እኩል እስካልተጋራን ድረስ የእርሶም ዕድል እንደ ጋዳፊ ቱቦ ለቱቦ ከመንከራተት የተለየ አለመሆኑን ከአሁኑ ላረጋግጥሎት እፈልጋለሁ። አሁንም የሚሰሙኝ ከሆነ እቅጩን ልንገሮት. . . . አንዳንዶቻችንን ማሰር፤ አንዳንዶቻችንን አገራችንን ጥለን እንድንሰደድ ማድረግ አንዳንዶቻችንን ደግሞ መግደል ይችሉ ይሆናል፤ ነገር ግን ምንም ያድርጉ ምን የነፃነትና የእኩልነት ፍላጎታችንን እንኳን መግደል መንካትም አይችሉም።
ክቡር ጠ/ሚኒስትር. . . እኔኮ ጭራሽ ግራ ገባኝ . . . ምን አድርጉ ወይም ምን ሁኑ ነዉ የሚሉን? ይህንን ጥያቄ የምጠይቆት ምናልባት አድርጉ የሚሉንን አድርገን ሁኑ የሚሉንንም ሆነን በሃያ አመት ዉስጥ አንድ ቀን እንኳን ከህዝብ አገር አብረዉ ብስቁ ብዬ ነዉ? መብታችንን ስንጠይቅ “ባግዳድ” እያሉ ሲኒማ ይሰሩብናል። የነፃነት ያለህ ስንል ደግሞ “አኬልዳማ” እያሉ ያልፈሰሰ ደም ያሳዩናል። ስንናገር “ሽብርተኛ”ዝም ስንል ደግሞ ጭራሽ “ሟርተኛ” ይሉናል። ክቡር ጠ/ሚኒስትር ኧረ ምን ይሻላል የእርሶ ነገርኮ ጨነቀኝ . . . እስኪ በማን ልበልዎ! በመድሐኒአለም እንዳልሎት “መድሐኒአለም” ከአገር አገር ከሰዉ ሰዉ ሳይለይ ሁላችንንም ነዉ ያደነዉ። በግሸን ማሪያም እንዳልሎት እርሶ ከወሎ ታቦት የትግራይ ጣዖት ይሻላል ባይ ኖት። ጠ/ሚኒስትር የሚሰሙኝ ከሆነ በዚያ በሚወዱት ታቦት በአቡነ አረጋዊ ይዤዎታለሁ . . . ለመሆኑ እኛ እንደርሶ ከዚያ ከወርቃማዉ ዘር ያልተወለድነዉ ኢትዮጵያዊያን ምን መስለን ነዉ የምንታዮት?
ክቡር ጠ/ሚኒስትር. . . ባለፉት ሃያ አመታት እርሶና ፓርቲዎ የሰራችሁት ድራማ ብዛቱና አይነቱ. . . እንዴ! እነዚህ ሰዎች መሪዎች ናቸዉ ወይስ ተዋንያን የሚያሰኝ ነዉ። እርሶ ፓርላማ ዉስጥ ከሚቀልዱት ቀልድና ቃለመጠይቅ በተደረጉ ቁጥር ከሚሠሩት ድራማ ዉጭ እርሶና ፓርቲዎ የህገ መንግሰት ድራማ፤ የፌዴራሊዝም ድራማ፤የምርጫ ድራማ፤ የህዳሴዉ ድራማ አሁን በቅርቡ ደግሞ እየቆየ ሲሄድ ቴክኖሎጂዉ እየገባችሁ መጣ መሠለኝ “ባግዳድ” እና “አኬልዳማ” የሚባል በድምጽና በምስል የተቀነባበረ ድራማ ሰርታችኋል። ክቡር ጠ/ሚኒስትር. . . የሰራችኋቸዉ ድራማዎች ሁሉ ፍንትዉ አድርገዉ የሚያሳዩት የእናንተን ቅሌትና ባዶነት ቢሆንም ከሰሞኑ ለእይታ የበቃዉ “አኬልዳማ” ድራማችሁ ግን ለተፃፈ ህግ፤ ለአገር ባህልና ለራሳችሁ ሂሊና የማትገዙ ዛሬም በጫካ ዉስጥ ህግ የምትተዳደሩ ተራ ወንበዴዎች መሆናችሁን ነዉ የሚያሳየዉ።
ክቡር ጠ/ሚኒስትር. . . ለእኔ ወያኔና ትልቅ ከበሮ አንድ ናቸዉ። በተነኩ ቀጥር ‘እሪ’ እያሉ መጮህ ነዉ እንጂ የዉስጣቸዉ ባዶነት አይታያችዉም። “ለሞኝ ተረት ስትናገር ትርጉሙን አብረህ ተናገር” ይላል የአገሬ ሰዉ . . . ወይ ጉድ! ደሞ ምን ይሁን ብላችሁ ከባዶም ባዶ መሆናችሁን አጉልቶ የሚያሳየዉን የሰሞኑን ድራማ “አኬልዳማ” ብላችሁ የሰየማችሁት? “ሞኝን ያስተምሩታል አንጂ አያሰለጥኑትም” ሲባል አስከዛሬ በጆሮዬ ነበር የምሰማዉ። አመሰግናለሁ ክቡር ጠ/ሚኒስትር. .. ዘንድሮ በእርሶ አየሁት። ክቡር ጠ/ሚኒስትር. . . ስለ አኬልዳማ ማን እንደነገሮት ባላዉቅም የነገሮት ሰዉ ትርጉሙን አብሮ አልነገሮትምና ይህ ሰዉ የአገር ጠላት ነዉ። ሽብርተኛ ይሏል እንደዚህ አይነቱን የአገር መሪ የሚያደናግር አደናጋሪ ሰዉ ነዉ። ክቡር ጠ/ሚኒስትር. . . አኬልዳማ የክህደቶች ሁሉ ክህደት እና ደም ተቀላቅለዉ የሚገኙበት ቃል ነዉ። እርሶ ደግሞ ሁሌም በክህደትና በደም ማፍሰስ የሚታሙ ሰዉ ኖትና አኬልዳማ ሞትና ክህደት የተቀላቀለበት ቃል መሆኑን ቢያዉቁ ኖሮ እርግጠኛ ነኝ ይህንን ማንነትዎን በግልጽ የሚናገር ድራማ “አኬልዳማ” ብለዉ አይሰይሙትም ነበር። አኬልዳማ መነሻዉ ከመቆሚያዉ እንዲሁም መቸቱ ከገጸ ባህሪያቱ የተደበላለቁበትና የፈጠራ ምናቡ ያልተባ ሰዉ ሰዉ የማይሸት ድራማ ነዉ። ሆኖም ሞኝ የሆነ ሰዉ እንኳን የሚሰራዉ ስራ እሱ ራሱ ሲያዩት ያስቃልና የሞኞች የፈጠራ ዉጤት የሆነዉ አኬልዳማም አስቂኝ የሆኑ ቦታዎች አሉት። እኔን ያሳቀኝና ዛሬም ድረስ ጥርሴን አላስከድን እያለ የሚያስቸግረኝ ግን ድራማዉ መግቢያ ላይ “ይህንን ፕሮግራም ከ13 አመት በታች ያሉ ህፃናት እንዲመለከቱት አይመከርም” ተብሎ በአንስታይ ፆታ የተነበበዉ ማስጠንቀቂያ ነዉ። እርግጠኛ ነኝ እኚህ ሴት ያሰኛቸዉን የመናገር ነፃነት ቢኖራቸዉ ኖሮ
አኬልደማን አይቶ መለስን ያመነ
ሰማይ አንጋጥጦ ጉም የዘገነ” በለዉ ይመክሩን ነበር
ከዚህ ቀደም አቶ መለስ እራሳቸዉ “ህግ” በሆኑበት አገር ፍትህ ሊኖር አይችልም ሲባል እየሰማሁ ግራ ይገባኝ ነበር። “አኬልዳማ” ምስጋና ይግባዉ አሁን ግራ መጋባቱ ቀርቶ እዉነቱ ጥርት ብሎ ታየኝ። ይህንን ለማረጋገጥ ደግሞ ብዙ መጓዝ የሚያስፈልግ አይመስለኝም። በቅርቡ በአቶ መለስ ዜናዊ አቀነባባሪነት የተሰራዉን አኬልዳማን መመልከቱ ይበቃል። ለይስሙላ የተጎለተዉ የእትዮጵያ ፓርላማ የፀረ ሽብሩን ህግ አፀደቀዉ ይባል አንጂ ህጉን የጻፉትም ያፀደቁትም አቶ መለስ ዜናዊ ናቸዉ። በሌላ በኩል ደግሞ በቅርቡ በዚሀ ህግ መሠረት ተጠርጥረዉ የታሰሩትን ግለሰቦች የከሰሱትም አቶ መለስ ዜናዊ እራሳቸዉ ናቸዉ። ዛሬ የእነዚህ የተከሰሱት ሰዎች ጉዳይ በፍርድ ቤት እየታየ ነዉ ቢባልም አቶ መለስ በአኬልዳማ ድራማቸዉ ግለሰቦቹ ሽብርተኞች መሆናቸዉን ለአለም ህዝብ በማብሰር በእርግጥም ኢትዮጵያ ዉስጥ ህጉ እሳቸዉ መሆናቸዉን አስመስክረዋል።
ብዙ አገሮች ሽብርተኛ ብለዉ የሚጠሯቸዉ እንደ አልቃይዳና አቡ ሰያፍን የመሳሰሉ ደርጅቶች የራሳቸዉን እምነትና ፍላጎት በህዝብና በመንግስት ላይ በኃይል ለመጫን መሳሪያ ጭምር የሚጠቀሙ አክራሪ ኃይሎች ናቸዉ። ደግሞም ብዙ አገሮች አንድን ሰዉ ሽብርተኛ ብሎ ለመፈረጅና እስር ቤት ለመክተት ብዙ ግዜ ይፈጅባቸዋል፤ ምክንያቱም እነሱ ሽብርተኛ ብለዉ የሚፈርጁት ሰላማዊ ዜጎችን ለማጥቃት ሲያሴር በማስረጃ የደረሱበትን ሰዉ ብቻ ነዉ አንጂ እንደኛዎቹ “ማን አለብኝ” አምባገነኖች ሠላማዊ ዜጎችን በጅምላ አስረዉ የሌለ ማስረጃ አይሰበስቡም። ለምሳሌ አሜሪካኖችና እንግሊዞች እስካሁን ድረስ በቁጥጥር ስር ያደረጓቸዉንና የመጨረሻ እርምጃ የወሰዱባቸዉን ግለሰቦች ስንመለከት ግለሰቦቹ እራሰቸዉ አሸባሪዎች መሆናቸዉን በግልጽ የሚናገሩ ናቸዉ። ለምሳሌ ከሊል ሼክ መሐመድ፤ ዘካሪያስ ሙሳዊና ብዙዎቹ ተከታዮቻቸዉ የተከሰሱበትን የሽብር ወንጀል አይክዱም ጭራሽ ትክክለኛ እርምጃ ነዉ ብለዉ ይሟገታሉ እንጂ – በሌላ በኩል ደግሞ እነዚህ ሰዎች የሚኖሩት በየጫካዉና በየተራራዉ ስር ተደብቀዉ ነዉ። በኛ አገር ግን አነ አቶ መለስ ዜናዊ ሽብርተኛ ብለዉ የሚያስሩት አብረዋቸዉ ከተማ ዉስጥ የሚኖሩትንና ከብዕር ሌላ መሳሪያ የሌላቸዉን ጋዜጠኞች፤ የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች፤ የሲቪክ ማህበራት መሪዎችና ለህዝብ መብትና ነፃነት የሚሟገቱ ግለሰቦችን ነዉ።
ክቡር ጠ/ሚኒስትር እርሶ ዉሸታም እንደሆኑ ድፍን አበሻ ያዉቃል፤ የኢትዮጵያ ህዝብ ችግሩ የእርሶ ዉሸት አይደለም። የህዝባችን ትልቁ ችግር እርሶን በፍጹም ማመን አለመቻሉ ነዉ። የሚገርመዉ እርሶም ሽንጥዎን ገትረዉ የሚታገሉት ህዝብ እንዳያምንዎ ነዉ መሠለኝ የኢትዮጵያ ህዝብ አዋቂዉና ህጻኑ እንደ ነጭና ጥቁር ለይቶ የሚያዉቀዉን የ1984 ዓም ዕልቂት ዛሬ በአዲስ መልክ በቪድዮ አቀነባብረዉ ሊነግሩን ይሞክራሉ።
ክቡር ጠ/ሚኒስትር አኬልዳማ ላይ ያታየዉ የጭካኔ ስራ የተሰራዉ በእርሶና በጓደኞችዎ አይደለም እንዴ? እነዚያ ህፃናት በግፍ የታረዱትና አባትና እናቶቻቸዉ ገደል ዉስጥ የተወረወሩት በእርሶ ደጅአዝማችነት አይደለም አንዴ? ደግሞም ባይሆንስ? ያ ሁሉ አንኳን ለወገን ለባዳም የሚሰቀጥጥ ግፍ የተፈፀመዉ እርሶ ፈላጭ ቆራጭ በሆኑበት አገር ዉስጥ አይደለም አንዴ? ክቡር ሆይ እርሶ በድራማዉ ዉስጥ ያንን ግፍ ፈጽመዋል ብለዉ የሚያሟቸዉ ኃይሎች በወቅቱ ከእርሶ ጋር አልነበረም አንዴ ሠርግና ምላሽ የሚወጡት? ታዲያ ምንዉ ያኔ የደስ ደስ “ቺርስ” እየተባባላችሁ የጠጣችሁበት የፓለቲካ ዝቅጠት ዛሬ እነሱን ብቻ ሽብርተኛ ሊያሰኝ በቃ? ምነዉ ክቡር ጠ/ሚኒስትር? እንዳንናገር የእርሶ ጠመንጃ የለጎመዉኮ አፋችንን ነዉ እንጂ አይናችን ያያል ጭንቅላታችንም ያስባልኮ! አቤት የዉሸት ያለህ! ክቡር ጠ/ሚኒስትር ዉሸትዎ በቁመትዎ ልክ ነዉ አንዳልል የክቡርነትዎ ቁመት እንደኔ ዘለግ አይልምና ዉሸትዎን እንዳላሳንሰዉ ፈራሁ። እንደ ወላጅ እናቴም ነጭ ዉሸት እንዳልልዎት የእርሶ ዉሸት ከነጭም የነጣ ጉደኛ ዉሸት ነዉ። ክቡር ጠ/ሚኒስትር እዉነትም ለህፃናት የሚያስቡ ቢሆን ኖሮ ይህንን አገር የሚያጠፋ ዉሸት ነበር ታዳጊ ህፃናት እንዳይሰሙት ማድረግ የነበረቦት።
ክቡር ጠ/ሚኒስትር. . . “የሀሜት መጨረሸዉ ስጋት የዉሸት መጨረሻዉ ዉጋት” ይባላል። ምነዉ . . . የመጨረሻዎ ታዮት አንዴ? አይዞት ላይቀርልዎ ነገር አይቸኩሉ። እርሶ ባይታዮትም እኛ እናሳዮታለን። ደግሞም እንደ ይሁዳ በክደትዎ ተጸጽተዉ ከሆነ ይሁዳ ያደረገዉን ሁሉ ያድርጉ . . . ደግሞስ ምን የቀሮት ነገር አለ? ይሁዳ ጌታዉን አንደካደ እርሶም የሚመሩትን አገር ክድዋል። ይሁዳ ጌታዉን እንደሸጠ እርሶም የአገርዎን መሬት ለባዕዳን ሽጠዋል። የቀሮት ነገር ቢኖር እንደ ይሁዳ መፀፀት ብቻ ነዉ። ክቡር ጠ/ሚኒስትር ይሁዳ እራሱን የሰቀለዉ ይሀንን ሁሉ ክህደት መሸከም ተስኖት ነዉ፡ “አኬልዳማ” የሚባለዉ ቃልም ዛሬ በምናዉቀዉ መልኩ በታሪክ የተመዘገበዉ ይሁዳ እራሱን ከሰቀለ በኋላ ነዉ። ታዲያ ምነዉ እርሶ ዋናዉን ነገር ትተዉ ዘልለዉ አኬልዳማ ላይ ጉብ አሉ?
ክቡር . . . ከትላልቆቹ የአለማችን መሪዎች ከባራክ ኦባማ፤ ከአንገላ መርክልና ከኒኮላይ ሳርኮዚ ጋር በአንድ ጠረቤዛ ዙሪያ ቁጭ ብለዉ መክረዋል። የአፍሪቃን ህብረት በሊቀመንበርነት መርተዋል። በእርግጫም ይሁን በፍጥጫ ኢትዮጵያን ከሃያ አመት በላይ መርተዋል። ታዲያ መቼ ነዉ በጫካ ህግ ሳይሆን በህገ መንግስት የሚመሩት? መቼ ነዉ ቂም በቀል እንደወጠረዉ ጎጠኛ ሳይሆን እንደ አስተዋይ የአገር መሪ ማሰብ የሚጀምሩት? መቼ ነዉ የፍርሀትና የጥላቻ ድራማ ሳይሆን የፍቅርና የተስፋ ሕይወት የሚያሳዩን?
ክቡር ጠ/ሚኒስትር. . . ከላይ መግቢያዬ ላይ አንደነገርኮት ዕድሜ ለእርሶ የኢትዮጵያን ቴሌቪዥን መመለክት ከተዉኩ ህዳር ሚካኤል ስድሰት አመት አለፈኝ። የሚገርሞት እርሶን በተለያዩ ገፀ ባህሪያት ከፋፍሎ የሚያሳየዉን የአኬልዳማ ድራማ የተመለከትኩት ኢቲቪ ላይ ሳይሆን “ድሬ ቲዩብ” ላይ ነዉ። አኬልዳማ ድሮም የማዉቀዉን የእርሶን ዉሸት፤ፍርሃትና ጭካኔ አረጋገጠልኝ አንጂ አዲስ ነገር አላሳየኝም። ክቡር ጠ/ሚኒስትር. . . በመጨረሻ ላም እንደሚወድዱ ስለማዉቅ እስኪ ስለ ላም ነግሬዎት ላብቃ…… ነጭ ላም ገዝተዉ ላሜ ጥቁር ናት ብለዉ ቢናገሩ ለራስዎ ይቀልሉ ይሆናል አንጂ የገዙትን ላም ያላየ ሁሉ ሊያምኖት ይችላል፤ ሆኖም የላሚቱ ወተት ጥቁር ነዉ ብለዉ ቢናገሩ ግን እንደዚህ አይነቱን ቅጥፈት ለማረጋገጥ ወተቱን መመልከት ያለብን አይመስለንም። ልብ ይበሉ እንግዲህ የእርስዎ ቅጥ ያጣ እብሪትና ቂልነት ጎልቶ የሚታየዉ እዚህ ላይ ነዉ ምክንያቱም ህዝብ የእርሶን ዉሸት ሰምቶ ዝም ባለ ቁጥር የተቀበለዉ ይመስሎታል። በቅርቡ ለእይታ የበቃዉ አኬልዳማ ድራማም የዚሁ እብሪትና ቂልነት ዉጤት ነዉ።
በሉ ለዛሬዉ በዚህ ይብቃኝ … ኑረዲን ነኝ ከመርካቶ