የሐውልቱ ሥር ቁማርተኞች
(ደጀ ሰላም፤ ኦገስት 8/2010) — የፓትርያርኩና የማፊያው ቡድን “ስውር ፀሐፊ” (Ghost Writer) ዘሪሁን ሙላቱ ስለ ፓትርያርኩ ሐውልትና ተያያዥ ጉዳዮች ባለ 50 ገጽ መጽሐፍ አወጣ፤ እነ በጋሻው ደሳለኝና ኤልዛቤል የምትባለው ወ/ሮ እጅጋየሁ ተጠቅሰውበታል። ዲያቆን ሲባል ቆይቶ በቅርቡ ሊቀ ትጉሃን የሚል የማዕረግ ስም የደረበው Ghost Writer ዘሪሁን ሙላቱ ጊዜውን በቶሎ በማጥናት እና የፓትርያርኩ ሐውልት ብዙ ተቃውሞ እንደበዛበት ሲመለከት፣ የሐውልቱ ተቃዋሚዎች ያሉትን በመሰብሰብና መጽሐፍ አድርጎ በማሳተም ሲያሳዝነው የሰነበተውን ምእመን አሁን ደግሞ ገንዘቡን ሊበላው ይህንን ፓምፍሌት (መጽሐፍ ለማለት ይከብዳል) አሳትሟል። መታሰቢያነቱንም በቅርቡ ከዚህ ዓለም በሞት ለተለዩት ለብፁዕ አቡነ መልከ ጼዴቅ በማድረግ መጽሐፉ ተቀባይነት እንዲያገኝ ለማድረግ ሞክሯል። ርእሱን ደግሞ በቅርቡ እኛም ካወጣነው (በአዲስ አበባ በጋዜጣ ከወጣ) አንድ ጽሑፍ ላይ የወሰደው ነው።
በዚህ መጽሐፍ ስማቸው የተጠቀሱት ሰዎች በርግጥም ቤተ ክርስቲያንን በሚጎዳ ሥራ ላይ የተሰማሩ መሆናቸውን በተደጋጋሚ መዘገባችን ይታወቃል። ነገር ግን ሰዎቹ ስሕተተኛ መሆናቸውን መጥቀሳችን አሁን ዘሪሁን የጻፈውን አስነዋሪ ጽሑፍ እንድንቀበለው አያደርገንም። ብዙ ጊዜ እንዳልነው “ለገንዘብ ብሎ ስለ እግዚአብሔር የሚሰብክ፣ ገንዘብ ከተሰጠው ለሰይጣንም መስበኩ የተረጋገጠ ነው። ዘሪሁን በዚህ ጽሑፉ የሚያዋርዳቸው ሰዎች በዓላማም በግብ አንድ የሆኑትን ሰዎች ነው።
ዘሪሁን “የሚታወቅባቸው ሥራዎቹ” በሙሉ የሰዎችን ስም የሚያንቋሽሹ ሲሆኑ ከነዚህም ውስጥ ሁለቱ ዋነኛ መጽሐፎቹ ለዲ/ን በጋሻው “የመስቀሉ ሥር ቁማርተኞች” መልስ የሰጠበት “የስድብ አፍ” እና ብፁዕ አቡነ ሳሙኤልን “የሚያዋርድ” ስድብ ያሳተመበት መጽሐፉ ናቸው። የመጀመሪያውን መጽሐፉን በጻፈበት ወቅት ቅ/ፓትርያርኩ 60 ሺህ ብር ጥሬ ገንዘብ እንደሰጡት ውስጥ አዋቂዎች ይናገራሉ። መጽሐፉንም እያንዳንዱ ቤተ ክርስቲያን በግድ እየወሰደ እንዲያከፋፍል፣ ካህናቱም በነፍስ ወከፍ እያንዳንዳቸው አምስት አምስት እንዲወስዱና እንዲሸጡ፣ ገንዘቡ ግን ከደሞዛቸው በግድ እንዲቆረጥ ተደርጎ ነበር። ይህ ግለሰብ ባለፈው ሐምሌ በተደረገው ሽልማት ላይ ስለዚሁ ስውር ሥራው (ከነ ዲ/ን በጋሻው ጋር) ከቅዱስ ፓትርያርኩ እጅ በአደባባይ ሽልማት ተበርክቶት ነበር።
የመጽሐፉ ርዕስ፦ የሐውልቱ ሥር ቁማርተኞች፣
ዋጋው፦ 15 ብር
የገጽ ብዛት፦ 50 ብቻ
ደራሲ፦ ፈታሒ በጽድቅ (የብዕር ስም)፣
መታሰቢያነቱ፦ ለአቡነ መልከ ጼዴቅ
ማተሚያ ቤት፦ አልተጠቀሰም፣
ምእመናን እንዲህ ዓይነቱን ርካሽ መጽሐፍ እየገዙ አጽራረ ቤተ ክርስቲያንን በተዘዋዋሪ እንዳይጠቅሙ እናስታውሳለን።