ኢትዮጵያውያን ስደተኞች በየመን እና ሳውዲ ድንበር ላይ እየተንከራተቱ መሆኑ ታወቀ
ሁለት ሺህ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች በየመን እና ሳውዲ አረቢያ ድንበር ላይ እየተካሄደ ባለው ግጭት መካከል አጣብቂኝ ውስጥ ገብተው እየተንከራተቱ መሆኑን አፍሪክጄት የተባለው የዜና ድረ-ገጽ ዘግቧል። ስደተኞቹ ምግብ፣ ውሃና መጠለያ እንደሌላቸው እና በአስከፊ ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኙም ዘገባው አመልክቷል።
በአንድ ጎን በሁዚ ሸማቂዎች እና በየመን መንግስት መካከል የሚደረገው ግጭት፣ በሌላ ጎን ደግሞ የሳውዲ አረቢያ መንግስት ድንበሩን ለመቆጣጠር የሚያደርገው ጥረት በመቶ ሺሆች የሚቆጠሩ ስደተኞችን በአስከፊ አጣብቂኝ ውስጥ እንደጣላቸው ለማወቅ ተችሏል።
የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽን ኢትዮጵያውያኑ ወደአገራቸው የሚመለሱበትን መንገድ ከሌሎች ድርጅቶች ጋር በመሆን እያቀናጀ እንዳለ ዘገባው የጠቀሰ ሲሆን፤ ከተመላሾቹ ውስጥ የፖለቲካ ስደተኞች መኖር አለመኖራቸው አልታወቀም።
በየአመቱ በአስር ሺሆች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን በፖለቲካ እና ኢኮኖሚ ምክንያት አገራቸውን እየጣሉ እንደሚሰደዱ ይታወቃል። በርካቶች በተለያዩ አገራት ለእስር ሲዳረጉ፤ ቁጥራቸው የማይታወቅ የረዥም እግር ጉዞን ወይም በብረት ኮንቴነር የመጓጓዝን ሙቀት መቋቋም እየተሳናቸው ለሞት ይዳረጋሉ።