በጋምቤላ የመሬት ቅርምት ተዋናይ የሆነው አንድ የህንድ ኩባንያ ዜጎች አልተፈናቀሉም ሲል የሰጠው መረጃ ሃሰት መሆኑ ተጋለጠ
የጋራ ንቅናቄ ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የተባለው የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅት ባወጣው መግለጫ፣ የህንዱ ካራቱሪ በጋምቤላ የተፈናቀሉ ዜጎች ስላለመኖራቸው የተናገረው ሃሰት መሆኑን አጋልጧል።
ካራቱሪ የኢትዮጵያን መሬት እየተቀራመቱ ካሉት የባዳ አገር የንግድ ድርጅቶች እና ግለሰቦች ውስጥ አንዱ መሆኑን እና ቀድሞ ከተሰጠው የአበባ እርሻ በተጨማሪ በአሁኑ ሰዓት በጋምቤላ ክልል ሰባት ሺህ ሰባት መቶ ጋሻ መሬት ተሰጥቶት በመንቀሳቀስ ላይ እንዳለ መዘገባችን ይታወሳል። በዚህ ምክንያትም በጋምቤላ ክልል ገበሬዎች እንዲፈናቀሉ እየተደረጉ መሆኑን የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች የገለጹ ሲሆን፤ የግንቦት 7 ድምጽ ዘጋቢም ከአዲስ አበባ ባስተላለፈው መረጃ ይህንኑ አረጋግጧል።
ይሁን እንጂ የካራቱሪ ስራ አስኪያጅ ለመገናኛ ብዙሃን በሰጠው መግለጫ፤ በእርሻ መሬቱ አካባቢ ብዙ ሰዎች አለመኖራቸውን፤ ያለው አንድ መንደር ብቻ መሆኑን እና ነዋሪዎቹ እንዲፈናቀሉ ድርጅቱ አለመፈለጉን፤ በተጨማሪም ለዚህ መንደር ነዋሪዎች እርዳታ እያደረገ መሆኑን፤ በጥቅሉ የተፈናቀሉ ዜጎች አለመኖራቸውን ገልጿል።
የጋራ ንቅናቄ ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ ባወጣው መግለጫ፣ በእርሻው ምክንያት ተጽእኖ ያደረባቸው በርካታ መንደሮች መሆናቸውን ገልጾ፤ እነዚህም ወይ በራሳቸው ፈቃድ አካባቢውን ለቀው እንዲወጡ፤ አለበለዚያ በግዳጅ ወደ ሰፈራ ጣቢያ እንደሚወሰዱ እንደተነገራቸው መስክሯል። የመንደሮቹ ነዋሪዎች እስካሁን በገዛ ፈቃዳቸው ለመውጣት ፈቃደኞች አልሆኑም ያለው መግለጫ፤ ነገር ግን በአካባቢው ያለው የወያኔ ጦር ጥቃት ይፈጽምብናል የሚል ፍርሃት እንዳለባቸው አስታውቋል።
የዘረኛው እና አምባገነናዊው አገዛዝ ጦር ከበርካታ አመታት በፊት በአካባቢው ከፍተኛ ጭፍጨፋ መፈጸሙ የሚታወስ ሲሆን፤ አለማቀፍ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች የዘር ማጥፋት ወንጀል መፈጸሙን እንደመሰከሩ ይታወቃል።
መግለጫው በተጨማሪ፥ ለአካባቢው ነዋሪዎች የተደረገ ምንም እርዳታ እንደሌለም አስረድቷል።
በርካታ የህንድ ነጋዴዎች የገዛ አገራቸው ዜጎች የንብረት ባለቤትነት መብታቸውን በስራ ላይ በማዋል መሬት አልለቅ እያሉ ሲያስቸግሯቸው ወደ አፍሪካ መፍለስ መጀመራቸውን ቢዝነስ ዊክ የተባለውን የመረጃ አውታር ጠቅሰን መዘገባችን ይታወሳል።