“ የአገራችን መሠረታዊ ችግሮች በፕሮፖጋንዳ ጋጋታና በባዶ መፈክር፣ እንዲሁም በአልባሌ ትወና አይፈታም” መድረክ
የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲዊ አንድነት መድረክ በቅርቡ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ድርጅት የተላለፈው ‹‹አኬልዳማ›› የተሰኘው ፕሮግራም ‹‹ድራማ›› መሆኑንና የመድረክ አባል ድርጅቶችን ድራማው በፍፁም አይከፋፍላቸውም አለ፡፡ መድረክ ትናንት ‹‹በፈጠራ የፖለቲካ ተውኔት ተቃዋሚዎችን መክሰስና ሕዝቡን ማሸበር ይቁም›› በሚል ርዕስ ባወጣው መግለጫ፣ ኢሕአዴግ “አኬልዳማ” በሚል የፈጠረው ድራማ “የመድረክ አባላት እየተከፋፈሉ ነው” የሚል መልክት ለማስተላለፍ አቅዷል ይላል፡፡
‹‹ለመድረክና ለአባል ድርጅቶቹ ህልውና ስጋት እየሆነ ያለው ኢሕአዴግ ራሱ መሆኑን ሕዝባችን ይገነዘበዋል ብለን እናምናለን፡፡ የሩቁን እንኳ ብንተወው ላለፉት አሥር ወራት የኢሕአዴግ የፕሮፓጋንዳ ጥቃት ዒላማ ያልሆነ የመድረክ አባል የለም፤›› ሲል የመድረክ መግለጫ ያትታል፡፡
መድረክ ለዚህ ማስረጃውን ሲያቀርብ የመድረክ አባል ድርጅቶች የሆኑ የኦሮሞ አባል ድርጅቶች አባላት በግፍ ታስረዋል፣ መሪዎቻቸውም በአኬልዳማ ቴአትር ውስጥ ተካተዋል፡፡ በዓረና አባላት ላይ በተከታታይ የተፈጸሙት የእሥርና የወከባ ዘመቻዎች የሚታወቁ ናቸው፡፡ የአንድነት ፓርቲ አባላት ለአሰቃቂ እስር ተዳርገዋል፡፡ የአንድነት አባላት ያልሆኑ ሰዎች “ወንጀለኛ የአንድነት አባላት›› በማለት ሕዝቡን ለማወናበድ ጥረት ተደርጓል ይላል፡፡
“እኛ የገዛ ሕዝባችንን እልቂትና ደም መፍሰስ በጭራሽ አንመኝም” የሚለው የመድረክ መግለጫ፣ ‹‹አኬልዳማ›› የተሰኘው ድራማ የሕዝቡን ሰቆቃና ዋይታ ለመደበቅና ያልሆነ አቅጣጫ ለመፍጠር ያደረገው ሙከራ ነው ሲል የቴሌቪዥኑን ፕሮግራም ይኮንነዋል፡፡
መድረክ አያይዞ የአገሪቱ ችግሮች በአልባሌ ትወና እንደማይፈታ ታውቆ፣ በአስቸኳይ አገሪቱንና ሕዝቦቿን ወደ ብሔራዊ መግባባት መውሰድ እንደሚገባ ገልጿል፡፡
“በአኬልዳማ ድራማ የመድረክ አባል ድርጅቶች የአገሪቱን ገጽታ ለማበላሸት፣ ከሻዕቢያ ጋር በማቆራኘት አፍቃሪ ኤርትራ ናቸው የሚል ተረት ለማስነገርም ሞክሯል፡፡ በመድረክ እምነት የአገራችን ገጽታ እንዲበላሽና ሕዝቦቿ በቀጣይ ስጋትና ሽብር ውስጥ እንዲኖሩ እያደረገ ያለው ኢሕአዴግ ራሱ መሆኑን በተደጋጋሚ ገልጸናል፡፡ ይህንን ስንልም ከባዶ ነገር ተነስተን የኢሕአዴግን ስም ለማጥፋት የተወጠነ ነገር ስላይደለ፣ የአገራችንን ገጽታ እያበላሹ ያሉትንና የሕዝቡንም የስጋትና የሰቆቃ ምንጭ የሆኑትን ነገሮች አንስተን ኢሕአዴግን የተወሰኑ ጥያቄዎችን መጠየቅ እንወዳለን፤” ብሏል፡፡
መድረክ አሥር ያህል መጠይቆችን ያቀረበ ሲሆን፣ ከእነዚህ መካከል ኢሕአዴግ ነፃና ፍትሐዊ ምርጫ አለማካሄዱን፣ ዜጎችን በግፍ ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ማሰሩን፣ የዕርዳታ እህልና ማዳበሪያን በፖለቲካ ታማኝነት መስጠቱን፣ የመንግሥት አገልግሎቶችን በእኩልነትና በፍትሐዊነት ስለማቅረቡ ማስረጃ ማቅረብ እንደማይችል፣ ወዘተ ይዘረዝራል፡፡
“የእኛ ዓላማ በኢሕአዴግ አምባገነናዊነትና ማንአለብኝነት የተነሳ በአገራችን የተከሰተው እልቂትና ቆይታ እንዲገታ መታገል ነው፤” የሚለው መድረክ፣ “በዚህ አጋጣሚ የአገራችን መሠረታዊ ችግሮች በፕሮፖጋንዳ ጋጋታና በባዶ መፈክር፣ እንዲሁም በአልባሌ ትወና እንደማይፈታ ታውቆ፣ በአስቸኳይ አገሪቷንና ሕዝቦቿን ወደ ብሔራዊ መግባባት እንድንወስዳት በቁርጠኝነት መሥራት እንደሆነ እናምናለን፤” ብሏል፡፡
የዘላቂው ሰላምና ብልጽግና መሠረት “የኢኬልዳማ” መሰል ቴአትር ሳይሆን፣ በኢትዮጵያ ሕዝቦች ይሁንታ የሚፈጠር ዲሞክራሲያዊ የፖለቲካ ሥርዓት መሆኑን ለአፍታ እንኳ እንዳይረሳ ለማሳሰብ እንደሚፈልግ መድረክ በመግለጫው አስታውቋል፡፡