በሕገወጥ መንገድ ከአገር የሚወጣው ከፍተኛ ገንዘብ የትልቅ ወንጀል ማሳያ መሆኑ ተገለጸ
ሕገወጥ በሆነ መንገድ ከኢትዮጵያ የሚወጣው ከፍተኛ ገንዘብ በፋይናንስ ዘርፍ ውስጥ ዋነኛውና ትልቁ ወንጀል መሆኑን፣ ስማቸው እንዳይገለጽ የፈለጉ የፋይናንስ ባለሙያ ለሪፖርተር ገለጹ፡፡ ባለሙያው በጉዳዩ ላይ አስተያየታቸውን የሰጡት ባለፈው ሳምንት የአንድ ዓለም አቀፍ ተቋም ጥናት ከኢትዮጵያ በሕገወጥ መንገድ እ.ኤ.አ. በ2009 ብቻ 3.26 ቢሊዮን ዶላር መውጣቱን ከገለጸ በኋላ ነው፡፡
በዚህ ወር በይፋ ይወጣል የተባለውንና ግሎባል ፋይናንሻል ኢንተግሪቲ በተባለው ዓለም አቀፍ ድርጅት የተጠናከረውን ጥናት ጠቅሶ የወጣው ሪፖርት፣ ከኢትዮጵያ በሕገወጥ መንገድ እ.ኤ.አ. ከ2000 እስከ 2009 ባሉት አሥር ዓመታት ውስጥ፣ 11.7 ቢሊዮን ዶላር በሕገወጥ መንገድ ማጣቷን ያብራራል፡፡
በሪፖርቱ እንደተመለከተው የዓመት የነፍስ ወከፍ ገቢዋ ከ365 ዶላር ያልዘለለው ኢትዮጵያ፣ በሕገወጥ መንገድ ከሚወጣ ከፍተኛ ገንዘብ ዋነኛዋ ተጎጂ ከሆኑ አገሮች መካከል አንዷ እንደሚያደርጋት ያብራራል፡፡
ወደ 166 ታዳጊ አገሮችን የሚያካትተውና በዚህ ወር ይፋ ይደረጋል ተብሎ የሚጠበቀው ጥናት፣ ለዚህ በሕገወጥ መንገድ ከታዳጊ አገሮች ለሚወጣ ገንዘብ ዋነኛው ምክንያት ከሙስና ጋር እንደሚያያዝ፣ ቀሪው ደግሞ ከአገሮች የገቢና የወጪ ንግድ ውስጥ በሚፈጸም ሕገወጥ አሠራር መሆኑን ይገልጻል፡፡
ይሁንና በተባበሩት መንግሥት የንግድና ልማት ጉባዔ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ባለሙያ የሆኑት አቶ ታፈረ ተስፋቸው፣ ከታዳጊ አገሮች ሕገወጥ በሆነ መንገድ የሚወጣው ገንዘብ ከ70 እስከ 75 በመቶ ከገቢና ወጪ ንግድ ሕገወጥ የሆነ የደረሰኝ አሠራር መሆኑን፣ ለዚህም ቀደም ሲል በአብዛኛው የሚወቀሱት ትላልቅ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎችና አንዳንድ የመንግሥት ኃላፊነት የተሰጣቸው ግለሰቦች መሆናቸውን ለሪፖርተር አብራርተዋል፡፡
ሪፖርቱ ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ. በ2009 ብቻ በሕገወጥ መንገድ ከ3.26 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገንዘብ ማጣቷን ሲገልጽ፣ ይህም አገሪቱ እ.ኤ.አ. በ2009 ከወጪ ንግድ ካገኘችው ከሁለት ቢሊዮን ዶላር በእጅጉ የሚልቅ ነው፡፡
“ይፋ ይሆናል ተብሎ በሚጠበቀው ሪፖርት እ.ኤ.አ. በ2009 በሕገወጥ መንገድ ከኢትዮጵያ ወጥቷል የተባለው ገንዘብ እንዴት እንደተሰላ ባላውቅም፣ መጠኑ በጣም ብዙ ነው፤” ያሉት የኢኮኖሚ ባለሙያውና በተባበሩት መንግሥታት የንግድና ልማት ጉባዔ ከፍተኛ ባለሥልጣን ከሆኑት በጣት ከሚቆጠሩ አፍሪካውያን አንዱ የሆኑት አቶ ታፈረ፣ ከኢትዮጵያ ከ70 እስከ 75 በመቶ የሚሆነው በሕገወጥ መንገድ የሚመጣው ገንዘብ ከወጪና ገቢ ንግድ ጋር የተያያዘ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ በገቢና በወጪ ንግድ ደረሠኞች በሕገወጥ መንገድ በማዘጋጀት አንዳንድ ላኪዎችና አስመጪዎች የማጭበርበር ተግባር እንደሚፈጽሙ አስረድተዋል፡፡
እንደዚህ ዓይነት ሪፖርት ወይም ጥናት በሚካሄድበት ጊዜ ቁጥሮችን የማስሊያው ዘዴ በግምት ላይ የተመረኮዘ በመሆኑ፣ የሚወጡት ቁጥሮች ሙሉ በሙሉ ትክክል ሊሆኑ የማይችሉበት ሁኔታ መኖሩንም ባለሙያው ጠቅሰዋል፡፡
ከኢትዮጵያ በሕገወጥ መንገድ ይወጣል የተባለው ገንዘብ ዋነኛ መስመሩ ከወጪና ገቢ ንግድ ጋር የተያያዘ ሲሆን፣ ከትክክለኛው ባነሰ ዋጋ የኤክስፖርት ገቢውን በደረሰኝ በመግለጽ፣ ገቢ የተደረገውን የዕቃ ዋጋ ደግሞ ከዋጋው በላይ ከፍ አድርጎ ደረሰኝ በማዘጀት ተገቢ ያልሆነ አሠራር መሆኑንም አቶ ታፈረ አብራርተዋል፡፡
ይኼው ሪፖርት በፌዴራል ሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን እጅም መግባቱ የገለጹት የኮሚሽኑ የሥራ ኃላፊዎች፣ ሪፖርቱ ለኮሚሽኑ ዓይን ገላጭ ሊሆን እንደሚችልም ገልጸዋል፡፡
ሕገወጥ በሆነ መንገድ ከታዳጊ አገሮች የሚወጣው ከፍተኛ ገንዘብ የአገሮቹን ዕድገት የሚፈታተን እንደሆነ የሚያብራራው ሪፖርቱ፣ ይህንንም ለማስወገድ ዓለም አቀፋዊና ፈጣን የሆነ የታክስ መረጃ ልውውጥ መረብ መዘርጋት አስፈላጊ መሆኑን መክሯል፡፡
ይህንን ሪፖርት አስመልክቶ የብሔራዊ ባንክና ሌሎች ይመላከታቸዋል የተባሉ የመንግሥት መሥርያ ቤቶች ኃላፊዎች ለማነጋገር የተደረገው ጥረት ሳይሳካ ቀርቷል፡፡