ኳሷ በዲያስፖራው እጅ ናት – ዋልተንጉስ ዳርጌ

መግቢያ

በመፅሐፈ ሳሙኤል ቀዳማዊ፣ በሰባተኛው ምዕራፍ፣ በሁለተኛው ቁጥር ላይ እንዲህ የሚል አርፍተ ነገር ተፅፏል፣ “ታቦቱም በቂርያትይዓሪም ከተቀመጠበት ቀን ጀምሮ ወራቱ ረዘመ፣ ሀያ ዓመትም ሆነ፤ የእስራኤልም ቤት ሁሉ አዝኖ እግዚአብሔርን ተከተለ፡፡”

ከጥቂት ምዕራፋት በፊት ታቦቱ የእስራኤል ክብር፣ በፍልስጥኤማውያኑ እስከተማረከበት ጊዜ ድረስ ደግሞ ማደሪያው በሴሎ እንደነበር እናነባለን፡፡ ይህ የህልውናቸው እና የአንድነታቸው ማዕከል ታዲያ ከማደሪያው እንደዋዛ ወጥቶ፣ ከዛሬ ነገ ይመለሳል ሲባል፣ ሀያ አመታት አለፉ፡፡ የሚገርመው ነገር ግን፣ ህዝቡ ያለ ታቦቱ ደስ ብሎት ማደር አለመልመዱ ነው፡፡ ከሀያ አመታት በኋላ እንኳ ኑሯቸው የሀዘን ነበር፡፡

ይህ የብዙዎቻችንን ኢትዮጵያውያን ህይወት የሚያንጸባርቅ ይመስለኛል፡፡ የምንበዛው፣ ለሃያ አመታትና ምናልባትም ከዛም ለሚበልጡ ጊዜያት በሀዘን ኖረናል፡፡ በሀገራችን ፍትህ በመዛባቱ፣ አንድነታችን ጥያቄ ላይ በመውደቁ፣ ሀገሪቱን በተመለከተ በሚወሰኑ ቁልፍ ውሳኔዎች ላይ የኛ አስተያየት ባለመጠየቁ፣ ሰዎች ሲሾሙም ይሁን ሲሻሩ ለምን እንደሆነ ካለማወቃችን የተነሳ ግራ በመጋባታችን ምክንያት፡፡ መፍትሔ ቢሆን ብለን አያሌ ስብሰባዎችን፣ ኮንፍረንሶችን፣ ወርክሾፖችን፣ ፎረሞችን፣ ወዘተርፈ፣ ተካፍለናል፤ በቁጥር ልናስታውሳቸው የማንችላቸውን ፅሁፎች አንብበናል፤ ሰላማዊ ሰልፎች ተጠርተው፣ አንዳንዴ በብዙ፣ የሚበዙቱን ጊዜያት ግን በጥቂቱ፣ እየተንጠባጠብን ወጥተናል፡፡ ከኛ መካከል የበረቱቱ ደግሞ ሀሳባቸውን በፅሁፍ፣ በመጽሐፍት መልክ አሳትመው ጨለማውን ለመተርጎም ሞክረዋል፡፡

እውነቱን ለመናገር ያመጣነው ለውጥ ከጊዜው እርዝመትና ከልባችን ስብራት አንፃር ሲታይ፣ በንፋስ እንደተወሰደ ምኞት ነው፡፡

አሁን፣ ውጤት የማጣታችንን ምክንያት መዘርዘርና መተንተኑ ብዙም የሚያመጣው ፋይዳ ባይኖርም፣ ወደፊት ለመቀጠል ከተፈለገ ግን የግድ አስቸጋሪ መሰናክሎችን ፈጥነን ማለፍ ይኖርብናል፡፡

የችግሩ መፍትሔ አሐዱው፣ ችግሩ እንዳለ ማመኑ ላይ ነው

በሒሳብ ህግ፣ እስካሁን ያሰላኹት ስሌት የተሳሳተ እንደኆነ ከገባኝ፣ ወደኋላ ተመልሼ ስህተቱን ማረም ይኖርብኛል፡፡ ሌላ አማራጭ የለኝም፡፡ ከችግሮቻችን ዋናው፣ የምንበዛው በምንም ሀሳብ አንድ ልንሆን አለመቻላችን ነው፡፡ ሌላውን ባንቆጥር፣ ለባለፉት ሃያ አመታት፣ የሀገራችንን ፖለቲካ በተመለከተ አንድ መሆን አልቻልንም፡፡ የዚህ ችግር ታላቅ ምጸት ደግሞ፣ እንዲሁ የምንበዛውን የሀገራችን አንድነት ጉዳይ በተመሳሳይ ጥልቀት መቀስቀሱ ነው፡፡ ለምን ከዚህ የጋራ ስሜት ልንነሳ እንዳልቻልን አላውቅም፡፡ አሁንም ጊዜው ገና ቀን ሳለ ልንነቃ ይገባናል፣ የተረፈውን ለማዳን፡፡
ይህን በተመለከተ ደግሞ፣ የዛሬ አስር አመታት አካባቢ፣ ጠቅላይ ምኒስትሩ በስድስት ኪሎ ቅጥር ጊቢ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህራንን ሰብስበው ባነጋገሩበት ወቅት፣ አንድ መምህር እንዲህ ብለዋቸው ነበር፤ “ኳሱ በእጅዎ ነው፡፡፡” ይህ አባባል እውነትነት ያለው ቢመስልም፣ በመሰረቱ ትክክል አይደለም፡፡ በስልጣን የተያዘ ማንም ሰው የፈቃድ ነጻነት የለውም፡፡ ጁሊየስ ቄሳር ነጻ አልነበረም፡፡ ናፖሊዮን ነጻ አልነበረም፡፡ ሂትለር ነጻ አልነበረም፡፡ ቶኒ ብሌር ነጻ አልነበረም፣ በምን ያህል ሙግት፣መቃቃር፣ እና ምሬት ስልጣን እንደለቀቀ ሁላችንም እናውቃለን፡፡ የምዕራቡ አገር ሰዎች የሚመሰገኑት መሪዎቻቸው ስልጣንን በፈቃዳቸው በመልቀቃቸው ሳይሆን፣ መሪዎቻቸውን ለህግና ለመረጣቸው ህዝብ ተጠያቂ ማድረጋቸው ነው፡፡

አሁን አገራችን ባለችበት ሁኔታ፣ ኳሷ በአንድ ወገን እጅ እንደሆነች ማሰብ ከተደፈረ፣ ኳሷ በዳያስፖራው እጅ ናት ብል የተሳሳትኩ አይመስለኝም፡፡ ዳያስፖራው ነው ነፃነቱ፣ ጊዜው፣ ሚዲያው፣ እና ገንዘቡ ያለው፡፡ ዳያስፖራው ከሱ እጅግ በሚበልጥ ጉዳይ ላይ ዛሬ መስማማት ካቃተውና የልቡን መስጠት ካልቻለ እንዴት ስለሀገር አንድነት ለማውራትም ሆነ ሌሎችን በአንድነት ጉዳይ ላይ ለመክሰስ የሞራል ብቃት ይኖዋል? ዳያስፖራው ከሀገር ውጭ ሆኖ የሚያመጣው ለውጥ በእርግጥ ውስን ነው ብለን የምንከራከር ካለን፣ በመጀመሪያ ያንኑ ትንሽ ለውጥ አምጥተን ስለቀረው መወያየት ይኖርብናል፡፡

ካለን መጀመር ይኖርብናል

ይሄ በምርምር አለም ለቆዩት ግልጽ ነው፡፡ አዲስ ነገር እፈጥራለሁ ብሎ ለሚከራከረው ብዙም ታዳሚ አይኖረውም፡፡ ወደድንም ጠላንም፣ በስልጣን ላይ ካለው መንግስት ጋር መደራደር ይኖርብናል፡፡ ተሞክሮዎች በደቡብ አፍሪካ፣ በዝምባቡዌ፣ በኬኒያ፣ ወዘተ፣የሚያሳዩት ይህንኑ ነው፡፡ ይሔ ሐሳብ ሊጭር የሚችለው ቁጣና የቁጣውም ፍትኸኝነት ይገባኛል፡፡ ሆኖም ግን እውነታው ይህ ነው፣ እኔም በሀሳብ ለበሰሉት ነው መናገር የምፈልገው፡፡ በስልጣን ላይ ያለው መንግስት በትግራይ ክልል ድጋፍ የለውም ብለን ብንከራከር አውነተኞች አንሆንም፡፡ ይህም ሲባል ግን የቅንነት ድርድር ይቻላል ማለት አይደለም፡፡ ሆኖም አያውቅም፡፡ የየትኛውም የአለም ክፍል ተሞክሮ የሚያሳየው ወደ ድርድር ስትገባ፣ በድርድሩ ላይ የሚኖርህ ተሰሚነት የሚመዘነው ይዘኸው በመጣኸው ሀይል ልክ ነው፡፡ ባለፉት አመታት፣ በሀገር ውስጥ ያሉት ተቃዋሚዎች ተመጣጣኝ ሃይል ስለሌላቸው ብቻ ሳይሆን፣ በስልጣን ላይ ያለው መንግስት ተጨማሪ ሀይል ከእንግሊዝ፣ ከአሜሪካ፣ ከቻይናና ከመሳሰሉት መንግስታት በማከማቸቱ፣ እስካሁን ምንም አይነት እውነተኛ ድርድር ሊደረግ አልተቻለም፡፡ አሁን የቀረን እኛ ነን፡፡ ዲያስፖራው፡፡ ከእኛ የምንበዛው በአንድ ድምጽ ብንሰለፍ፣ በአንድ ልብ፣ ቀን ወስደን፣ አስበንበት፣ በአመት አንዴ አደባባይ ብንወጣ፣ ብዙ ሀይል ልናደርግ እንችላለን፡፡ ይሔ ደግሞ ለእውነተኛ ድርድር መሰረት ይሆናል፡፡ ይሄን ማድረግ እስካልቻልን ድረስ ግን ፀሐይ አትወጣም፡፡ እውነታው ይሔው ነው፡፡

ጥላችን ከአብዮተኝነት ጋር ከሆነ፣ እኛም አብዮተኝነትን መተው ይኖርብናል

ብዙ ጊዜ የአንድ አብዮት አስቀያሚ ገጽታ አብዮቱን የፀነሰው አላማ ሳይሆን ወደ አላማው የሚወስዱት መንገዶች፣ መሪዎቹን ጨምሮ፣ በቅጡ ያልተፈተሹ መሆናቸው ነው፡፡ ስለዚህም የጎደለውን ለመሙላት፣ እድል እንደኮፍያ ከአናቷ በላይ ያዋለቻቸው መሪዎች፣ የሰሚዎቻቸውን ስሜታዊነት ይበዘብዛሉ፤ ከገሀዱ አለም ጋር በጭራሽ ሊገናኙ የማይችሉ ተስፋዎችን በከንቱ ይመግባሉ፤ ሀይላቸው ያስቻላቸውን ያህል በተቃዋሚዎቻቸው እና ጥያቄ በሚያነሱባቸው ላይ ሁሉ ያለርህራሄ ይዘምታሉ፡፡ ይህ ግልጽ ነው፡፡ ግልጽ ያሆነው ተቃዋሚዎቻቸው የሚወስዱት መንገድ ነው፡፡ ብዙውን ጊዜ (ሁል ጊዜ አይደለም) ሰላማዊ መንገድ በጭራሽ የማይቻል የሚመስለን፣ መንገዱ ስለሚረዝምብን ነው፡፡ ስለዚህም፣ መፍትሄዎቻችን ሁሉ በባህሪያቸው አቢዮታዊ ናቸው፡፡ የሰዎችን ስሜት እያስቆጣን፣ ያልተረጋገጡ መረጃዎችን ከእውነት ጋር እየቀላቀልን፣ ደጋፊዎችን የምንሰበስብ ከሆነ፣ ስልጣኑን የተንተራስን እለት፣ እኛ ከተዋጋናቸው ጭራቆች ስለመሻላችን ልናቀርበው የምንችለው ምንም አይነት መከራከሪያ ሊኖረን አይችልም፡፡

መሪዎች ያስፈልጉናል

በአገር ቤት ስላሉት አልልም፡፡ ስለነሱ ቅንጣት ለማውራት የሞራል ስልጣን የለኝም፡፡ በውጭ ስላለነው ግን ይህን እላለሁ፡፡ ቆንጆዎቹ መሪዎች ገና አልተወለዱም፡፡ በሚናገሩት ርዕስ ላይ ስልጣን ያላቸው፣ ለሚያስቡትም ሆነ ለሚናገሩት ጊዜ መውሰድ የቻሉ፣ የሚዲያውን ቀልብ የገዙ፣ እናም፣ በስልጣን የተናገሩ፣ የጻፉ፣ የተሟገቱ፣ ማሳመን የቻሉ፣ በተናገሩት የጸኑ፣ መሪዎች እንካሁን በመካከላችን አልተመላለሱም፡፡

ማጠቃለያ

ምናልባት አዲስ ነገር አልተናገርኩ ይሆናል፡፡ በአንዳንድ ነጥቦች ላይ ደግሞ ደፍሬ ተናግሬም ይሆናል፡፡ በተሳሳትኩባቸው ነጥቦች ላይ ይቅርታ እጠይቃለሁ፡፡ ስለአንድ ነገር ግን በግልፅነት እናገራለሁ፡፡ ለሃያ አመታት ያህል ለውጥ በኢትዮጵያ ላለመምጣቱ እጅግ አብላጫውን ሀላፊነት አሁን በስልጣን ላይ ያለው መንግስት ሊወስድ ቢገባውም፣ የያንዳንዳችን ድርሻ እንዳለበት ግን አምነን መቀበል ይኖርብናል፡፡ በሰለጠኑት ሕዝቦች መካከል ስንመላለስ፣ ስልጣኔያቸው በብዙ ዋጋና መስዋዕትነት እንደተጸነሰ፣ እንደተማጠና እንደተወለደ ከገባን፣ እኛ ለኛ ለሆኑት ምን ያህል አምጠናል ብለን እራሳችንን መጠየቅ ይኖርብናል፡፡ ያልዘራነው ሊበቅል አይችልም፡፡ አበው እንደሚሉት፣ ሳይዘሩት የሚበቅል አረማሞ ብቻ ነው፡፡ መናተፉንና መለያየቱን ዛሬ ትተን፣ ለአንድ ልብ ብንተጋ፣ ነገን ሀብታችን ማድረግ እንችል ይሆናል፡፡ ይሄ መጣጠፍ ያልመለሰው፣ ሆኖም ግን ትልቁ ጥያቄ፣ “እንዴት ነው ለአንድ ልብ ልንተጋ የሚቻለው?” የሚለው ነው፡፡ በማስተዋል የሚበልጡኝን ለዚህ ጥያቄ እጋብዛለሁ፡፡