[አንድ ለቅዳሜ] የፖለቲካ ተሐድሶን ፍለጋ
የኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ሽግግር በብዙ መልኩ ከማይላወስበት ቅርቃር ውስጥ ገብቷል። መሠረታዊ ፖለቲካዊ ተሐድሶ (Political Reform) እንደሚያመጣ ተስፋ የተጣለበት ኢሕአዴግ በቀዳሚዎቹ ዓመታት ያደረጋቸውን ለውጦች ሳይቀር መልሶ እያጠፋ በኋላ ማርሽ መጓዝን መርጧል። በአጠቃላይ ሲታይም ኢትዮጵያ አዲስ የፖለቲካ ተሐድሶ እንደሚያስፈልጋት ግልጽ ነው። አሁን ለመወያየት ጭምር ቀላል ሆኖ የማይታየው “ቀጣዩ የፖለቲካ ተሐድሶ በወሳኝነት የሚመጣው ከየት እና እንዴት ነው?” የሚለው ጥያቄ ነው።
ጥያቄውን በአቋራጭ ለመመለስ ቀላሉ መፍትሔ “አንድ ብቸኛ የተሐድሶ አነሳሽ ሊኖር አይችልም” ብሎ ውይይቱን በአጭሩ መቅጨት ነው። አለዚያም ፖለቲካችን ዞሮ ዞሮ የአፍሪካ ፖለቲካ ስለሆነ አለዚያም “ያልተጠበቀ ነገር” ወይም “ተአምር” ሊፈጠር እንደሚችል በማመን መልሱን ለጊዜ መተው አማራጭ መልስ ይመስል ይሆናል። ሁለቱም የአጭር መልስ አማራጮች ፖለቲካችን የገባበትን ድቅድቅ ከማሳየታቸውም ባለፈ ቀላል መከራከሪያዎች ተደርገው የሚታዩ አይደሉም። እነዚህን ለጊዜው ትተን ግን አሁን በማኅበረሰባችን ውስጥ ካሉ ኀይሎች/ክፍሎች መካከል ቀጣዩን የፖለቲካ ተሐድሶ በመቀስቀስ የትኛው ምን አይነት አቅም እና ዕድል እንዳለው መገምሙ ጠቃሚ ይሆናል።
1. አገር ውስጥ የሚገኙ ተቃዋሚዎች?
2. የተማረው ኀይል (ተማሪዎችን ጨምሮ)
3. የተደራጁ አካላት (ሲቪል ማኅበራት፣ የሞያ ማኅበራት ወዘተ)?
4. በሥልጣን ላይ በሚገኘው ቡድን ውስጥ የሚገኙ/የሚፈጠሩ ንዑስ ቡድኖች?
5. የታጠቁ ተቃዋሚ ኀይሎች
6. በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን (ዳያስፖራ)
7. ክፍለ አህጉራዊ ሁኔታዎች
8. የውጭ ተጽእኖ (በተለይ የምዕራቡ ዓለም እና ቻይና)
9. ዓለም አቀፋዊ ሁኔታዎች
(እዚህ ያልተቀሰ ቢኖር እየጨመርን እንደምንቀጥል ታሳቢ በማድረግ) ቀጣዩን የፖለቲካ ተሐድሶ በማስጀመርና በመምራት በተናጠልም ሆነ በጋራ ወሳኝ ድርሻ የሚኖራቸውን ሦስት አካሎች በቅደም ተከተል ምረጡ ብንባል መልሳችን ምን ይሆናል?
***************
[በነገራችን ላይ]
የብዙ ሰዎች አትኩሮት የአውሮፓ ኅብረት የምርጫ ታዛቢ ልኡክ ባወጣው የመጨረሻ ሪፖርት ላይ እንደሰነበት ግልጽ ነው። አንባቢዎቻችን ይህ አትኩሮት የሸፈነው ሌላ ምርጫ ነክ ዜና እንዳያመልጣቸው ማስታወስ አግባብ መሰለኝ። የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ “ድኅረ ምርጫ የዳሰሳ ጥናት” እያደረገ መሆኑን አስታውቋል። ጥናት መደረጉ መልካም ሐሳብ ነበር። የጥናቱን ውጤት ከወዲሁም መገመት ስለሚቻል ብዙ የሚያነጋግር አይደለም። ቁም ነገሩ ወዲህ ነው።
የዳሰሳ ጥናቱ “በሁሉም የክልል መስተዳድሮችና በሁለቱ የከተማ አስተዳደሮች በሚገኙ በ77 የዞን መስተዳድሮች ለናሙና በተመረጡ 154 የምርጫ ክልሎች ይካሄዳል፡፡ በተመሳሳይም በተመረጡ 916 የምርጫ ጣቢያዎች ከእያንዳንዱ የምርጫ ጣቢያ 15 መራጮች ናሙና ተወስዶ በጠቅላላው ከ13 ሺህ መራጮች በላይ በጥናቱ ይካተታሉ፡፡…ለጥናቱ መረጃ የመሰብሰብ ሥራ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ እንደሚጠናቀቅና ይህንን ሥራ የሚያከናውኑ ቡድኖች በሁሉም ክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች ካለፈው ጥቅምት 29 ቀን 2003 ጀምሮ ተሰማርተል፡፡”
13 ሺህ ሰዎች በመላ አገሪቱ የሚጠቁበት ጥናት በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ይጠናቀቃል። ኢትዮጵያ እንዴት አይነት ለጥናት የተመቸች አገር ብትሆን ነው 13 ሺህ ሰዎችን ለጥናት ግብአት ለማነጋገር አንድ ወር ብቻ የሚበቃው? የጥናት አቅማችን በየዓመቱ ስንት እያደገ ይሆን? የምስራች ነው።