ግንቦት 7 በጥቅምት 98 የወደቁትን ሰማእታት አስመልክቶ መግለጫ አወጣ
ግንቦት 7 የፍትህ፣ የነፃነት እና የዴሞክራሲ ንቅናቄ በድህረ-ምርጫ 97 በዘረኛው አምባገነን መለስ ዜናዊ ቀጥተኛ ትእዛዝ የአጋዚ ጦር በንጹሃን ዜጎች ላይ ከፈጸማቸው ጭፍጨፋዎች ውስጥ በጥቅምት 98ቱ የወደቁትን ሰማእታት ለማሰብ መግለጫ አውጥቷል።
ንቅናቄው ባወጣው መግለጫ፥ በጥቅምት 98 የወደቁትን በአስርት የሚቆጠሩ ንጹሃን ዜጎች ስናስብ፤ እነሱ የጀመሩትን ጉዞ ለመጨረስ ቃላችንን ማደስ አለብን ብሏል። ዘረኛውና አምባገነናዊው የወያኔ አገዛዝ የግንቦት 1997ቱን ምርጫ ከሰረቀ በኋላ፤ የህዝብ ድምጽ ይከበር ብለው የተነሱ ንጹሃን ዜጎችን በሰኔ ወር እና በተከታዩ ጥቅምት በጭካኔ ማስጨፍጨፉ ይታወሳል።
ብዙዎቹን የግፍ ግድያዎች የፈጸመው እና በብዛት ከአንድ ብሔር በተውጣጡ ሰዎች የተዋቀረው የአጋዚ ጦር በወቅቱ የተልእኮውን ትእዛዝ ሲቀበል የነበረው ከዘረኛው አምባገነን መለስ ዜናዊ እንደሆነ ይታወሳል።
መለስ ዜናዊ ከምርጫው በኋላ ባሉት ወራት በንጹሃን ላይ ስለተካሄደው ጭፍጨፋ ሃዘን ይሰማው እንደሆን ተጠይቆ፤ በወቅቱ የተወሰዱት እርምጃዎች በፖለቲካ ስሌት ላይ ተመስርተው እንደሆነና ምንም ቁጭት እንደሌለው መናገሩ ይታወሳል። በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች እና በሶማሊያ ለተፈጸሙ የጅምላ ግድያዎች እጃቸው ያለበት እና ወደፊት አለማቀፍ ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ ምርመራ እየተደረገባቸው ካሉ የወያኔ ባለስልጣናት ውስጥ አንዱ የዘረኛው አገዛዝ ቁንጮ እራሱ መለስ ዜናዊ እንደሆነ ከዚህ ቀደም መዘገባችን ይታወሳል።
ግንቦት 7 ባወጣው መግለጫ፣ የቀድሞ ትውልዶች ለነጻነታቸው ከፍተኛ መስዋእትነት በመክፈል እንዳለፉ አስታውሶ፤ እነሱ የከፈሉት ዋጋ ግን ሁሌም በአዲስ ዋጋ ሊታደስ ይገባዋል ብሏል።
በተያያዘ ዜና፥ ለሰማእታቱ አለማቀፍ መታሰቢያ ዝግጅቶችን እያሰናዳ ያለው ግብረሃይል በለቀቀው መግለጫ፣ ጥቅምት 98ን በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ከታዩ የጨለማ ወቅቶች አንዱ ብሎታል። ግብረሃይሉ በዋሽንግተን ዲሲ የመታሰቢያ ስብሰባ እንደተዘጋጀም ይፋ አድርጓል።