በርካታ የፌደራል ፖሊስ አባላት በዘረኛነት ምክንያት ስራቸውን እየለቀቁ እንደሆነ ተዘገበ

የኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቪዥን – ኢሳት – በስራ ቦታ ዘረኛነት ምክንያት ስራቸውን እየለቀቁ የሚጠፉ የፌዴራል ፖሊስ አባላት ቁጥር ከመቼውም ጊዜ በላይ ጨምሯል ሲል የአዲስ አበባ ምንጮቹን ጠቅሶ ዘግቧል።

ተለያዩ ወረዳዎች የፌደራል ፖሊስ አባላትን ለመቅጠር ማስታወቂያዎች የተለጠፉ ሲሆን፣ እስከዛሬ ድረስ ብዛት ያላቸው አመልካቾች አለመምጣታቸውንም ዘገባው ገልጿል።

የኢሳት ዘጋቢ አንዳንዶቹን ፖሊሶች ጠይቆ ለመረዳት እንደቻለውም፤ በመስሪያ ቤቱ ውስጥ የሰፈነው በዘር ላይ የተመሰረተ አሰራር ስራቸውን ለመልቀቅ አስገድዷቸዋል። እድገት፣ ሹመት፣ እና የስራ ምድብ በተወሰኑ ብሄር አባላት ችሮታ እንደሚሰጥ የሚናገሩት ፖሊሶች፣ ማንበብና መጻፍ በቅጡ የማይችሉ የአንድ ብሄር አባላት ዲፕሎማና ዲግሪ ያላቸውን የሌላ ብሔር አባል ፖሊሶች እንደሚያዙ ተናግረዋል።

እድገት ለማግኘት የተወሰኑ ብሄር ተወላጆችን ታማኝነት ማግኘት ይጠይቃል የሚሉት ፖሊሶች፣ ሁኔታው ለመቋቋም ከሚችሉት በላይ ሲሆንባቸው እንደሚለቁ ኢሳት ዘጋቢውን ጠቅሶ ዘግቧል። በጉዳዩ ዙሪያ የፌደራል ፖሊስ ባለስልጣናትን ለማግኘት ያደረገው ጥረት እንዳልተሳካለትም የዜና አውታሩ ገልጿል።

ኢትዮጵያ ውስጥ፥ የመንግስትን ስልጣን በዋነኛነት የሚቆጣጠሩት እና በተለይ በመከላከያ እና የህግ አስከባሪ ተቋማት ውስጥ ቁልፍ ቦታዎችን የያዙት ጥቂት የትግራይ ተወላጆች እንደሆኑ ይታወቃል። የግንቦት 7 ድምጽ ከዚህ ቀደም ባወጣው ሰፊ ሪፖርት ከ60 የመከላከያ ቁልፍ መቀመጫዎች ውስጥ 57ቱ በትግራይ ተወላጆች መያዛቸውን ማጋለጡ ይታወሳል። በጦሩ ውስጥ፥ በውትድርና አሰራር ተቀባይነት በሌለው መልኩ፤ ዝቅተኛ የስልጣን ደረጃ ያላቸው ትግራውያን የበላያቸው የሆኑ የሌላ ብሔር ተወላጆችን እንደሚያዙ፣ እንደሚሰድቡ እና በግልጽ እንደሚያዋርዱ ተደጋጋሚ ስሞታዎች ይሰማሉ።