በድህረ-ምርጫ 97 የወደቁትን ሰማእታት ለማሰብ የተሰናዱ ዝግጅቶች በአለም ዙሪያ ተካሄዱ
በጥቅምት 1998 አመተ ምህረት፤ በዘረኛው አምባገነን መለስ ዜናዊ ቀጥተኛ ትእዛዝ በአጋዚ ጦር የተጨፈጨፉትን ሰማእታት ለማሰብ ከተሰናዱት እና አንድ ወር ሙሉ ከሚካሄዱት ዝግጅቶች ውስጥ የመጀመሪያዎቹ እሁድ ኖቬምበር 7 ቀን በተለያዩ የአለማችን ክፍሎች ተካሄደዋል።
በሰሜን አሜሪካ፣ በአውሮፓ፣ በአፍሪካ፣ በአውስትራሊያ እና በመካከለኛው ምስራቅ ከተሞች የመታሰቢያ ዝግጅቶች የተካሄዱ ሲሆን፤ በአሜሪካ ዋና ከተማ ዋሽንግተን ዲሲ የተዘጋጀው ስብሰባ በተሳካ ሁኔታ ተከናውኗል። በመቶዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች በተሳተፉበት ዝግጅት ላይ ተገኝተው ንግግር ካደረጉት መሃል ዳኛ ፍሬህይወት ሳሙኤል፤ ዶ/ር አክሎግ ቢራራ፤ ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ፤ ዶ/ር ግሬጎሪ እስታንተን እና የጋራ ንቅናቄ ለአዲሲቱ ኢትዮጵያ የተባለው ድርጅት መስራች እና ዋና ዳይሬክተር አቶ ኦባንግ ሜቶ ይገኙበታል።
በድህረ ምርጫ 97 የተካሄዱትን ግድያ እንዲያጣራ የተቋቋመው ኮሚቴ ሊቀመንበር የነበሩትና በአሁኑ ሰዓት በስደት ላይ የሚገኙት ዳኛ ፍሬህይወት ሳሙኤል፣ “የህግ የበላይነት መጥፋት፤ አንድም ሰው ለፍርድ ያለመቅረቡ…ይረብሻል። የመኖር ዋስትና ያሳጣል” ብለዋል።
ዘረኛው እና አምባገነናዊው የወያኔ አገዛዝ በኢትዮጵያ ላይ የሚያካሄደውን ዘረፋ የሚጋልጥ መጽሃፍ በቅርቡ ያሳተሙት እና ለረዥም አመታት የአለም ባንክ ሰራተኛ የነበሩት ኢኮኖሚስት ዶ/ር አክሎግ ቢራራ፤ በውጭ አገር ያሉ ኢትዮጵያውያን ቢያንስ የወያኔን አገዛዝ የውጭ ምንዛሬ በመከልከል ትልቅ ስራ ሊሰሩ እንደሚችሉ መክረዋል።
የግንቦት 7 ንቅናቄ እና የጥምረት ለነፃነት፣ ለእኩልነት እና ለፍትህ በኢትዮጵያ ሊቀመንበር የሆኑት ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ በበኩላቸው ግድያዎቹ በተካሄዱበት ጊዜ የሆኑ ክስተቶችን፤ በወቅቱ ሰላምን ለማውረድ ከገዢው ቡድን ጋር የተሞከሩ ውጤት አልባ ድርድሮችን አስታውሰው፤ የአገዛዙ ቁንጮዎች “ምርጫቸው ከስልጣን መውረድ እና ኢትዮጵያን ማጥፋት ቢሆን፤ ኢትዮጵያን ከማጥፋት ምንም ወደ ኋላ የምይሉ ናቸው…” ሲሉ መደምደማቸውን ገልጸዋል።
“ጄኖሳይድ ዋች” የተባለው እና በአለማችን ዙሪያ የሚካሄዱ የዘር ማጥፋት ወንጀሎችን የሚከታተለው ድርጅት መሪ የሆኑት ዶ/ር ግሬጎሪ እስታንተን፤ ኢትዮጵያውያን ቢደራጁ የወያኔን አገዛዝ መገልበጥ ከባድ እንዳልሆነ አስረድተዋል። ዶ/ር ግሬጎሪ ጨምረውም፥ በኢትዮጵያ ግፍ የሚፈጽሙት ግለሰቦች አንድ ቀን ወደ ፍርድ መቅረባቸው ስለማይቀር፤ ሁሉም ሰው ስማቸውን በመጻፍ እና መረጃ በማሰባሰብ እንዲሳተፍ ጥሪ አቅርበዋል።
የመታሰቢያ ዝግጅቱ አስተባባሪ ግብረሃይል በበኩሉ፥ በኢትዮጵያ የሚካሄዱ የግፍ ግድያዎችን እና ጭፍጨፋዎችን የሚመመዘግብ፣ “ethiopianmassacre.com” የተባለ ዌብ ሳይት መከፈቱን አስታውቆ፤ ኢትዮጵያውያን የሚያውቋቸውን መረጃዎች ወደዚህ ማህደር በመላክ እንዲረዱ ጥሪ አድርጓል።