በአንድ ስፍራ የሚፈጸም ኢ-ፍትሃዊነት፣ በየትኛውም ቦታ ላለ ፍትህ አደጋ ነው

ከዝግጂት ክፍላችን

ዘረኛውና አምባገነናዊው የወያኔ ቡድን፣ “ጅቡ አማራ መጣብህ” እያለ የትግራይን ህዝብ ማስፈራራትን እና ከጉያው ማስገባትን እንደ ፖለቲካ ስልት ሲጠቀም አስርተ አመታት ተቆጥረዋል። ይህ ስሌት አገዛዙ እድሜውን እንዲያራዝም ሲረዳው፤ የትግራይ ህዝብ ወደፊት ሊገጥመው ስለሚችለው አደጋ ያለውን ስጋት ግን እያባባሰው ሄደ እንጂ አልቀነሰውም።

በድህረ-ምርጫ 97፥ የወያኔ አገዛዝ “አማራ ሊያጠፋችሁ ነው” ብሎ ለትግራይ ተወላጆች የሰበከው ስብከት በትግራይ ምሁራን እና ልሂቃን ዘንድ ፈጣን ተቀባይነት ማግኘቱ ብዙዎችን አስደንግጦ ነበር። ምንም እንኳ የትግራይ ክልል እና ተወላጆች በወያኔ አገዛዝ አማካኝነት እንደሚጠቀሙ ብዙ ቢወራም፤ ከአገዛዙ ይልቅ ለትግራይ ህዝብ ጥቅም ይቆም የነበረው የተቀረው ኢትዮጵያዊ ነበር። ለዚህ የሚሆኑ ማስረጃዎችን ጠቅሶ ወደፊት ማስረዳት ይችላል።

ዘረኛው አገዛዝ በአገሪቱ ውስጥ ለሚያካሄደው ግፍ እና አፈና ሆን ብሎ የትግራይ ተወላጆችን መጠቀሙ፤ በተለይ በትምህርት ቤቶች እና በተለያዩ ስፍራዎች የስለላ ስራ የሚሰሩ የትግራይ ተወላጆች ጓደኞቻቸውን አሳልፈው ሲሰጡ እንዲታዩ መደረጋቸው የቂም፣ የቁጣ እና የበቀል ስሜቶችን ስለመፍጠሩ ጥያቄ የለውም። በንግድ እና በፖለቲካ ስልጣን ክፍፍልም ከመንግስት ተቋማት በሚደረግላቸው ልዩ ድጋፍ በብዛት እየተጠቀሙ ያሉት ትግራውያን በመሆናቸው ስር የሰደደ ቅሬታ መብቀል ከጀመረ ቆይቷል።

እነዚህ ስሜቶች ተፈጥሯዊ እና አዎንታዊም ናቸው፤ እየተሰራ ያለው ነገር ትክክል አለመሆኑን እናውቃለን ማለት ነው። በህዝብ ንብረት እና ተቋማት ውስጥ እንዲህ ያለ የአድሎ ስራ ሲሰራ መቆጣትም ተገቢ ነው። ስጋት እየፈጠረ ያለው ግን እነዚህ ስሜቶች ወዴት ሊያመሩ ይችላሉ የሚለው ጥያቄ ነው።

አንዳንዶች፥ ወያኔ የፈለገውን ያህል የመከፋፈል ስራ ቢሰራ በሃገራችን ውስጥ የእርስ በርስ ግጭት አይፈጠርም፤ ህዝባችን ለብዙ ዘመናት ተከባብሮ መኖርን የተለማመደ ነው ይላሉ። ይህ የኛም ተስፋ ነው። ይሁን እንጂ፥ ይህንን ደግሞ የሚቃረን አስተያየት የሚሰጡ እና በአገሪቱ ውስጥ በዘር ወይም በሃይማኖት ላይ የተመሰረተ ግጭት ሊቀሰቀስ እንደሚችል የሚያሳስቡ ድምጾች እየተበራከቱ መጥተዋል። ከዚህ ቀደም፥ በተለያዩ የውጭ አገር ተመራማሪዎች የወጡ ጽሁፎችን ጨምሮ፤ በዛሬ የዜና ዘገባ እንዳሰማናችሁ፥ ጄኖሳይድ ዋች የተባለው የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅት ፕሬዚደንት ዶ/ር ግሬጎሪ እስታንተን በግልጽ ቋንቋ ትግራውያን ለወያኔ ሃጢያት ሊከፍሉ ይችላሉ የሚል ስጋት እንዳለባቸው ተናግረዋል። ይህንን አመለካከት የሚጋሩ ኢትዮጵያውያንም ብዙ ናቸው።

ለምሳሌ ያህል ከጥቂት አመታት በፊት በጅማ አካባቢ የተከሰተውን ሃይማኖታዊ ግጭት እና የተካሄደበትን አሰቃቂ አኳኋን ልብ ላለ፤ የምንኖረው በተለየ ጊዜ እንደሆነ፤ እንዲሁም ከመጋረጃው በስተጀርባ የሚቀሳቀሱ እና ግጭትን በመፍጠር የሚጠቀሙ ሃይሎች እንዳሉ ለመረዳት አያዳግተውም። ከነዚህ ሃይሎች ደግሞ ቀንደኛው የወያኔ አገዛዝ እራሱ ነው። የዛሬው ትኩረታችንም በዚሁ ላይ ነው።

ብዙዎች የወያኔ አገዛዝ ሲገለበጥ በትግራውያን ላይ የሚወሰድ የበቀል እርምጃ ሊኖር እንደሚችል ያሳስባሉ። ያ ስጋት እንደተጠበቀ ሆኖ፣ እኛ ደግሞ የምንጨምረው አለን። ሊያሰጋን የሚገባው፥ የወያኔ የስልጣን ወንበር ሲነቀነቅ በትግራውያን ላይ ከሌሎች ብሔረሰቦች አባላት ሊደርስባቸው የሚችልን ጥቃት ብቻ ሳይሆን፤ በአገዛዙ ራሱ የሚቀናበርን የጭካኔ እርምጃ ነው።

መለስ ዜናዊ እና ጓደኞቹ፥ እስካሁን ከኢትዮጵያ ህዝብ የበዘበዙትን ሃብት ማስቀመጫ እና ልጆቻቸውን ማንገሻ መንበረ ስልጣን ይፈልጋሉ። የኢትዮጵያ ህዝብ “በቃ!” ብሎ በመነሳት ከስልጣን ያባረራቸው ለታም፤ ትግራይን ገንጥሎ አዲስ አገር በመፍጠር ለራሳቸው እና ለእኩይ ህልማቸው መሸሸጊያ ምሽግ ለመፍጠር እንደሚሞክሩ የብዙዎች ግምት ነው። ይህን ህልማቸውን እውን ለማድረግ ደግሞ የትግራይን ህዝብ ድጋፍ ማግኘት የግድ ነውና፤ ትግራውያንን ከተቀረው የኢትዮጵያ ህዝብ ጋር በማያዳግም ሁኔታ ሊያጣሉ የሚችሉበት አንድ መንገድ ቢኖር ከፍተኛ ፍጅት ማቀናበርን ነው። እንዲህ አይነቱ እልቂት እና ተከትሎት የሚመጣው ቅራኔ ደግሞ ህዝቡ ከሌላው ኢትዮጵያዊ የተለየ ማንነት እንዲሰማው የሚያደርገው ሲሆን፤ ይህ ለወያኔ ቁንጮዎች ታላቅ ድል ነው። በመለስ ዜናዊ የሚመራው ገዢ ቡድን፣ ይጠቅመኛል ብሎ ካመነ እንዲህ ያለን ጭካኔ ከመፈጸም ወደ ኋላ የሚል እንዳልሆነ ደግሞ ያለፈ ታሪኩ ያመለክታል።

ስለዚህም፥ የትግራይ ህዝብ እና ልሂቃኑ፥ “በአንድ ስፍራ የሚፈጸም ኢ-ፍትሃዊነት፣ በየትኛውም ቦታ ላለ ፍትህ አደጋ ነው” የሚለውን አባባል አንግበው፤ ቀኑ ሳይመሽ እና ምንም መስራት የማይቻልበት ደረጃ ላይ ሳይደረስ በፊት በአገራችን ፍትህን ለማስፈን የሚደረገውን ትግል ሊቀላቀሉ ይገባል።

ያም ሆነ ይህ ግን፥ ግንቦት 7 የፍትህ፣ የነጻነት እና የዴሞክራሲ ንቅናቄ፤ በማንኛውም ጊዜ ቢሆን ለሁሉም የኢትዮጵያ ህዝቦች ደህንነት፣ ፍትህ እና መብት የሚቆም፣ የሚሟገት፣ የሚታገል እና የሚከላከል መሆኑን ደግሞ እና ደጋግሞ ሊያስረግጥ ይወዳል።