ፖለቲካዉ የማይነካዉ ሰዉ የለም ! – ግርማ ካሳ
ፖለቲካ የሚለዉ ቃል እንደ ጸያፍና አስፈሪ ቃል ነዉ በብዙ ኢትዮጵያዉያን ዘንድ የሚታየዉ። እንደዉም በተለምዶ ፖለቲካ ከኮረንቲ ጋር ይመሳሰላል። ነገር ግን፣ ይመስለናል እንጂ፣ ከፖለቲካ ነጻ የሆነ ሰዉ የለም።
በአዎንታዊነት ሆነ በአሉታዊነት «ፖለቲካ አያገባንም» የሚሉ ዜጎችን ጨምሮ ፣ ምን ያህል የፖለቲካ ዉሳኔዎች፣ በእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ላይ እያደረሱ ያለዉን ተጽእኖ በስፋት ለማብራራት በርካታ ምሳሌዎችን መዘርዘር ይቻላል። ለጊዜዉ ግን አራት ምሳሌዎችን ብቻ አቀርባለሁ።
1. ሰሞኑን በአገራችን ትልቅ የመወያያ አጀንዳ የሆነዉ፣ በአዲስ አበባ ሊደረግ የታሰበዉ (ምናልባት ይሄን ጊዜ ተደርጎ ሊሆን ይችላል) የግብረ ሰዶማዉያን ስብሰባ ነዉ። ከተፈጠሮ ሕግ ዉጭ የሆነ፣ እግዚአብሄርን የሚያስቆጣ እጅግ ጸያፍ የሆነ የርክሰት ተግባር ላይ በመሰማራት፣ እንደጀብድ ይህንን ርካሽ ተግባር በአገራችን ለማስፋፋት የተሰለፉ ጥቂት የዉጭ አገር ዜጎች፣ የሚያደርጉትን ስብሰባ በማዉገዝ፣ የሃያማኖት አባቶች በአንድ ላይ ሆነዉ አንዳንድ ዉሳኔዎችን ለማሳለፍ እየተነጋገሩ እንደሆነ ይነገራል።
ነገር ግን አንድ የማይነሳ ትልቅ ጥያቄ አለ። ይህ ስብሰባ በመጀመሪያ ደረጃ ለምን ተፈቀደ ? የፈቀደውስ፣ እነዚህ ጸያፍ አላማ ይዘዉ የመጡ ግለሰቦች ወደ አገር ቤት እንዲገቡ ያደርገዉስ ማን ነዉ ? የፖለቲካ መሪዎች አይደሉም እንዴ ? ዉሳኔዉ የፖለቲካ ዉሳኔ አይደለምን ? ይህን አይነት ስብሰባ እንዲደረግ የፖለቲካ ዉሳኔ ሲወስኑ፣ አራት ኪሎ ያሉ ባለስልጣናት የግብረ ሰዶማዉያን ወዳጆች፣ እግዚአብሄርን የሚያስቆጣ፣ ቤተሰብን የሚበትን ጸያፍ ተግባር እንዲስፋፋ ተባባሪዎች ተደርገዉ ሊወሰዱ አይችልምን ?
2. ሌላዉ ለሳምንታት ዜጎችን ሲያምስና ሲያሰጭንቅ የቆየዉ ሁለተኛዉ አጀንዳ የመሬት ሊዝ ጉዳይ ነዉ። የቤት አከራይ፣ ተከራይ፣ ገዢ፣ ሸጪ የሆኑ ..በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎች ግራ ተጋብተዉ፣ ወደዚህ ወዲዚያ ሲላወሱ እያየን ነዉ። ይህ በመሬት ሊዝ ዙሪያ በኢሕአዴግ የተደነገገዉ አዋጅ የፖለቲካ ዉሳኔ ነዉ። በዚህ በፖለቲካ ዉሳኔ መሰረት የሚመጡ ጥቅሞችም ሆነ ጉዳቶች በፖለቲካዉ ምክንያት የመጡ ወይንም የሚመጡ ናቸዉ።
በአገር ቤት የሚኖሩ የአንድ ቤተ ክርስቲያን ፓስተር፣ በዉጭ አገር በተለያዩ ከተሞች በመዞር ላይ ይገኛሉ። በአዲስ አበባ ለቤተ ክርስቲያናቸዉ ሕንጻ ማሰሪያ ገንዘብ ለማሰባሰብ ነዉ ወደ አሜሪካን አገር የመጡት። ቤተ ክርስቲያኗ የተሰጣት መሬት አለ። በባለስልጣናቱ በዚያ መሬት ላይ ፎቆ መሰራት አለበት ስለተባለ፣ ተለቅ ያለ የቤተ ክርስቲያን ሕንጻ መስራት ስላስፈለገ ነበር ገንዘብ የተፈለገዉ።
ሕዝቡ አምላኩን ለማምለክ በቀላል ዋጋ የተሰራ አዳራሽ ይበቃ ነበር። እንደዉም እግዚአብሄርን ለማምለክ የግድ ጣራ አያስፈልግም። በሜዳ ላይ እጆችን ወደ አምላክ ዘርግቶ መጸለይ ይቻላል። ነገር ግን በባለስልጣናቱ የተወሰነዉ የፖለቲካ ዉሳኔ ፣ የቤተ ክርስቲያኒቱን ፓስተር በየዉጭ አገሩ ሄደዉ ገንዘብ ለመለመን እንዲንከራተቱ፣ እርፈውም ወንጌልን በመስበክ ላይ እንዳያተኩሩ አደርጓቸዋል።
3. ከጥቂት ወራት በፊት በፍኖት ለነጻነት ጋዜጣ ላይ ያነበብኩት አንድ አሳዛኝ ታሪክ ነበር። አንዲት የነቀምቴ ነዋሪ የሆነች፣ ከዚያዉ ከኦሮሚያ ከኮሌጅ የተመረቀች ወጣት፣ በወለጋ ስራ ስላላገኝች ወደ አዲስ አበባ ትሄዳለች። በአዲስ አበባ ስራ ማፈላለጉን ትያያዛለች። ልጅቱ የፌደራልና የአዲስ አበባ ከተማ የሥራ ቋንቋ የሆነዉን አማርኛ መናገር በትንሹ ብትችልም፣ መጻፍ ግን ጭራሹን አታወቅም። በዚህም ምክንያት ስራ የማግኘቱ ነገር ትልቅ ተራራ መዉጣት ሆነባት። ሳምንታት፣ ወራት አለፉ፤ በጭራሽ ስራ ልታገኝ አልቻለችም። መሻሻል ትፈልጋለች፣ በሞያዋ መቀጠር ትፈልጋለች። በኢኮኖሚ እራሷን ችላ ትልቅ ደረጃ መድረስ ትፈልጋለች። ግን ቋንቋ ካለማወቋ የተነሳ ወደፊት መሄድ አልቻለችም። ተመልሳ ፣ ተስፋ ቆርጣ ወደ ነቀምቴ ተመለሰች።
አሁን ለዚች ልጅ ስራ አለመግኘት ምክንያት የሆነዉ ምን ነዉ ? የልጅቷ ስንፍና ነዉን ? በጭራሽ አይደለም። እርሷማ ጎብዛ፣ የሁለተኛ ትምህርቷን በደንብ አጠናቃ፣ ስራ ለመፈለግም ካደገችበት ከተማ በመቶ ኪሎሜትሮች ርቃ በመሄድ ስትባዝን የከረምች ሴት ናት። ነገር ግን በትግራይ እንደሚደረገዉ (በትግራይ የአራተኛ ክፍል ተማሪዎች አማርኛን አቀላጥፈዉ ያነባሉ) በኦሮሚያ የሚኖሩ ተማሪዎች አማርኛ እንዲማሩ አልተደረገም።
አማርኛን አለማስተማር ከብሄር ብሄረሰቦችን መብት ማስጠበቅ ጋር ምንም አይነት ግንኙነት የለዉም። በትግራይ ትግሪኛና አማርኛ ዜጎች እንዲማሩ እንደተደረገዉ ሁሉ፣ በኦሮሚያም ተማሪዎች ኦሮምኛንና አማርኛን አቀላጥፈዉ የሚናገሩ የሚያነቡና የሚጽፉ እንዲሆኑ ማድረግ ይቻል ነበር። በአዉሮፓ ያለ ተማሪ በትምህርት ቤት ሶስት ቋንቋ እንዲማር ነዉ የሚደረገዉ።፡ለምሳሌ በፈረንሳይ ፈረንሳይኛና እንግሊዘኛ በብዙ ቦታ ትምህርት ሲሰጥ፣ሌላ ሶስተኛ ቋንቋም በምርጫ እንዲማሩ ይደረጋል። አንዳንዶቹ ጣሊያንኛ፣ አንዳንዶቹ ጀርመንኛ ..ይማራሉ። ቋንቋ መማር ይጥቅማል እንጂ አይጎዳም። ቋንቋ መግባቢያ ነዉ።
ነገር ግን በኦሮሚያ የሚኖሩ ተማሪዎች የፌደራል እንዲሁም ከትግራይና ከኦሮሚያ በስተቀር የተቀሩት ክልሎች የሥራ ቋንቋ የሆነዉን አማርኛን እንዳይማሩ ተደረገ። በአዲስ አበባ፣ በደብረ ማርቆስ፣ በአዋሳ፣ በአሶሳ፣ በሃረር፣ በመተክል ፣ በሳማራ .. የኦሮሚያ ተማሪዎች እንዳይሰሩ፣ በተወሰኑ የኦሮሚያ ቦታዎች ብቻ እንዲወሰኑ ተደረገ። ስስተማቲክ በሆነ መንገድ በኢኮኖሚዉ ዘርፍ የበታች ሆኑ። ትልቅ በደል ደረሰባቸዉ።ይህን አማርኛን ያለማስተማርና የኦሮሚያ ነዋሪዎች የስራ በር በመላዉ ኢትዮጵያ ክልሎች እንዳይከፈትላቸዉ ያደረገዉን ዉሳኔ፣ ኢሕአዴግ ብቻዉን የወሰነዉ የፖለቲካ ዉሳኔ ነዉ። ለዚች የነቀምቴ ልጅ ከኦሮሚያ ዉጭ ስራ ላለማግኘቷ ምክንያቱ በአገራችን የተስፋፋዉ የዘር ፖለቲካው ነዉ።
4. ማንም ዜጋ ልጆቹ ተምረዉ፣ ትልቅ ደረጃ እንዲደርሱለት ይፈልጋል። በኢትዮጵያ ብዙ ትምህርት ቤቶች ቢኖሩም የትምህርት ጥራቱ እጅግ በጣም ያሽቆለቆለ መሆኑን ብዙዎች ይናገራሉ። አብዛኛዉ ተማሪ ከአስረኛ ክፍል አልፎ እንዲሄዱ አይደረገም።
አገራችን ኢንጂነሮች፣ ሃኪሞች፣ የኮምፒተር ሳይንቲስቶች ፣ ነርሶች ወዘተረፈ በብዛት ያስፈልጓታል። ፊስክስ ፣ ኬሚስትሪ፣ ባዮሎጂ .. ሳይማሩ፣ በአስረኛ ክፍል ተገድበዉ እንዲቆዩ ተማሪዎች ከተደረገ፣ እንዴት ተደርጎ ነዉ በእዉቀት የዳበሩ ዜጎችን የምናፈራዉ ? ለዚህ ለትምህርት ደረጃ ማሽቆልቆል የዳረገን፣ ልጆቻቸዉን፣ አገር ቤት በሚገኙ እንደ ሳንፈርድ፣ ሊሴ ገብረማሪያም በመሳሰሉ የግል ትምህርት ቤቶች፣ አሊያም ዉጭ አገር ልከዉ በአሥር ሺሆች የሚቆጠሩ ዶላሮች እየከፈሉ በሚያስተምሩ የኢሕአዴግ ባለስልጣኖች የፖለቲካ ዉሳኔ አይደለምን ?
በርካታ ሌሎች ምሳሌዎችን በተለያዩ ዘርፎች በመዘርዘር መቀጠል ይቻላል። በአንድ በኩል ይሁን በሌላ በኩል፣ ከአራት ኪሎ የሚወሰኑት የፖለቲካ ዉሳኔዎች የማይነኩት ዜጋ አይኖርም። « ኦ ኦ ፖለቲካና ኮንረንቲ አንድ ናቸዉ. ! እኔ አያገባኝም » በሚል የፖለቲካ ፓርቲዎች ወይንም የሲቪክ ማህበራትን ተቀላቅለን ፖለቲካዊ አስተያየት ላለመስጠት ዝምታን ብንመርጥም፣ ሌሎች ጥቂቶች የሚያደርጉት የፖለቲካ ዉሳኔ፣ ወደድንም ጠላንም ቁጭ ብለን በተቀመጥንበት፣ ቤታችንን አንኳኩቶ እኛን መንካቱ ፣ ማናጋቱ አይቀርም።
እንግዲህ ያለን አማራጭ ሶስት ነዉ። የመጀመሪያዉ አማራጭ በፖለቲካዉ ምክንያት በቀጥታ፣ አሊያም ፖለቲካዉ በወለደዉ በኢኮኖዉ ችግር አገር ለቆ ተሰዶ መሄድ ነዉ። የቀናን ወደ አሜሪካና አዉሮፓ፣ ያልቀናን ደግሞ ወደ አረብ አገረ !!!!
ሁለተኛዉ አማራጭ ጥቂቶች በሚወስኑት የፖለቲካ ዉሳኔ ዉስጣችን እየደበነ፣ እየተቃጠለና እየተናደድን ማጉረምረምና ብሶታችንን ነጋ ጠባ ማዉራት ነዉ። ከጊዜ ወደ ጊዜ በንዴት ደም ብዛታችን እየጨመረ፣ ጸጉራችን እየሸበተ፣ ኑሮን ለመርሳት በየመሸታ ቤቱ ብርሌያችንን መጨበጥ !!!
ሶስተኛዉ አማራጭ እጅግ ፈታኝ፣ ከራስ ጥቅም አልፎ ለሌላ ማሰብን የሚጠይቅ፣ በርግጥ ዘላቂነት ያለዉ መፍቴሄ እንዲመጣ የሚረዳ ፣ የሚያዋጣ አማራጭ ነዉ።
ዋናዉ የአገራችን ችግር የመልካም አስተዳደር፣ የእኩልነት፣ የፍትሕ እጦት፣ እንዲሁም የሙስና የዘረኝነት የጥላቻ መሳፋፋት ነዉ። በአጭሩ አባባል፣ የአገራችን ችግር የፖለቲካ ችግር ነዉ። የፖለቲካ ችግር የሚፈታዉ ደግሞ በፖለቲካ ትግል ነዉ። ይህን ተረድተን፣ የፖለቲካ ዉሳኔዎች አገርንና ሕዝብን በሚጥቀሙ መልኩ እንዲወሰኑ ለማድረግ ሰላማዊ የሆነዉን የፖለቲካ ትግል መቀላቀል የግድ አስፈላጊ ነዉ። ሳይታረስ አይታጨድም። ሳይወቃ አይፈጭም።
ይህ ሶስተኛ አማራጭ ትእግስትን የሚያስጨርስ፣ እጅግ ፈታኝ የሆነ አማራጭ ነዉ። ነገር ግን ካለፉት ስህትቶች ትምህርት በመወሰድ ፣ በጥንቃቄ፣ በትጋት በቁርጠኝነትና በአንድነት ይህን ትግል ከተያያዝነዉ ዉጤት የማናመጣበት ምንም ምክንያት የለም።
መሰረት በሌለዉ አስቂኝ ወህኒ የወረዱት አቶ አንዱዋለም አራጌና አቶ እስክንድር ነጋን የመሳሰሉ ወገኖቻችን የመረጡት አማራጭ ይሄንኑ ሶስተኛ አማራጭ ነዉ። እነዚህ ብርቱና አገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን ፣ ተሰደዉ መኖር ይችሉ ነበር። እንደማንኛዉም ሌላ ዜጋ፣ በሞያቸው ተቀጥረዉ ፣ አፋቸዉን ዘግተዉ፣ ግፍ ሲፈጸም እያዩ ዝም ብለዉ ፣ በአንጻራዊነት የተመቻቸ ኑሮ መኖር አላቃታቸዉም። ነገር ግን ሕሊናቸውን፣ በዉስጣቸዉ የሚያቃጭለዉን የፍትህ ደዉል አዳምጠዉ፣ ፍጹም ሰላማዊ በሆነ መንገድ የፖለቲካ ለዉጥ እንዲመጣ እየጣሩ ያሉ ጀግኖች ናቸዉ።
አዎ በዚህም ምክንያት፣ ደፋር፣ ቆራጥና በራሱ የሚተማመን የፍትህና የዲሞክራሲ አርበኛ ሲነሳ የማይወድ የኢሕአዴግ አገዛዝ፣ ለሌሎች ታጋዮች የመቀጣጫ ምሳሌ እንዲሆኑ፣ ዜጎችንም ለማስፈራራት ሲል ወደ ወህኒ ልኳቸዋል።ነገር ግን እነ አንዱዋለም በመታሰራቸዉ መልእክታቸዉን ማስተላለፋቸዉን አላቆሙም። ቢታሰሩም መታሰራቸው በራሱ ድምጽ ሆኖ እየተናገረ ነዉ። በአካል ፊታቸዉን ባናይም፣ ድምጻቸዉን ባንሰማም፣ በመንፈስ እየሰማናቸዉ ነዉ። «ዛሬ በኛ የደረሰው ግፍ ምልክት ይሁናችሁ። ነገም የእናንተን ቤት ያንኳኳል። ከዝምታ ወጥታችሁ፣ ዉስጥ ዉስጡን ማጉረምረማችሁን አቁማችሁ፣ በድፍረት ትግሉን ተቀላቀሉ » እያሉን ነዉ። «ለጊዜዉ በዝምታችሁ ጌዚያዊ ጥቅም ልታገኙ ትችላላችሁ። ነገር ግን ይቆጫቹሃል። ዛሬ አሳ ተሰጧችሁ ነገ ከምትራቡ፤ አሳ ማጥመድ ብትለምዱ አይሻላችሁምን ? » እያሉን ነዉ። አዎ የነ እስክንድር ነጋን መልእክት አዳምጠን በሶስተኛዉ አማራጭ ለመንቀሳቀስ የምንነሳበት ጊዜ ነዉ።
አንዳንዶቻችን አራተኛ አማራጭ አለ የምንል አለን። በዉጭ አገር ተቀምጠን፣ በኢሳያስ አፈወርቂ አገዛዝ ትከሻ ላይ ተኝተን ፣ እንመራዋለን የምንለዉ፣ ይኑር አይኑር የማይታወቅ የትጥቅ ትግልን እንደ አማራጭ ልናቀርብ እንሞክራለን። ነገር ግን ታሪክና ልምድ እንደሚያሳየዉ አገር ቤት መሰረት ያላደረገ ትግል ዉጤት ሊያመጣ አይችልም። ያዉ ደግሞ እንደ ኢሳያስ አፈወርቂ ያለ ኤርትራዉያን ወንድሞቻችንን ደም በየሳዋዉ እያፈሰሰ ያለን አምባገነን መሪ ቀሚስ ስር ተሸሽገን ፣ ለዲሞክራሲ እንቆማለን ማለት አይሰራም። ጎበዝ እናስብ እንጂ !!!
በዉጭ የሚኖረዉ ኢትዮጵያ በትግሉ ትልቅ ሚና ሊጫወት የሚችል እንደሆነ ግልጽ ነዉ። ሆኖም ግን ከአገር ቤቱ ትግል ተነጥሎ ለብቻዉ የሚያደርገዉ ማናቸዉም አይነት እንቅስቃሴ ጊዜና ገንዘብ ከማባከን ዉጭ እንደ ቁም ነገር ሊቆጠር የሚገባዉ አይደለም።በመሆኑም ኢትዮጵያዉያን ቆም ብለን፣ ያለዉን ሁኔታ ግራ ቀኝ አገናዝበን ለአገራችን በሚጥቅሙ ጉዳዮች ላይ በቁርጠኝነትና በአንድነት መነሳት ይኖርብናል። በአገር ቤት ያለነዉ፣ የፍርሃትንን ካባ አዉልቀን ለመብታችን፣ ለክብራችን ለልጆቻችን የወደፊት እድል መቃናት በመነሳት፣ የሰላማዊ ትግሉን እንቀላቀል። አዎ ፖለቲከኞች እንሁን !!!!!! ፖለቲካ ሐጢያት አይደለም። ለፍትህ ፣ ለሰላም፣ ለእኩልነት መቆም፣ «ፍርድ አይዛባ፣ ዜጎች አይበደሉ፣ የግፍ ቀንበር ይሰበር፣ የሕሊና እስረኞች ይፈቱ ፣ በዘር መከፋፈል ይቁም ፣ ዳቦ ለተራበ …» ማለት ሐጢያት አይደለም። ይልቅስ ሰዉ ሲበደል፣ ፍርድ ሲዛባ ዝም ማለት ነዉ እግዚአብሄርን የሚያሳዝነዉ።
በዉጭ አገር የምንኖር ኢትዮጵያዉያን የሕዝባችን አካል ነን። በባእድ አገር ስንኖር፣ በአገራችን ያላየነዉን መብታችን ተጠብቆ፣ የተመቻቸ ኑሮ ልንኖር እንችላለን። ነገር ግን ከየት እንደመጣን መርሳት የለብንም። በአገራችን ያሉ ወገኖቻችን ሕመም ሕመመቻን፣ ብሶት ብሶታችን ሊሆን ይገባል። በመሆኑም ከነርሱ ጎን በመቆም የሚያደርጉትን ትግል ሳንታክት፣ ሳንዘናጋ፣ በተለያዩ አምታች ወሬዎች ሳንወናበድ ፣ ሳንከፋፈል፣ ተስፋ ሳንቆርጥ መደገፍ ይጠበቅብናል።