አቡጊዳ – የተባበሩት መንግስታት የፀጥታዉ ምክር ቤት በኢሳያስ አፈወርቂ አገዛዝ ላይ ጠንካራ አቋም ወሰደ !

ምክር ቤቱ እንደ ፈረንጆች አቆጣጠር ዛሬ ሰኞ ዲሴምብር 5 ቀን 2011 ዓ.ም፣ ባደረገዉ ስብሰባ የኤርትራ መንግስት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ለሽብር ፈጣሪዎች በተለይም በሶማሊያ ለሚገኘዉ የአልሻባብ አሸባሪ ቡድን የሚሰጠዉን ድጋፍ፣ በአስቸኳይ እንዲያቆም ያስጠነቀቀ ሲሆን፣ ከኢትዮጵያና ከጅቡቲ ጋር ኤርትራ ያላትን የድንበር ግጭትም በሰላም እንድትፈታ ጥሪ አቅርቧል።

ምክር ቤቱ ባወጣዉ ሕግ 2023 ፣ የኤርትራ መንግስት ከጅቡቲ ጋር ከአራት አመታት በፊት በተፈጠረዉ ግጭት ምክንያት የተማረኩ የጅቡቲ ወታደሮችን ጉዳይ በተመለከተ፣ ግልጽ መረጃ እንዲያቀርብ የጠየቀ ሲሆን፣ ኤርትራ በግዛቷ ለተከሉ የሽምቅ ተዋጊዎች ወታደራዊ ማሰልጠኛዎች፣ ካምፖች፣ ወታደራዊና ፋይናንሻል እርዳታዎች፣ የስለላ መረጃዎች፣ የመጓጓዣ ፓስፖርቶች የመሳሰሉት .. መስጠቷን እንድታቆም አሳስቧል።

የኤርትራ መንግስት በዉጭ ከሚገኙ ትዉልደ ኤርትራዉያን የሚሰበስበዉን ግብር በመጠቀም፣ ለመሳሪያ መግዣና ለሽብር ተግባር ማዋሉን ምክር ቤቱ ያወገዘ ሲሆን፣ የኤርትራ መንግስት ትዉልደ ኤርትራኡውያንን እያስፈራራ፣ እያስጨነቀ የሚሰበስበዉን ግብር በአስቸኳይ እንዲያቆም፣ የተባበሩት መንግስታ አባል አገራትም የኤርትራ መንግስትን እያገለገሉ፣ በዉጭ ከሚኖሩ ትዉልደ ኤርትራዉያን ገንዘብ የሚሰበስቡ ግለሰቦችን ለተጠያቂነት እንዲያቀርቡ አዟል።

ምክር ቤቱ ባጸደቀዉ አዋጅ ዙሪያ አስተያየት የሰጡት በተባባሩት መንግስታት የአሜሪካን አምባሳደር ዶክተር ሱዛን ራይስ «ይህ ሕግ የአለም አቀፉ ማህበረሰብ የኤርትራ መንግስት እየፈጸመ ያለዉን፣ የአካባቢዉን ጸጥታ የማደፍረስና ሽብርተኞችን የመደገፍ ተግባራትን፣ የሚያወግዝ እንደሆነ ያሳያል» በማለት ኤርትራ ምን ያህል የተገለለች አገር እንደሆነች አብራርተዋል። « ኤርትራ፣ አለም አቀፍ ሰላምን እንዲሁም በምስራቅ አፍሪካ መረጋጋትን ለማደፍረስ ከምታደርገዉ ሕግ ወጥ ተግባር እንድትቆጠብ ፣ ዛሬ የማያሻማ ግልጽ መልእክት ለኤርትራ መንግስት አስተላልፈናል» ሲሉም አምባሳደር ራይስ አክለዋል።

የጀርመን አምባሳደር ፒተር ዊቲግ በበኩላቸዉ፣ ሕግ 2023 ግልጽ የፖለቲካ መልእክት ለኤርትራ እንዳስተላለፈ ገልጸዉ፣ ኤርትራ የአካባቢዉ ሰላም ከማደፍረስ ተግባሯ ተቆጥባ ከጎሮቤት አገሮች ጋር ችግሯን በሰላም መፍታት እንዳለባት አሳስበዋል።

በሕግ 2023 ተጨማሪ የኤኮኖሚ እቀባ እንደሌለ ያስረዱት አምባሳደር ዊቲግ የሕጉ ትኩረት ለኤርትራ የሚሰጡ እርዳታዎችና ድጋፎች ወደ አላስፈላጊ መስመሮች እንዳይዞሩ፣ ጥብቅ ክትትል፣ ተጠያቂነትና ግልጽነት እንዲኖር የሚያደርግ ሕግ እንደሆነ አስረድተዋል።

የኤርትራ መንግስት መሪ አቶ ኢሳያትስ አፈወርቂ ለተባበሩት መንግስታ ቀርበዉ ንግግር ያላደረጉ ሲሆን፣ በስፋራዉ አምባሳደራቸዉም ቀርቦ የኤርትራን መንግስት አቋም ለመግለጽ እንዳልሞከረ ታወቋል።

ከዉሳኔዉ በኋላ አስተያየት የሰጡት የኤርትራ የዉጭ ጉዳይ ሚኒስተር አቶ አሊ አብዶ «ኤርትራ ጥፋት እንደሌለብት ተረጋግጦ፣ ጥፋተኛ ተብላለች » ሲሉ የቀረበባቸዉን ክስ ከእዉነት የራቀ ሲሉ አስተባብለዋል።

የተባበሩት መንግስታት የጸጥታዉ ምክር ቤት፣ ድምጽና በድምጽ የመሻር (ቪቶ) ስልጣን የሌላቸው፣ ናይጄሪይ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ጋቦን፣ ሊባኖስ፣ ጀርመን፣ ቦዚያ ሄርዞጎቢና፣ ፖርቱጋል፣ ብራዚል፣ ኮሎምቢያና ሕንድ እንዲሁም የቪቶ ስልጣን ያላቸው ፈረንሳይ፣ እንግሊዝና አሜሪካ በዉሳኔዉ ሲስማሙ፣ ቻይናና ራሺያ ድምጽ እንዳልሰጡም ለማወቅ ተችሏል። ኤርትራን በመደገፍ ዉሳኔዉን ተቃዉሞ ድምጽ የሰጠች አንዲት አገር የለችም።

ኤርትር ከአልሻባብ በተጨማሪ፣ የኦጋዴን ነጻ አዉጭ ግንባርን፣ የኦሮሞ ነጻ አዉጭ ግንባር የተለያዩ አንጃዎችን እንዲሁም ስማቸው በስፋት የማይታወቁ የተለያዩ የሽምቅ ተዋጊዎችን የምትደግፍና የምታስታጥቅ ሲሆን፤ ይህን የተባበሩት መንግስታት ዉሳኔ ተክትሎ፣ ኤርትራ በአስመራ ያሉ የተለያዩ የሽምቅ ተዋጊ ቡድኖችን የሚጠቀሙበትን ጽ/ቤቶች ፣ ካምፖችና ማሰልጠኛዎችን መዝጋት እንደምትገደድ በጉዳዩ ላይ ያነጋገርናቸዉ አንድ የፖለቲካ ተንታኝ ይገልጻሉ። «ይህ የተባበሩት መንግስታት የፀጥታዉ ምክር ቤት ዉሳኔ፣ መሰረታቸዉን አስመራ ያደረጉ ፣ በአዲስ አበባ እየገዛ ያለዉን የኢሕዴግ አገዛዝ እንዋጋለን የሚሉ ድርጅቶችን ከፍተኛ አጣብቂኝ ዉስጥ የሚከት ነዉ » ሲሉ ያላቸዉን አስተያየት ይሰጣሉ።

የተባበሩት መንግስታት ዉሳኔ በሙሉ ለማንበብ ከዚህ ይጫኑ