ንስሀዬ፤ እኔ እንደ መለስ ዜናዊ

ሉሉ ከበደ

የሰው ልጅ በዓለም ላይ ከተፈጠረ ጊዜ ጀምሮ እስካሁን አለንበት ዘመን ድረስ፤ አዝጋሚ የሆነ የአካልና የአእምሮ ለውጥ እያመጣ ሳለ፤ ዘመናዊ ልጣኔ በድንገት ብቅ ባለበት የቅርብ ዘመን ጀምሮ  ባስተሳሰብ ረገድ እያሳየ ያለው እድገት የፈጠነ ይምሰል እንጂ፤ ስልጣኔው ከጥግ እጥግ የዓለም ክፍል እኩል ስላልተጀመረና ስላልተስፋፋ፤ ሰው በምድር ላይ ከኖረ ሶስት አራት ሚሊዮን ዓመታት በሗላም፤ አሁን ላይ ቆመን ስናየው ከሚሊዮን ዓመታት በፊት የነበረ አኗኗር በአንዱ  የዓለም ጥግ፤ ለማመን የሚያዳግት ስልጣኔ በሌላው የዓለም ጥግ አለ። ዛሬም ቅጠላቅጠል እየበጠሰ፤ ስራስር እየማሰ፤ እያደነ፤ እርቃኑን የሚኖር የሰው ልጅ አለ። ጥቂቱ ደግሞ ምድርን ለቆ፤ በመንኮራኩር ሌላ አካል ላይ አርፎ፤ ሌላ መኖሪያ መሆን የምትችል ዓለም በመፈለግ ላይ ያለ አለ።