በተስፋ የተሞሉት ቀጣዮቹ አምስት ዓመታት ‹‹ኢትዮጵያ በዓለም ፊት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ በተመጽዋችነት ስሟ አይነሳም›› አቶ ሱፊያን አህመድ

በአገሪቱ የማክሮ ኢኮኖሚ ኮሚቴ አመራር ሰጭነት የተዘጋጀው የኢትዮጵያ የአምስት ዓመት ስትራቴጂክ ፕላን (የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ) የሚሳካ ከሆነ በ2007 ዓ.ም.፡-

በአገሪቱ የማክሮ ኢኮኖሚ ኮሚቴ አመራር ሰጭነት የተዘጋጀው የኢትዮጵያ የአምስት ዓመት ስትራቴጂክ ፕላን (የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ) የሚሳካ ከሆነ በ2007 ዓ.ም.፡-

• በኢትዮጵያ ሙሉ በሙሉ የምግብ ዋስትና ይረጋገጣል
• አገሪቱ የምግብ ዕርዳታ አትጠይቅም
• የአገሪቱን ኢኮኖሚ ኢንዱስትሪው መምራት ይጀምራል
• 2395 ኪሎ ሜትር የባቡር መስመር ይዘረጋል
• 8000 ሜጋ ዋት ኢነርጂ ይመነጫል
• አንድ ቢሊዮን ዶላር ከጨርቃ ጨርቅ ገቢ ይገኛል
• ትላልቅ የግንባታ ዕቃዎች አገር ውስጥ ይመረታሉ

በከፍተኛ ባለሥልጣናት አመራር ሰጭነት በገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር ባለሙያዎች፣ በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት በኢትዮጵያ ተግባራዊ የሚደረግ ስትራቴጂካዊ የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ በሚል ስያሜ ተዘጋጅቷል፡፡

ዕቅዱ በባለሙያዎች ዓይን ሲታይ ‹‹የተጋነነ›› የሚባል ሲሆን፣ በኢትዮጵያ የምግብ ዋስትናን በቤተሰብ፣ በአካባቢና በአገር ደረጃ ሙሉ በሙሉ የማረጋገጥ ራዕይ አለው፡፡ ይህንን ለማሳካት በአገሪቱ በአሁኑ ጊዜ የሚመረተውን 18.08 ሚሊዮን ቶን የእህል ምርት በ2007 ዓ.ም. ከእጥፍ በላይ በማሳደግ ወደ 38.5 ሚሊዮን ቶን ማድረስ ነው፡፡

ይህ የሚገኘው የኤክስቴንሽን አገልግሎት ተጠቃሚ ገበሬዎችን ቁጥር ከ5.08 ሚሊዮን ወደ 14.6 ሚሊዮን በማሳደግ ነው፡፡ ከዚህ ሌላ ከውጭ የሚገባውን ማዳበሪያ በማስቀረት እዚሁ አገር ውስጥ የማምረት ዕቅድ ተይዟል፡፡

ይህ ሥራ የሚካሄደው በፕራይቬታይዜሽንና በመንግሥት የልማት ድርጅቶች ተቆጣጣሪ ኤጀንሲ ሲሆን፣ በኦሮሚያ ክልል ያዩ ወረዳ የሚገኘውን የድንጋይ ከሰል በመጠቀም የሚካሄድ ነው፡፡ ይህንን ፋብሪካ ለመገንባት ከሁለት ዓመት በፊት የወጣው ጥናት እንደሚያሳየው 730 ሚሊዮን ዶላር ይፈልጋል፡፡

ይህ ሁሉ ከተሠራ በአሁኑ ወቅት በሴፍቲኔት ፕሮግራም የታቀፉ 7.8 ሚሊዮን ሰዎች ራሳቸውን እየቻሉ ስለሚሄዱ፣ በ2007 ዓ.ም. ቁጥራቸው 1.3 ሚሊዮን ብቻ እንደሚሆን መረጃው ያመለክታል፡፡ የቡና ምርትንም በተመለከተ በ2002 ዓ.ም. ወደ ውጭ ከተላከው 319.6 ቶን ወደ 600.9 ቶን የማሳደግ ዕቅድ አለ፡፡

ባለፈው ሐሙስ ሐምሌ 29 ቀን 2002 ዓ.ም. የዕቅዱን ዝግጅት በተመለከተ መግለጫ የሰጡት የገንዘብና የኢኮኖሚ ልማት ሚኒስትር አቶ ሱፊያን አህመድ እንደገለጹት፣ በግብርናው ዘርፍ የምርት ጭማሪ አለ፣ የዕቅድ ዘመኑ ከመጠናቀቁ በፊት የአገሪቱ የምግብ ዋስትና ይረጋግጣል፡፡ ‹‹የምግብ እጥረት ቢኖር እንኳ በራሳችን ገንዘብ ገዝተን ችግሩን እንፈታለን እንጂ ወደ ዕርዳታ አንሄድም፤›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡
ዕቅዱ የኢንዱስትሪው ዘርፍ በ2002 ዓ.ም. ያስመዘገበውን የ10.2 ዕድገት ወደ 21.4 በመቶ ለማሳደግ ነው፡፡ ዘርፉ ትኩረት ያደረገው አሁን በአገሪቱ የሚመረተውን የስኳር ምርትን 314.5 ቶን፣ በ2007 ዓ.ም. ወደ 2250 ቶን ማሳደግ ነው፡፡ ይህ የሚሆነው በመንግሥት ይዞታ ሥር የሚገኙት ሦስቱ የስኳር ፋብሪካዎች ማለትም ወንጂ ሸዋ፣ ፊንጫና መተሐራ እያካሄዱ የሚገኙትን የማስፋፊያ ሥራ ሲያጠናቅቁና በአፋር ክልል እየተገነባ የሚገኘው ግዙፉ የተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ ሥራ ሲጀምር ነው፡፡ እነዚህ ፋብሪካዎች ሲጠናቀቁ ኢትዮጵያ ስኳር ወደ ውጭ በመላክ በዓመት 661.7 ሚሊዮን ዶላር ታገኛለች የሚል ዕቅድ አለ፡፡

ሌላው የጨርቃ ጨርቅ ውጤቶች ምርትን በማሳደግ በዓመት አንድ ቢሊዮን ዶላር የማግኘት ዕቅድ ነው፡፡ የቆዳና የቆዳ ውጤቶችን ምርት በማሳደግም አሁን ከሚያስገኘው 75.73 ሚሊዮን ዶላር ወደ 496.5 ሚሊዮን ዶላር የማሳደግ ዕቅድ አለ፡፡ በሲሚንቶ በኩልም አሁን በአገሪቱ የሚመረተውን 2.7 ሚሊዮን ኩንታልን ወደ 27 ሚሊዮን ኩንታል የማሳደግ ዕቅድ አለ፡፡

ከእነዚህ ዘርፎች በተጨማሪ መንግሥት በቅርብ ካቋቋመው የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ብዙ ይጠብቃል፡፡ ይህ ኮርፖሬሽን በመከላከያ ሥር የሚገኙ ዘጠኝ የኢንጂነሪንግ ፋብሪካዎች ከመከላከያ እንዲወጡ ተደርገው በሥሩ እንዲዋቀሩ ተደርጓል፡፡ ከእነዚህ በተጨማሪም በመንግሥት ቁጥጥር ሥር የሚገኙ የብረታ ብረት ፋብሪካዎችም በኮርፖሬሽኑ ሥር ተጠቃለዋል፡፡ ኮርፖሬሽኑ የተመሠረተው በ10 ቢሊዮን ብር ነው፡፡
ኮርፖሬሽኑ የተቋቋመበት ዋነኛ ዓላማ፣ በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት በአገሪቱ ግዙፍ የኮንስትራክሽን ሥራዎች ስለሚካሄዱ ነው፡፡ ከእነዚህ ውስጥ 2395 ኪሎ ሜትር የባቡር መስመር፣ የኃይድሮ ኤሌክትሪክ፣ የጂኦተርሚል፣ የንፋስ ኃይልና የመንገድ ግንባታዎች ይገኙበታል፡፡ ቀደም ሲል በአገሪቱ ይካሄዱ በነበሩ ግንባታዎች አብዛኛዎቹ ግብዓቶች ከውጭ አገር ይገቡ የነበረ ሲሆን፣ አሁን ግን በዚህ ኮርፖሬሽን አማካኝነት እዚሁ አገር ውስጥ በርካታ ግብዓቶች እንዲመረቱ ለማድረግ ነው፡፡ ‹‹ያልተወሳሰቡ ቴክኖሎጂዎችን ጨምሮ አገር ውስጥ የማናስገባቸው የሉም፡፡ እዚህ ማምረት ይቻላል ነገር ግን በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ይህንን ሁሉ እናደርጋለን፤›› በማለት አቶ ሱፊያን ለጋዜጠኞች ገልጸዋል፡፡ ‹‹የኢነርጂ፣ የባቡር፣ የመንገድ ግንባታዎችን በአገር ውስጥ አቅም ማካሄድ እንደሚቻል ካገኘነው ጥናት ተረድተናል፤›› በማለት አቶ ሱፊያን አስረድተዋል፡፡

የሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ዕቅድ እንደሚያመለክተው፣ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ተሳትፎ፣ የጤና አገልግሎት ሽፋንና ንፁህ የመጠጥ ውሃ ሽፋን መቶ በመቶ ለማድረስ ዕቅድ የተያዘ ሲሆን፣ አቶ ሱፊያን እንደሚገልጹት፣ የዕቅዱ ዘመን ማብቂያ ከምዕተ ዓመቱ የልማት ግብ ጋር አንድ ላይ የሚጠናቀቅ በመሆኑ፣ በዚያን ጊዜ ሙሉ ለሙሉ ግቡን ማሳካት ይቻላል በማለት አስረድተዋል፡፡

በዚህ ዕቅድ ላይ ከነሐሴ ሦስት ጀምሮ የመንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት ከሕዝቡ ጋር ውይይት ይቀመጣሉ፡፡ በየክልሉና በሁለቱ የከተማ አስተዳደሮች ሕዝቡን ካወያዩ በኋላ፣ በፌዴራል ደረጃ ደግሞ አራት የውይይት መድረኮች ይዘጋጃሉ፡፡ የመጀመሪያው መድረክ ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማትና ከሙያ ማኅበራት፣ ሁለተኛው ከግሉ ዘርፍ ከአሠሪና ሠራተኛ፣ ሦስተኛው ከሲቪል ማኅበራትና ከተለያዩ የተደራጁ ማኅበራት ጋርና አራተኛው ደግሞ ከለጋሾች ጋር ይሆናል፡፡

ይህ ዕቅድ ውይይት ተደርጎበት ሲያበቃ በአዲሱ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአገሪቱ የአምስት ዓመት ፕሮግራም ሆኖ ይፀድቃል፡፡
ይህ ዕቅድ ተግባራዊ ከሆነ፣ ‹‹ኢትዮጵያ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ በዓለም ፊት በተመጽዋችነት ስሟ አይነሳም፤›› በማለት አቶ ሱፊያን ተስፋቸውን ይገልጻሉ፡፡

የማክሮ ኢኮኖሚ ኮሚቴው የሚመራው በገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስትሩ አቶ ሱፊያን አህመድ ሲሆን፣ በሥሩ እሳቸውን ጨምሮ አራት ከፍተኛ ባለሥልጣናት አባላት አሉት፡፡ እነሱም የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ ግርማ ብሩ፣ የጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ የኢኮኖሚ አማካሪ አቶ ነዋይ ገብረ አብና የብሔራዊ ባንክ ገዥ አቶ ተክለ ወልድ አጥናፉ ናቸው፡፡