ከ3 ቀናት በኋላ የአዉሮፓ ሕብረት ታዛቢ ቡድን ሪፖርቱን ይፋ ያደርጋል
ዓርብ ጥቅምት 26 ቀን 2003 ዓ.ም
የአዉሮፓ ሕብረት የምርጫ ታዛቢ ቡድን ሰኞ ጥቅምት 29 ቀን 2003 የመጨረሻ ሪፖርቱን ይፋ ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል። ሪፖርቱ በኢትዮጵያ የተደረገዉን የ2002 ምርጫ፣ የአለም አቀፍ መስፈርትን ያላሟላ እንደሆነና ዲሞክራሲያዊ ወይንም ፍትሃዊ ተደረጎ ሊቆጠር እንደማይችል፣ መረጃዎችን በመዘርዘር በስፋት እንደሚተነትን ብዙዎች ይናገራሉ።
ይህ የአዉሮፓ ሕብረት የታዛቢዎች ቡድን የምርጫ 2002 ሪፖርቱን ካጠናቀቀ ሳምንታት ቢሆኑትም እስከአሁን ድረስ በሚስጥር ይዞት እንደቆየ የሚገልጸዉ የደረሰን ዘገባ ፣ ከዚህ በፊት በነበሩ መርጫዎች እንደተደረገዉ ሪፖርቱን በአዲስ አበባ ለማቅረብ ፍልጎት ቢኖረዉም፣ የኢሕአዴግ መንግስት ግን የታዛቢ ቡድኑን ለመቀበል ፍቃደኛ ስላልሆነ፣ ሪፖርቱ በብራሰልስ ቤልጂየም ይፋ እንደሚሆን ዘገባዉ አክሎ ይጠቁማል።
በቅርቡ ሂዉመን ራይት ዋች የተሰኘዉ የሰብዓዊ መብት ተከራካራ ድርጅት፣ ባደረገዉ ሰፊ ጥናት፣ የመለስ አገዛዝ ከአለም አቀፍ ማህበረሰብ የሚሰጠዉን እርዳታ ለፖለቲካ ጥቅም እንደሚያዉለዉና ኢሕአዴግን የማይደግፉና ያልመረጡ ዜጎች የምግብ እርዳታ እንደማያገኙ ማተቱ ይታወቃል። ከዚህም የተነሳ በአለም አቀፉ ማህበረሰብ ዘንድ ከፍተኛ ተቃዉሞና ወገዛ አቶ መለስ እየደረሰበት ሲሆን በአለም አቀፍ መድረክም እንዲያቀረቅር ተደርጓል።
ከጥቂት ቀናት በኋላ ይፋ የሚሆነዉ የአዉሮፓ ሕብረት የምርጫ ታዛቢ ቡድን የመጨረሻ ሪፖርትም፣ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንደሚባለዉ፣ አቶ መለስ በማጭበርበርና የዲሞክራሲ ካባ በመልበስ ያገኛትን ትንሽ አለም አቀፍ ድጋፍ በእጅጉ እንደሚሸረሽር ተንታኞች ይናገራሉ።
ላለፉት በርካታ ሳምንታት የመለስ አገዛዝ በሂዉመን ራይትስ ላይ የፖጋንዳ ዘመቻ እንደከፈተ ያስታወሱት ያነጋገርናቸዉ አንድ የፖለቲካ ተንታኝ በአዉሮፓ ሕብረት ታዛቢ ቡድን ላይም ተመሳሳይ የስም ማጥፋት ዘመቻ ከመለስ አገዛዝ እንደሚጠብቁ ይናገራሉ። «እነዚህ አለም አቀፍ ድርጅቶች አቶ መለስ የለበሰዉ የዲሞክራሲ ካባ ነዉ የገፈፉት። በመሆኑም እነርሱን በአሁኑ ወቅት እንደጠላት ነዉ የሚያያቸዉ ። እነርሱ አልጠየቁትም። እርሱ ራሱ ነዉ የጋበዛቸዉ። አሁን መስማት የማይፈልገዉን ከአሁን ለአሁን ይናገራሉ ብሎ አዲስ አበባ እንዳይገቡ መከልክሉ ምን ያህል ሰዉየዉ የኋላ ቀርና አምባገነን ባህሪ ያለዉ እንደሆነ የሚያሳይ ነዉ» ሲሉ አሁን በኢትዮጵያ የአንድ ፓርቲ አምባገነንነት ብቻ ሳይሆን ከዚያ በባሰም የግለሰብ አምባገነንነት እንደሰፈነ ያስረዳሉ።
በተያያዘ ዜና በአገዛዙ አካባቢ ካሉ ምንጮቻን የደረሰን ዘገባ እንደሚያመልክተዉ በደርግ ጊዜ የኮሎኔል መንግስቱ ኃይለማሪያም ፎቶ በየቦታዉና በየቢሮዉ ይሰቀል እንደነበረዉ ሁሉ፣ አሁን የአቶ መለስ ዜናዊን ፎቶ መስቀል እየተጀመረ እንደሆነ ለማወቅ ችለናል።
በቅርቡም ሲኖዶሱ ቦሌ መድሃኔ ዓለም አካባቢ የተተከለዉን የአባ ጵዉሎስ ሃዉልት እንዲፈርስ መወሰኑ ይታወቃል። «የባሌ ሃዉልት ሳይሰራ እንዴት የቄሱ ይሰራል ? » በሚል ወ/ሮ አዜብ ትልቅ ቅሬታና ንዴት እንደነበራት የሚገልጸዉ የደረሰን ዘገባ፣ የአባ ጳዉሎስ ሃዉልት እንዲፈርስ በተወሰነዉ ዉሳኔ ጀርባ፣ ወ/ሮ አዜብ ልትኖርበት እንደምትችልም አክሎ ያትታል።
አቶ መለስና ወ/ሮ አዜብ፣ ሙሉ ለመሉ ፖለቲካዉንና ኢኮኖሚዉን እንደሚቆጣጠሩ፣ ኢሕአዴግ ወይንም ሕውሃት የሚባል ነገር በስም እንጂ በተግባር እንደሌለ፣ አሁንም በኢትዮጵያን የሰፈነዉ የቤተሰብ አምባገነንነት እንደሆነ ለብዙዎች ከቀን ወደ ቀን ግልጽ እየሆነ እየመጣ ሲሆን፣ ይህም በደርግ ጊዜ እንደነበረዉ፣ በአገዛዙ ባለሥልጣናት መካከል ትልቅ አለመተማመንና መፈራራትን ማስከተሉንም ብዙዎቻ ያናገራሉ።