የኖርዌይ መንግስት ኦዲተር ጄኔራል የአገሪቱን የእርዳታ ቁጥጥር ሂደት አወገዙ

ኖርዌይ በምግብ ፕሮግራሞች እና በህጻናት እርዳታ ስም የምትለግሰውን ገንዘብ ከሙስና እና ከምዝበራ ለመከላከል የአገሪቱ እርዳታ ሰራተኞች በቂ ስራ እየሰሩ አይደለም ሲሉ የኖርዌይ ኦዲተር ጄኔራል ማውገዛቸው ተዘግቧል።

“ሂውማን ራይትስ ዋች” በቅርቡ ባወጣው ሰፊ ሪፖርት፣ ምእራባውያን በድሆች ስም ለወያኔ አገዛዝ የሚሰጡት እርዳታ ለአፈና ስራ እየዋለ እንዳለ ማጋለጡን መዘገባችን ይታወሳል። ኖርዌይ ከነዚህ ለጋሽ አገራት ውስጥ አንዷ ስትሆን፣ ባለፈው አመት ብቻ ከ41 ሚሊዮን ዶላር በላይ ለዘረኛው እና አምበገነናዊው የወያኔ አገዛዝ መስጠቷ ታውቋል።

“ሂውማን ራይትስ ዋች” በሪፖርቱ ኖርዌይ በአሁኑ ሰዓት ለኢትዮጵያ የምታደርገውን የእርዳታ አሰጣጥ አውግዞ፣ ሂደቱን እንድታሻሽል ጥሪ አቅርቧል። ኖርዌይ ለኢትዮጵያ የምትሰጠው ገንዘብ ለተባለለት ተግባር መዋል አለመዋሉን የምትቆጣጠርበት መንገድ እንደሌላት ለማወቅ ተችሏል።

የኖርዌይ የአካባቢ ጥበቃና የውጭ እርዳታ ሚኒስቴር ሶልኸም ጉዳዩን ያስተባበሉ ቢሆንም፤ የኦዲተር ጄነራሉን ሂስ ተከትለው ክትትል እንደሚያደርጉና ስህተቶችን ለማስተካከል እንደሚሞክሩ ገልጸዋል።

በተያያዘ ዜና የስዊድን መንግስት ለኢትዮጵያ የሚሰጠውን እርዳታ ሊቀንስ ነው ሲል የኢትዮጵያ ወቅታዊ ጉዳዮች መወያያ መድረክ የተባለው ድረ-ገጽ ዘግቧል። ድረ-ገጹ የስዊድን መንግስት በኢትዮጵያ ባለው የፖለቲካ ሁኔታ ለረዥም ጊዜ ደስተኛ እንዳልነበረ ገልጿል። ዘረኛውና አምባገነናዊው የመለስ ዜናዊ አገዛዝ በስዊድን ያለው የኢትዮጵያ ኤምባሲ እንዲዘጋ ማዘዙ ይታወቃል።