የእምነት ነፃነት፤ የሰብዓዊ መብቶች አካል ነው

በዓለም ዓቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ድንጋጌ አንቀጽ 18 መሠረት እያንዳንዱ ሰው በግሉም ሆነ በጋራ የፈለገውን ሃይማኖት የመከተልና የማስተማር፤ ያልፈለገውን ደግሞ የመተው መብት አለው።

እንደሚታወቀው፤ ሰብዓዊ መብቶች እርስ በርሳቸው የተቆራኙ፤ እርስ በርሳቸውም የሚደጋገፉ ናቸው። አንዱ የመብት ዓይነት ሲጓደል፤ ሌላውም አብሮ ይጓደላል። ለምላሴ የመናገር መብት ተገፎ እያለ የማምለክ መብት ሊፋፋ አይችልም፤ ወይም ደግሞ ፍትሃዊ ዳኝነት የማግኘት መብት ተጥሶ እያለ የማምለክ መብትን የሚያስከብር ተቋም ሊኖር አይችልም። ለዚህም ነው ሰብዓዊ መብቶች የማይነጣጠሉ ናቸው የሚባለው።

በአገራችን እየተባባሰ የመጣው በእምነት ላይ ያለው ግልጽ አፈና በአጠቃላይ በሰብዓዊ መብቶች ላይ ያለው አፈና አንድ ዓይነተኛ መገለጫ ነው። አገዛዝ በሰፈነበት ሥርዓት ውስጥ ሰብዓዊ መብቶችን ማስከበር የነበረባቸው ተቋማት ሰብዓዊ መብቶችን መርገጫ እንደሚሆኑ በመለስ ዜናዊ አገዛዝ ሥር ያለችውን አገራችንን ማየት በቂ ነው። በአገዛዙ ሥር ያሉ ፍርድ ቤቶች እየሠሩ ያሉት ምንድነው? ምንድነው “የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን” እየሠራ ያለው? ምንድነው “የሕዝብ እንባ ጠባቂ ኮሚሽን” እየሠራ ያለው? ምንድነው ፓሊስ፣ ምርጫ ቦርድና ፓርላማ እየሠሩ ያሉት? ጥያቄዎቻችንን መቀጠል እንችላለን። ምላሹ ግን አንድ ነው። እነዚህ መሰል ተቋማት በአገዛዝ ሥር ሲወድቁ የሰብዓዊ መብቶች መርገጫ እንጂ ማስከበሪያ ሊሆኑ አይችሉም። በመለስ ዜናዊ ዘረኛ አገዛዝ ውስጥ ደግሞ እነዚህ ተቋማት የአፈና ብቻ ሳይሆን የዘረኝነትም ማስፋፊያ ናቸው።

የአገዛዝ ሥርዓት አፈናውን ባጠናከረ መጠን የመንግሥት ተቋማትን ብቻ ሳይሆን ማኅበራዊ ተቋማትንም ጭምር የጭቆናው መሣሪያ ያደርጋቸዋል። ለዚህ ደግሞ ገሃድ ምሳሌ የሃይማኖት ተቋማቶቻችን ናቸው።

የመለስ ዜናዊ አገዛዝ በኢትዮጵያ ውስጥ በሚገኙ በሁሉም ሃይማኖቶች ተቋማት ውስጥ የራሱን ካድሬዎች በመሾም ምዕመናኑን ለመቆጣጠር ጥረት ማድረግ የጀመረው ሥልጣን ኮርቻ ላይ ከወጣበት ጊዜ ጀምሮ ነው። ከዚያ ጊዜ ጀምሮ የእምነት ተቋማት መሪዎች ከእምነት መሠረታዊ መርሆዎች ያፈነገጡ ተግባራትን ሲተገብሩ ማየት እጅግ የተለመደ ነገር እየሆነ መጥቷል።

በእምነቶችና በእምነት ተቋማት ላይ እየደረሰ ያለው በደል ሁሉንም ሃይማኖቶች ያዳረሰ ቢሆንም በአሁኑ ወቅት በእስልምና ሃይማኖትና በሙስሊም ማኅበረ -ሰብ ላይ እየደረሰ ያለው አፈና ግን ከሁሉም የከረረ እና የመረረ ሆኗል። የመለስ ዜናዊ አገዛዝ የመጅሊስን አመራር በራሱ ካድሬዎች ከማስያዝ በላይ በዝርዝር ሃይማኖታዊ አስተምህሮት ውስጥ በመግባት አንዱን ጀማ ወዳጅ፤ ሌላኛውን ደግሞ ጠላት እያደረገ ነው።

ዘረኛው አገዛዝ የተለያዩ ሃይማኖቶች ተከታዮችን ከማጋጨት አልፎ በአንድ ሃይማኖትም ውስጥ የተለያዩ ጎራዎች እንዲፈጠሩና እርስ በርሳቸው እንዲጋጩ እያደረገ ነው። ይህ አካሄድ እጅግ ክፋት የተሞላበት ውጤቱም አደገኛ የሆነ ነገር ነው።

ለምንድነው የመለስ ዜናዊ አገዛዝ በአሁኑ ሰዓት በተለይ በእስልምና ሃይማኖትና በሙስሊም ማኅበረሰብ ላይ ያነጣጠረው? ለዚህ በርካታ ምክንያቶች ቢኖሩም የሚከተሉት ሁለቱን ብቻ ማንሳት ይበቃል።

  1. መለስ ዜናዊ “ሙስሊም ለፓለቲካ ደንታ የለውም” የሚል የትዕቢት አስተሳሰብ ተቆራኝቶት ቆይቷል። ሆኖም ግን እያለቀ ባለው የአውሮፓውያን ዓመት በሰሜን አፍሪቃና መካከለኛው ምሥራቅ እየታዩ ያሉ ለውጦች መለስንና የመለስ ዓይነት ሰዎችን መግቢያ ቀዳዳ አሳጥቷቸዋል። የሰሜን አፍሪቃና መካከለኛው ምሥራቅ አብዮቶች ሙስሊም ወገኖቻችን ለፍትህና ለዲሞክራሲ ያላቸውን ጥማት ብቻ ሳይሆን ቁርጠኝነታቸውንም አጉልቶ አሳይቷል። መለስ ዜናዊና ጋሻ ጃግሬዎቹ አሻግረው እያዩት ያለው ሕዝባዊ ማዕበል እንዳይውጣቸው መፍትሄ አድርገው ያቀረቡት ሙስሊሙን መከፋፈል ነው።
  2. የመለስ ዜናዊ ዘረኛ ቡድን በተለያዩ ሃይማኖቶች መካከል የከረረ ጥል ለመፍጠር ያልቆፈረው ጉድጓድ የለም። በተለይም ሙስሊሙንና ክርስቲያኑን ማኅበረሰብ ለማቃቃር ብዙ ጥሯል። በሰኔ 2001 በደሴ አርሴማ ቤተክርስቲያን ግንባታ ሰበብ ሆነ ብሎ ያስነሳው ጠብ አንዱ የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው። ሆኖም ግን መለስ ዜናዊና ዘረኛ ቡድኑ በፈለጉት መጠን ኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞችና ክርስቲያኖች አልተጣሉም። ጊዜዓዊ ግጭቶችም በተከበረው አገራዊ የሽምግልና ባህል እየተፈቱ እርቅ የሚወርድ በመሆኑ መለስ አዲስ እና የከፋ ዘዴ መሸረብ ነበረበት። አዲሱ ዘዴ፣ የእያንዳንዱ ሃይማኖት አማኝ እራሱ ከራሱ ጋር እንዲጣላ ማድረግ ሆነ።

ግንቦት 7: የፍትህ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ አሁን የመለስ ዜናዊ ዘረኛ አገዛዝ በእስልምና ሃይማኖት ላይ እየተሞከረ ያለው አደገኛ ጣልቃ ገብነትን አጥብቆ ይቃወማል። አደጋው በእስልምና ብቻ ሳይሆን በሌሎችም ሃይማኖቶችም ላይ ነው፤ በእስልምና ላይ እየተሞከረ ያለው ከተሳካ ነገ ወደሌሎቹም ይዛመታል።

ከሁሉም በላይ ደግሞ የአምልኮት ነፃነት ማጣት የሰብዓዊ መብት እጦት መሆኑን ሁላችንም መረዳት ይኖርብናል። መፍትሄም የሚገኘው በተናጠል ሳይሆን በጋራ ነው። ልናስከብረው የሚገባ መብትም ሰብዓዊ መብቶችን በሙሉ ነው።

የመለስ ዜናዊ ዘረኛ አገዛዝ ተወግዶ ዲሞክራሲያዊ እና ፍትሃዊ ሥርዓት ሳይገነባ ሰብዓዊ መብቶች መከበር የማይችሉ በመሆኑ ትኩረታችን በዋነኛው የጋራ ጠላታችን በሆነው የመለስ ዜናዊ ዘረኛ አገዛዝ ላይ መሆን ይኖርበታል።

ሙስሊሙ ወገናችን፣ ሰብዓዊ መብቶች ሳይከበሩ የሃይማኖት ነፃነት ብቻውን መከበር የማይችል መሆኑን ተረድቶ መለስ ዜናዊን ለማስወገድ በምናደርገው የጋራ ትግል በጽናት እንዲቆም ግንቦት 7 ጥሪ ያደርጋል።

የመለስ ዜናዊ ዘረኛ አገዛዝ ሳይወገድ ሰብዓዊ መብቶችን ማስከበር ስለማንችል አንድነታችንን አጠንክረን የነፃነት ትግላችንን እናፋፍም።

ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!!