በጀርመን የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን በፋሽስቱ መለስ ዜናዊ አገዛዝ የታሰሩ የፖለቲካ እስረኞች እንዲፈቱ በሰላማዊ ሰልፍ ጠየቁ
እንደ ፈረንጆች አቆጣጠር ከትናንትና ወዲያ ማክሰኞ ኖቨምበር 29 ቀን በፍራንክፈርት ጀርመን የተቃውሞ ሰልፉን ያካሄዱት ኢትዮጵያዊያን፤ የመለስ ዜናዊ አገዛዝ በአገራችን ውስጥ እየፈጸመ ያለው ገደብ የለሽ ግፍና ሰቆቃ እንዲቆም ለመጠየቅ መሆኑን የሰልፉ አስተባባሪዎች መናገራቸውን ዘጋቢያችን ከስፍራው በላከልን ዜና ገልጾአል።
የተቃዋሚ ፓርቲዎችን እንቅስቃሴ ለመግታት በፓርቲ መሪዎች፤ በአባላቶቻቸውና ነጻ ጋዘጤኞች ላይ እየተወሰደ ያለውን እስርና እንግልት አጥብቀን እንቃወመዋለን ያሉት ሰልፈኞች፤ ከጀርመን ግብር ከፋይ ህዝብ ተስብሰቦ በሚሰጥ ገንዘብ ወያኔ እየፈጸመ ያለውን ወንጀል የጀርመን መንግሥትና ህዝብ እንዲገነዘብ ለማስቻል በጀርመንኛ ቋንቋ የተዘጋጀ ደብዳቤ ቅጂ ለብዙ ሺ ህዝብ በትነዋል።
መለስ ዜናዊ ለፍርድ ይቅረብ፤ መለስ ዜናዊ ነፈሰ ገዳይ ነው፤ መለስ ዜናዊ ሽብርተኛ ነው፤ ሞት ለመለስ ዜናዊ፤ ሞት ለወያኔ መሪዎች፣ የታሰሩት ንጹሀን ዜጎች ይለቀቁ፣ የመሬት ሽንሸናው ይቁም፣ ጀርመን አምባገነኖችን አትርጂ የሚሉና ሌሎችም በርካታ መፈክሮች በእለቱ ሰላማዊ ሰልፍ ላይ ተስተጋብተዋል።
ኢትዮጵያኑ ከዚህ ቀደም በኑረምበርግ ተመሳሳይ የተቃውሞ ሰልፍ ያካሄዱ ሲሆን፣ በሚቀጥሉት ሳምንታትም በዋና ከተማዋ በርሊን ተመሳሳይ ሰልፍ ለማድረግ ዕቅድ እንዳላቸው የደረሰን ዜና ያመለክታል።
የመለስ አገዛዝ ሰለማዊ ዜጎችንና የነጻነት ታጋዮችን አንዴ በአሸባሪ ሌላ ጊዜ በአገር ክዳት ወንጀል ስም ማሰሩ አለማቀፍ ውግዝት እያስከተለበት ነው።
የአለማቀፉ የጋዜጠኞች መብት ተንከባካቢ ድርጅት ሲፒጄ ፣ ሂውማን ራይትስ ወች እና አምነስቲ ኢንተርናሽናል የመለስ አገዛዝ ሀሳብን በጉልበት ለማፈን የሚደረገውን ሙከራ መቃወማቸው ይታወሳል።
ይህ በዚህ እንዳለ፣ በዴንቨር ኮለራዶ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የወያኔ ባለስልጣናት ለአባይ ግድብ ማሰሪያ ቦንድ ለመሸጥና አዲሱን የዲያስፖራ ፖሊሲ ለማስተዋወቅ ላለፈው እሁድ ጠርተውት የነበሩት ስብሰባ እንዳይሳካ ማድረጋቸውን ከስፍራው የተላከልን ዜና ገለጸ።
በወያኔ አምባሳደር ተበጀ በርሄ የተመራው የልኡካን ቡድን ያቀደውን ስብሰባ በተሳካ ሁኔታ ሳይፈጽም፣ በአካባቢው በሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በደረሰበት ተቃውሞ ወደ ዋሽንግተን ዲሲ መመለሱን የገለጸው ዘጋቢያችን፤ የወያኔን ተላላኪዎች ለማሰባሰብ እቦታው ድረስ ተጉዞ የነበረው ተበጄ በርሄ ስበሰባው የህዝብ ስብሰባ እንዳልሆነ በማስታወቅ በስፍራው የነበሩት ተቃዋሚዎች አካባቢውን ለቀው እንዲሄዱ ለፖሊስ ጥያቄ አቅርቦ የነበረ ቢሆንም ኢትዮጵያውያኑ ግን ተቃውሞአቸውን በመቀጠላቸው ስብሰባው ያለውጤት ለመበተን ችሎአል።
በሰሜን አመሪካ የሚኖሩ ኢትይጵያዊያን የፋሽስቱ ወያኔ ተላላኪዎች በስደት የሚኖረውን ኢትዮጵያዊ ለመከፋፈል የተሸረበውን ተንኮል በመከታተል እያከሸፉ እንደሚገኝ ለማወቅ ተችሎአል።