በኢትዮጵያ ጉዳይ ሰፊ ጥናት ያካሄዱና የተለያዩ መጽሃፎችን የጻፉ ታዋቂው የፖለቲካና ታሪክ ምሁር ጆን ማርካኪስ ፣ ህወሀት መራሹ አገዛዝ ከደርግና የሀይለስላሴ ስርአቶች ውድቀት ለመማር ባለመቻሉ፣ እሱም በተራው ወደ ውደቀት እየተጓዘ ነው አሉ

ለረጅም ጊዜ በአገራችን ፖለቲካ ሰፊ ጥናት ያካሄዱት ጆን ማርካኪስ “ኢትዮጵያ፣ ዘ ላስት ቱ ፍሮንቲየርስ” የሚለውን አዲሱን መጽሀፋቸውን ለማስተዋወቅ በለንደን ቻትሀም ሀውስ በተገኙበት ወቅት ህወሃት መራሹ የመለስ ዜናዊ አገዛዝ ስልጣን በበቂና ተጨባጭ በሆነ መልኩ ወደ ክልሎችና ወደ ወረዳዎች ለማስተላለፍ ባለመቻሉ፣ የመፈረካከስ አደጋ ተጋርጦበታል ብለዋል።

በዚህ ስነሥርዓት ላይ ተመሳሳይ ንግግር ያደረጉት ሌላው ታዋቂ ምሁር ፕሮፌሰር ክርስቶፈር ክላፋም የኢትዮጵያ መንግሥት  እጅግ አሳዛኝ የሆነ መንግስት ነው ብለውታል።

ኢትዮጵያ በውስጥና በአካባቢው ተጽኖ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ አገደኛ ሁኔታ ውስጥ እንደምትገኝ የገለጡት ምሁሩ፣ ህወሀት እጅግ ፈላጭ ቆራጭ በሆነ መንገድ በስልጣን ላይ ለመቆየት የሚያደርገው ጥረት፣ የኢትዮጵያን መጻኢ እድል አደጋ ላይ ጥሎታል ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

ሁለቱ ምሁራን ያቀረቡት ጽሁፍ የብሄር ብሄረሰቦችን መብት አክብሬያለው፣ ፌደራሊዝምን ተግባራዊ አደርጋለሁ፣ የኢትዮጵያን አንድነት ከመቼውም ጊዜ በላይ አስጠብቄያለሁ ለሚለው ወያኔ ኢህአዴግ፣ ትልቅ የዲፕሎማሲያዊ ውድቀት እንደሚያስከትልበት አስተያየቶች ቀርበዋል።

ፕሮፌሰር ክላፋም በእንግሊዞች ፖለቲከኞች ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነት ካላቸው ምሁራን አንዱ ናቸው።