ወያኔ በመላው አገሪቱ የፍርሃት ድባብ ለማስፈን ሲል በውሸት አቀነባብሮ በቴሌቪዥን ያሰተላለፈው የአኬልዳማ ድራማ ብዙዎችን እያነጋገረ መሆኑ ተገለጸ

የዘረኛው መለስ ዜናዊ አገዛዝ እየፈጸመ ያለውን የአገር ሃብት ዘረፋና የስልጣን ብልግና በመቃወም የመንግሥት ለውጥ እንዲመጣ በህጋዊ መንገድ ተመዝግበው በመንቀሳቀስ ላይ ያሉትን የፖለቲካ ድርጅቶች ለማጥፋት ሲባል በ3 ተከታታይ የቴሌቪዥን ፕሮግራም ተቀነባብሮ የተላለፈው የፈጠራ ድራማ ህዝብን በሰፊው እያነጋገረ መሆኑን የግንቦት 7 ዘጋቢ ከአዲስ አበባ በላከው የህዝብ አስተያየት ገለጸ።

አኬልዳማ የሚል መጠሪያ የተሰጠው ድራማ በክፍል አንድና ሁለት ኦነግና ኦብነግ ፈጽመውታል የተባለውን ግዲያዎች ቅንብር ያስተላለፈ ሲሆን በክፍል ሶስት ደግሞ ግንቦት7 በአገር ውስጥ እየዘረጋው ነው የተባለውን ድርጅታዊ መዋቅር ምንነት ለማሳየት የሞከረ ነበር።

በአዲስ አበባና ሌሎች ትላልቅ ከተሞች ከሚኖሩት የህብረተሰብ ክፍሎች በዘጋቢያችን የተሰባብሰቡ የህዝብ አስተያየቶች እንዳመለከቱት፤ ወያኔ የራሱን የአገዛዝ ዕድሜ ለማራዘም ድህረ ምርጫ 97 በአዲስ አበባና ሌሎች ትላልቅ ከተሞች ባሰማራው የአጋዚ ጦር በጠራራ ጸሃይ የጨፈጨፉቸው ሰላማዊ ዜጎች ትውስታ ገና ከህዝብ አዕምሮ ሳይፋቅ በማን፤ መቼና የት ቦታ እንደተፈጸመ በውል ያልተገለጹ የህጻናት ግዲያዎች በኦነግና ኦብነግ ተፈጽመዋል ተብለው በምስል ቅንብር በቴለቪዥን መቅረቡ አገዛዙ የገባበትን የስነልቦና ኪሳራና ውድቀት ማሳየት የቻለ ነው።

የአጋዚ ጦር የሰጠው ማስፈራሪያ ምንንነት በደንብ ሳይገባው ይጫወትበት የነበረውን የጨርቅ ኳስ ሩጦ ለመውሰድ ሲንደረደር የነበረውን የ10 አመቱን ህጻን ነቢዩን ጨምሮ ወደትምህርት ቤት ይሄዱ የነበሩትን 13ና 14 አመት ታዳጊዎች ባንክ ሊዘርፉ ነው በሚል የፈጠራ ወንጀል ጭንቅላታቸውን በጥይት አስቦጭቆ ያስገደለው መለስ ዜናዊ፤ ለዜጎች ህየወት ተቆርቋሪ መስሎ ለመታየት ያሰራው የአኬልዳማ ቅንበር የታሰበለትን አላማ ለማሳካት ያልቻለ የተለመደ የወያኔ ቅጥፈት ተደርጎ መወሰዱን ዘጋቢያችን አረጋግጦአል።

ኦነግ በሚከሰስበት የበደኖ ግዲያ ወቅት ሥልጣን ላይ የነበረው የመለስ ዜናዊ አገዛዝ የህዝብ ወገንተኛነት ቢኖረው ኖሮ የተገደሉትን ሰዎች ምስል በፊልም የሚቀርጽ ሃይል በቦታው ከማሰማራት ይልቅ ወንጀሉን ለመከላከል አስፈላጊውን እርምጃ መውሰድና ተጠያቂዎቹንም ህግ ፊት የማቅረብ ግዴታ ነበረበት የሚሉት አስተያየት ሰጪዎች፤ ኦነግ በተገንጣይነት ከወያኔ ጋር የነበረው ተመሳሳይ አጀንዳ በሂዴት ተለውጦ ከአንድነት ሃይሎች ጋር መቀራረብ በመጀመሩ በተፈጠረ ድንጋጤና ጭንቀት፤ በአለም አቀፍ የሚዲያ ህግ የተከለከለ አሰቃቂና ዘግናኝ ምስሎችን ለህዝብ እይታ ለማቅረብ ችሎአል ብለዋል።

በአኬልዳማ ክፍል ሶስት የተቀነባበረው ድራማ እንዳመለከተው፤ አገር ውስጥ ተመዝግበው በሰላማዊ የትግል ስልት መንግሥት ለመቀየር የሚንቀሳቀሱ ፓርቲ መሪዎችና አባላት አለአግባብ ከታሰሩ ቦኋላ ለመስከረም 24 ተጠርቶ የነበረው ህጋዊና ሰላማዊው የተቃውሞ ሰልፍ “ነውጥና ሽብር በአገሪቱ ውስጥ ለማነሳሳት የተዘጋጀ” ነው በማለት በዱላና ሌሎች ወያኔያዊ የጥቃት እርምጃ ተገደው እንዲመሰክሩ የተደረገበት መሆኑ ብዙዎችን በማስቆጣት ለትግል እያነሳሳቸው ነው ተብላኦል።

ወያኔ ባላሰበው ሰዓትና ጊዜ ሊፈነዳ ይችላል ብሎ የሚፈራው ህዝባዊ አመጽ እንዳይቀሰቀስ ዜጎችን በሙሉ በፍርሃት ቆፈን ውስጥ ለመክተት ተብሎ በተቀነባበረው በዚህ የአከልዳማ ክፍል ሶስት ቅንብር ፤ግንቦት 7 የወያኔን መሪዎች ምን ያህል እረፍት እየነሳው የመጣ ድርጅት እንደሆነ በግልጽ የተመሰከረበት በመሆኑ ፤ የነጻነት ትግሉን ሊመራ የሚችል ፓርቲ ገና ያላገኘ መስሎት በፍርሃትና ተስፋ መቁረጥ አንገቱን ደፍቶ የነበረው ህዝብ እንዲነቃቃና እንዲጽናና አስችሎታል ብሎአል የግንቦት 7 ዘጋቢ መረጃ።

በአኬልዳማ ድራማ ላይ “በግንቦት 7 ታዝዤ ነውጥ ለመቀስቀስ ስንቀሳቀስ ነበር ብሎ” ቃላቸውን እንዲሰጡ ከተደርጉት መካከል በሽብርተኛነት ክስ መዝገብ በ5ተኛ ተራ ቁጥር ተከሳሽ የሆነው ክንፈሚካኤል ደበበ በረደድ (አበበ ቀሲቶ) በትናትናው ዕለት በዋለው የወያኔ ችሎት ፍት ቀርቦ እምነት ክሀደት ቃሉን በተጠየቀበት ወቅት ”ክቡር ፍርድ ቤት እዚህ የክሥ ቻርጅ ላይ የተዘረዘሩትን ተረታ ተረቶች አልፈጸምኩም፣ ወደፊትም አልፈጽምም፤ መንግሥት የእኛን ብቻ ሳይሆን የፍርድ ቤቱን ክብር ነው ያሳጣው- በፍርድ ቤት ሥራ ጣልቃ እየገባ‘ በማለት መልሥ እንደሰጠ የደረሰን ዜና ያስረዳል።

በትናትናው የፍርድ ቤት ውሎ የ እመነት ክህደት ቃላቸውን ከተጠየቁት መካከል፡ 1ኛ ተከሳሽ የአንድነት ፓርቲ ምክትል ሊቀመንበርና የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አንዷለም አራጌ ”ይህ በኢትዮጵያ ሠላማዊ ትግልን ለማፈን የተዘጋጀ የውሸት ድሪቶ ነው፤ እኔ ምንም አይነት ወንጀል አልፈጸምኩም…‘ ሲል ፍርድ ቤቱ በመሐል ገብቶ ዛሬ ሌላ ነገር ለመስማት ዝግጁ አይደለሁም፣ አሁን መናገር የምትችሉት ወንጀሉን ፈጽማችኋል ወይስ አልፈጸማችሁም በቃ! ሲል አቶ አንዷለም ”ይገርማል እኔ ከዚህ በፊትም ፍርድ ቤት ቀርቤ አውቃለሁ፣ ነገር ግን ይህ ፍርድ ቤት ለእኛ ፍትህ ለመስጠት የቆመ አያስመስለውም፤ የገጠመንን ኢፍትሃዊነት በተናገርን ቁጥር በጽሑፍ አቅርቡ እየተባልን አድማጭ አጥተን እንገላታለን፣ መንግሥት እኛን በእሥር ላይ አድርጎ በኢትዮጵያ ቴሌቭዥን አኬልዳማ በሚል በሦስት ክፍል ፕሮግራም የሥም ማጥፋት ዘመቻ እያካሄደብን ይገኛል፡፡‘ ብሏል።

ሁለተኛ ተከሳሽ የሆነው የአንድነት ፓርቲ አመራር አባል ናትናኤል መኮንን ”በሠላማዊ መንገድ መታገል ወንጀል ከሆነ አዎን ፈጽሜያለሁ፣ እንጂ የተባለውን የመንግሥት ድርሰት ግን አልፈጸምኩም በማለት የአላማ ጽናቱን አስመስክሮአል።

በትናትናው የወያኔ ፍርድቤት ውሎ ተከሳሾች የሰጡት ቃል በህብረተሰቡ ውስጥ ሲሰራጭ የወያኔን ማፈሪያነት ይበልጥ ይመሰክራል ህዝቡንም በ እልህ ለትግሉ ያነሳሳል ተብሎአል።