በአኬልዳማ ድራማ የሕዝብን የዴሞክራሲና የለውጥ ጥያቄ ማዳፈን አይቻልም! ከአንድነት ፓርቲ የተሠጠ መግለጫ

የአትዮጵያ ሕዝብ ላለፉት አራት አስርት አመታት በላይ ከፍተኛ መስዋትነት የሚጠይቅ ትግል ቢያደርግም ዴሞክራሳዊ ስርዓት መፍጠር አልተቻለም፡፡ ደርግን የተካው ኢህአዴግ ትምህርት ወስዶ የተሻለ ስርዓት ይገነባል ተብሎ ቢጠበቅም፣ እሱም የለየለት አምባገነንና አፋኝ ስርዓት ለመሆን በቃ፡፡ ጭቆና እንዲወገድ፣ እኩልነት እንዲረጋገጥና እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት እንዲመሠረት በሚድረግ ጥረት ሁሉም የኢትዮጵያ ልጆች ለሀገራቸው ልማትና ብልፅግና ተሳታፊ እንዲሆኑ ለማድረግ ከመስራት ይልቅ ጥላቻና አምባገነንነት የአገዛዙ የአመራር ዘይቤ ሆኖአል፡፡

ደርግ ህወሓትን“ወንበዴ”፣ “ፀረ-ሰላም” እና “አስገንጣይ” የሚል ስም ሰጥቶት እንደነበር ይታወቃል፡፡ ህወሓት/ኢህአዴግም በተራው ተቀናቃኞቹን “ፀረ-ሰላም”፣“ፀረ-ልማት” እና “አሸባሪ” ለማለት ወግ ደርሶታል፡፡ አገዛዙ ትላንት ካሳለፈው የትግል ልምድ ሊማር ያለመቻሉን በግልፅ እንረዳለን፡፡ የሕዝብን ጥያቄ በሰላይ ጋጋታና በወታደር ብዛት ማዘግየት እንጂ መጨፍለቅ እንደማይቻል ከኢህአዴግ በላይ ምሳሌ ሊሆን የሚችል ድርጅት ሊኖር አይችልም፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ አገዛዙ የተቃዋሚ አባለትና ጋዜጠኞች ላይ ሰፊ የእስርና የአፈና እርምጃ አጧጥፎ ቀጥሎበታል፡፡ የተቃዋሚፖለቲካ ፓርቲ አባላትንና የነፃው ሚድያ አባላትን ወደ እስር ቤት መወርወርና ማዋከብ የአገዛዙ የቀን ተቀን ስራ ሆኖአል፡፡ ባለፉት ሶስት ወራት ብቻ ብዛት ያላቸው ጋዜጦኞች ለእስርና ለስደት ተዳርገዋል፡፡ በቅርቡም የአውራምባ ታይምስ ጋዜጣ ማኔጅግ ኤዲተር ዳዊት ከበደ ከሀገር መሰደዳቸው ይታወቃል፡፡

አገዛዙ በአሸባሪነት ስም እየወሰደ ያለው ቅጥ ያጣና ነውረኛ ርምጃ በዜጎች ዓይን ተቀባይና አሳማኝ ሊሆን እንዳልቻለ ተረድቷል፡፡ አገዛዙ ከህዝብ ያጣውን ተቃባይነትና አመኔታ ርካሽ የሆነ ፕሮፓጋንዳ በመንዛት ሕዝብን ለማሳመን አቅዶ ተነስቷል፡፡ እንደተለመደው የኢ.ቲ.ቪ. በተከታታይ ቀናት (ከ16-18/ 2004 ዓ.ም.) “አኬልዳማ” በሚል ርዕስ የቀረበው በጥላቻና በሽብር የተሞላ መርዘኛ የሆነ ፕሮፓጋንዳ ግቡ ግልፅ ነው፡፡ በአንድ በኩል ጠቅላይ ሚኒሰትሩ በፓርላማ ተገኝተው በቂ ማሰረጃ ይዘን ነው ያሰርነው ላሉትና ይህንንም ተከትሎ በተለያየ ሁኔታ ለሚደርሰው ነቀፌታና ተፅዕኖ ድጋፍ ለመሰጠት፤ በሌላ መልኩ ደግሞ በኑሮ ውድነትና በመልካም አሰተዳደር ዕጦት የተማረረ ህዝብ በሰሜን አፈሪካና በመካከለኛው ምስራቅ ያለውን ህዝባዊ እንቅሰቃሴ ፈለግ ይከተላል በሚል ፍርሃት ቀድሞ ለማሰፈራራትና ወዮልህ ለማለት፤አልሞ የተነሣ ነው፡፡

የኢ.ቲ.ቪ. የሶስት ቀናት ፕሮፓጋንዳ እርስ በርስ የሚቃረን፣ በጥላቻ የታጨቀና ግልፅ የስም ማጥፋት ወንጀል የተፈፀመበት የወረደ ሥራ ነው፡፡ የአንድነት ፓርቲ አባላት ያልሆኑ ግለሰቦች እንደ ፓርቲው አባላት አድርጎ አቅርቦቷል፡፡ ለምሳሌ አቶ ሙሉነህ እዬኤል “የአንድነት ፓርቲ ማህከላዊ ኮሚቴ አባል የነበሩ” ብሎ በዘገባው የቀረበ ቢሆንም፣ አቶ ሙሉነህ እዮኤል ግን ፈፅሞ የአንድነት ፓርቲ አመራርም ሆነ አባል ሆነው አያውቁም፡፡ አቶ ደበበ እሸቱም ሆኑ ሌሎች መርህ ይከበር በሚል ሰማቸው የተጠቀሰ ግለሰቦች ቀደም ሲል በዲስፕሊን ጉድለት ከፓርቲው መሰናበታቸው መንግሰት በሰነድ የሚያውቀው ጉዳይ ነው፡፡ አቶ አንዱዓለም አያሌው ከምርጫ 2002 በኋላ ከፓርቲው የለቀቁ ናቸው፡፡

ዘገባው በፓርቲውና በአመራሮቹ ላይ ከፍተኛ የስም ማጥፋት ወንጀል ፈፅሟል፡፡ አንድነት ፓርቲን አሸባሪ በሚል ገልፆታል፡፡ ዘገባው “የግንቦት ሰባትን የሽብር ተልዕኮ ከሚያስፈፅሙት የአንድነትና የመኢዴፓ ፓርቲዎች …” በማለት ግልፅ የሆነ የስም ማጥፋት በደል ተፈፅሟል፡፡ ከሁሉ በላይ “አኬልዳማ” የተባለው የኢህአዴግ ፕሮፓጋንዳ በፍርድ ቤት የተያዘን ጉዳይ በቴሌቨዥን ፍርድ የተሰጠበት ተግባር ነው፡፡ ዘገባው በህግ ጥላ ስር የሚገኙ ዜጎችን፣ ፍርድ ቤት ውሳኔ ሳይሰጥበት “አሸባሪውእከሌ” እያሉ የስም ማጥፋት ወንጀል ተፈፅሟል፡፡ አገዛዙ በህግ ሳይሆን በራሱ ሚዛን አሻባሪ ብሎ ዜጎችን የሚፈርጅ ከሆነ፣ የፍርድ ቤት አስፈላጊነት ምኑ ላይ ነው? የፍርድ ቤት ነፃነትስ ከየት ይመጣል?

በእነ አቶ አንዱዓለም አራጌ ክስ የፍርድ ሂደት እንዳስተዋልነው ስርዓቱ በህግ ጥላ ስር የዋሉ ዜጎችን መብት በመጣስ ወደር የሌለው ነው፡፡ ከታሳሪዎቹ አንዱ የሆኑት አቶ ናትናኤል መኮንን በማዕከላዊ እስር ቤት መርማሪዎች ከፍተኛ የሆነ የአካልና የአምሮ ስቃይ ደርሶቧቸዋል፡፡ አቶ ናትናኤል የደረሰባቸውን ግፍ ለፍርድ ቤቱ ቢያስረዱም ወዲያው ሊታይላቸው አልቻለም፡፡ ይህንን ክስ ለሚያየው ፍርድ ቤት “አኬልዳማ” በሚል በኢ.ቲ.ቪ. የቀረበው ዝግጅት ተከሳሾችን ወንጀለኛ የሚያደርግ ነው በሚል አቤቱታ ቢቀርብም፣ ፍርድ ቤቱ ወዲያው ሊመለከተው አልፈቀደም፡፡ “አኬልዳማ” በሚለው የኢ.ቲ.ቪ. ትረካ ላይ የተመለከትናቸው የፓርቲ አመራሮችና አባላት ቃለ-መጠይቅ በታሳሪዎቹ ሙሉ ፍቃደኝነትና ያለምንም ተፅኖ የተደረገነው ብለን ለማመን እንቸገራለን፡፡

ከዚህ ቀደም ብዛት ያላቸው የኢህአዴግ አባላትና አመራሮች ወደ ኦነግ እንደተቀላቀሉ ይታወቃል፡፡ የደንህነትና የመከላከያ አባለት የነበሩ ዜጎች በገፍ ወደ ኦነግና ግንቦት 7 የገቡበት ሁኔታ እንዳለ የአደባባይ ምስጥር ነው፡፡ በኢ.ቲ.ቪ. እይታና አመክንዮ ከተሄደ ኢህአዴግም ሆነ መከላከያ አሸባሪዎች ናቸው ማለት ነው፡፡ አንድነት ፓርቲ አባላቱ የሚተዳደሩበት ግልፅ ህገ-ደንብ ያለው ፓርቲ ነው፡፡ በህገ-ደንቡ በግልፅ እንደተቀመጠው የአንድነት ፓርቲ አባል ሆኖ የሌላ ፓርቲ አባል መሆን የተከለከለ ነው፡፡

አንድነት ፓርቲን በአሸባሪነት ስም ጥላሸት እየቀቡ ፓርቲውን ከሕዝብ ለመነጠል የሚደረግ እኩይ ተግባር ሊቆም ይገባል፡፡ አገዛዙ በእንዲህ ዓይነቱ ርካሽ ፕሮፓጋንዳ ከሕዝብ የማገኘው ጥቅም አለ ብሎ ካሰበ ተሳስቷል፡፡ በሌላ በኩል ኢ.ቲ.ቪ. ከእንዲህ ዓይነቱ በጥላቻ የታጨቀ አሰነዋሪና የወረደ ዘገባ ማስተላለፉ ከፍተኛ የሆነ የዕውቀት፣ የስነ ምግባር፣ የሞራል ውድቀት ላይ እንደሚገኝ ማሳያ ነው ብለን እናምናለን፡፡

ኢህአዴግ በነፍጥ ትግሉ ወቅት “ጭቆና ካለ፣ ትግል ይኖራል” የሚለውን መፈክር ማስተጋባት የሚስተካከለው አልነበረም፡፡ ህወሓት በረሃ በነበረበት ዘመን ባንክ ይዘርፍ እንደነበር በየአደባባዩ በኩራት የሚያወራው ጉዳይ ነው፡፡ እንዲህም ሆነ አንድነት ዘረፋና ግድያ ለፖለቲካ ዓላማ ማሳኪያ ተገቢ መንገድ ነው ብሎ ሰለማያምን በኢትዮጵያ የሠላማዊና ሕጋዊ የትግል ስልት የተሻለ አማራጭ ነው የሚለው፡፡

አንድነት ፓርቲን በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ከሻብያ ጋር ለማገናኘት መሞከር ከርካሽ የማጥላላት ፕሮፓጋንዳነት አያልፍም፡፡ የሕዝቡንም የማገናዘብ ችሎታ የናቀ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ካሳለፈችው ረጅም የታሪክ ዘመን አንፃር ሲታይ የሀገር ጥቅምን በሚመለከት እንደ ኢህአዴግ የታማኝነት ክፍተትና የሕዝብ ቅሬታ ያለበት ፓርቲ የለም፡፡ የኢህአዴግ አሰኳል የሆነው ህወሓት ከተመሰረተበት ጊዜ ጀምሮ እስካሁን በኤርትራ ጉዳይ ላይ እያራመደው ያለው አቋም ሀገራችንን ትልቅ ዋጋ አስከፍሏታል፡፡ ሀገራችንን ወደብ አልባ እንድትሆን ያደረገው፣ ስልጣንን እንጂ የሀገርን ጥቅም ማዕከል አድርጎ ያለመሄድ በሽታ ነው፡፡

ይህ አልበቃ ብሎ ሻብያ የሀገራችንን ሉዓላዊነት በእብሪት ጥሶ በወረረበት ወቅት፣ በስልጣን ላይ ያለው አገዛዛ የኢትዮጵያን ዘላቂ ጥቅም አስጠብቆ የሻብያን አጀንዳ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ መዝጋት እንዳይቻል አድርጎአል፡፡ በወቅቱ አገዛዙ ተጠሪነቱ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ሳይሆን ለምዕራብ አገሮች አለቆቹ መሆኑን ያስመሰከረበት ወቅት ነበር፡፡ በውጤቱም አገዛዙ ለሻብያ መሪዎች በስልጣን ላይ መሰንበት ከፍተኛ ሚና ተጫውቷል፡፡ ለሀገራችን ሉዓላዊነት የተሰዉ ጀግኖቻችን ደም ደመ-ከልብ አድርጎታል፡፡ በዚህ ሚዛን ኢህአዴግ ለሀገር አንድነትና ሉዓላዊነት በቁርጠኝነት የሚታገለውን አንድነት ፓርቲን ከሻቢያና ከሸብርተኝነት ጋራ ለማገናኘት መሞከር ታላቅ ሰህተት ከመሆንም አልፎ ይህን ክስ ለመሰንዘር የሞራል ብቃት የለውም፡፡ ይህን ሀቅ የኢትዮጵያ ሕዝብ ጠንቅቆ ያውቀዋል፡፡

እንደሚታወቀው አሳሪና አሰፈሪ የሆነው የፀረ-ሽብርተኝነት ህግ የሀገሪቷ ህግ ሆኖ ፀድቋል፡፡ ይሁን እንጂ ህጉ ሀገራችን ውስጥ መፈጠር አለበት ብለን ለምናምነው የመቻቻልና የእርቅ መንገድ ትልቅ እንቅፋት ነው ብለን እናምናለን፡፡ ከሁሉ በላይ ህጉ በህገ-መንግስቱ ውስጥ የሰፈሩትን መሠረታዊ የመደራጀትና ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ መብትን ይሸራርፋል ብለን እናምናለን፡፡ ስለሆነም በህጋዊ መንገድ ህጉ እንዲቀየርና እንዲሻሻል አንድነት ፓርቲ በፅናት ይታገላል፡፡

እንዳለመታደል ሆኖ አሁንም በሀገራችን በሰለጠነ መንገድ የተለያዩ ሃሳቦችን ለማስተናገድ የሚችል ስርዓት መገንባት አልተቻለም፡፡ ህዝብ የተሻለውን የሚመርጥበት ስርዓት አልተመሠረተም፡፡ አሁንም አንዱ አንዱን በደመኝነት፣ በእልህ፣ በጥላቻና በጠላትነት ፈርጆ ለማጥፋት ቀን ከለሊት የሚሰራበት ሁኔታ ውስጥ ነን፡፡ በዚህ የመጠፋፋት ፖለቲካ ሀገር፣ ሕዝብና ፓርቲዎች ተጠቃሚ ሊሆኑ አይችሉም፡፡

አንድነት ፓርቲ አሁንም በስልጣን ኮርቻላይ ለተፈናጠጠው ኢህአዴግ የሚያቀርበው ጥሪ በስለላና በመከላካያ መዋቅር ከመተማመን ይልቅ፣ ጊዜው ሳይረፍድ በዚች ሀገር እውነተኛ ዴሞክራሲዊ ስርዓትና የህግ የበላይነት የሚከረበት ሁኔታ እንዲሰፍን ጠንክሮ እነዲሰራ ነው፡፡ አገዛዙ የሕዝብን የለውጥ ፍላጎት በሰለላና በጦር ኃይል እጨፈልቃለሁ የሚል አምባገነናዊ አካሄድ የቁልቁል ጉዞ ነው፡፡ የጊዜ ጉዳይ ካልሆነ በቀር ተሸናፊ መስመር ነው፡፡የኢህአዴግ አባላትም አመራሩ እየተንደረደረ እየሄደበት ካለው የመቀመቅ ጉዞ፣ ሀገርንም ፓርቲውንም አይጠቅምምና ተመለስ ሊሉት ይገባል፡፡

የአገዛዙ ሟርተኛ ፕሮፓጋንዳ ሕዝብን የሚያሸብርና ወደ ደም መቃባት የሚወሰድ የእልህ ጉዞ ነው፡፡ የገዥው ፓርቲና የሀገር ጥቅም አንድ አንዳልሆነ ሊገባው ይገባል፡፡ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ሀገራችን ካለችበት የፖለቲካ አዙሪት አንድትወጣ ከፍርሃት ራሳችንን አውጥተን እጅ ለእጅ ተያይዘን ለዴሞክራሲና ለህግ የበላይነት የሚደረገውን ትግል ተጠናክሮ እንዲቀጥል አንድነት ፓርቲ እንደሁልጊዜው ጥሪውን ያስተላልፋል፡፡

አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ (አንድነት)
ህዳር 20 ቀን 2004 ዓ.ም.
አዲስ አበባ