የሕገ-መንግሥት ጥሰቱና ገደብ የለሽ አምባገነንነቱ እየጨመረና እየባሰበት ነው!! ከአንድነት ፓርቲ የተሠጠ መግለጫ

በመርህ ደረጃ የምናውቀውና በትምህርት ቤት የተማርነው ሰዎች ከታሪክ ይማራሉ በዚህም ስህተቶች እየታረሙ ይሄዳሉ፣ አይደገሙም የሚል ነው፡፡ ነገር ግን የሕይወት እንቆቅልሽና በተግባር ስናየው ታሪክ፣ የሚያስተምረን፣ ሰዎች ከታሪክ የማይማሩ መሆናቸውን መሆኑ የሚያስገርም ነው፡፡ ይበልጥ አስገራሚው ደግሞ ሰዎች እንኳን ከአለፈ ከታሪክና በፊት ለፊት ከሚያዩት፣ ከሚሰሙትና ከሚያውቁት እውነታም እንደማይማሩ ነው፡፡ በተለይም አምባገነኖች፤ ጥቂቱንና የቅርቡን ለመጥቀስ፤ የግብፁ ሙባረክ ከቱኒዚያው በንዓሊ አልተማሩም፡፡ የሊቢያው ጋዳፊ ከግብጹ ሙባረክ አልተማሩም፡፡ የየመኑ ዓሊ አብደላ ሳሊሕና የሶሪያው በሸር አልአሳድ ከጋዳፊ የተማሩ አይመስሉም፡፡ እንዲህ እንዲህ እያለ አንዱ ከሌላው የማይማር መሆኑ የቀጠለና የማያቋርጥ ክስተት እየሆነ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት ከምንም በላይ ግልጽ ሆኖ የመጣው ጉዳይ ከአለፈ ታሪክ፣ እንዲሁም ከፊት ለፊት ከሚያዩትና ከሚሰሙት አለመማር የአምባገኖች አንዱ ዓይነተኛ ባህሪ መሆኑ ነው፡፡

ከላይ በመንደርደሪያ የጠቀስናቸው አስተያየቶች ያለ ምክንያት አይደለም፡፡ በአገራችን ሥልጣን ላይ ያለው መንግሥትና የገዢው ፓርቲ እያደር እየታረመ፣ እየተማረ፤ እየሰከነና ልብ እየገዛ ይመጣ ይሆናል እያልን ስለ አገር፣ ስለ ሕዝብና ስለ ራሱም ብሎ የሕግ የበላይነት እንዲያስከብር ደጋግመን ሳንሰለች ስንጎተጉተው ብንከርምም ሰሚ ጆሮ አልተገኘም፡፡ እንዲያውም ይባስ ብሎ አምባገነኑ መንግሥት ሲፈልግ በየጊዜው በሚያወጣቸው አሳሪና አስፈሪ አዋጆች ከፈለገም ያለምንም አዋጅ በጠራራ ፀሐይ ሕገ-መንግሥቱን በጉልበት እየጣሰ ነው፡፡ ዜጎችን አክብሮ መከበር ለመንግሥት ባዕድ ነገር ሆኗል፡፡ መንግሥት በዜጎች ላይ ለሚያደርሰው ጉዳት ተጠያቂነት የለበትም፡፡ ‹‹ማንኛውም ሰው ሰብዓዊ ክብሩና መልካም ስሙ የመከበር መብት አለው›› የሚለው የሕገ-መንግሥቱ አንቀጽ 24 ተ.ቁ 1 የወረቀት ላይ ጌጥ ሆኖ ነው የቀረው፡፡ በመሆኑም መንግሥት ያለምንም ጥንቃቄና ማስተዋል ከጳጉሜ 2ዐዐ3 ዓም ጀምሮ የሠላማዊና ሕጋዊ ፖለቲካ አራማጆችንና ነፃ ጋዜጠኞችን በሽብርተኝነት ከሶ ወደ ወህኒ ቤት አውርዷቸዋል፡፡ ታሳሪዎቹ በቁጥጥር ሥር ከዋሉ በኋላ በአንድ በኩል በታክስ ከፋዩ ሕዝብ ገንዘብ የሚንቀሳቀሱት ቴሌቪዥኖች ሬዲዮኖችና ጋዜጦች በሕገ-መንግሥቱ አንቀጽ 2ዐ ተ.ቁ 3 የተከሰሱ ሰዎች ‹‹በፍርድ ሄደት ባሉበት ጊዜ በተከሰሱበት ወንጀል እንደ ጥፋተኛ ያለመቆጠር . . . መብት አላቸው›› የሚለውን በመጣስ አሸባሪነታቸው የተረጋገጠ እንደሆነ በአደባባይ ሲገልጽ ከርሟል፡፡ አሁንም እየገለጽ ነው፡፡

ከሁሉም በላይ የሚያሳዝነው ደግሞ ሕገ-መንግሥቱን የማሰከበርና የማስጠበቅ ኃላፊነትን በቃለ-መሀላ የተቀበሉት ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ጥቅምት 9 ቀን 2ዐዐ4 ዓም ፓርላማ ተገኝተው በአደረጉት ንግግር በሽብር ተጠርጥረው ከተያዙት ተከሳሻች መካከል አንድም ሰው ማስረጃ ያልቀረበበት የለም ብለዋል፡፡ አልፈው ተርፈውም ሁሉም ተከሳሾች በበቂና በአሳማኝ ሁኔታ ወንጅለኛ ሆነው ስለተገኙ ነው በቁጥጥር ሥር የዋሉት በማለት በሕግ በሚያሰጠይቃቸው መልኩና በተለመደው ማንአለብኝነት የሕገ መንግሥቱን አንቀጽ ጥሰውታል፡፡ የሚገርመው ጉዳዩ ግን እንዲህ ዓይነቱ ማረጋገጫ ከተሰጠባቸውና አለአግባብ ከተንገላቱት ሰዎች መካከል አራት ሰዎች በቅርቡ መፈታታቸው ነው፡፡ የተነገረውና እውነታው ሰማይና ምድር ያህል የተለያየ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ የሌሎቹም ተከሳሾች ጉዳይ ከዚህ የተለዬ አይደለም የሚል እምነት አለ፡፡ ተከሳሾቹን እኛ የምናውቃቸውና የምንመሰክርላቸው በሠላማዊ ትግል ተምሳሌትነታቸው ነው፡፡ ዛሬም ድምፃችንን ከፍ አድርገን እንዲፈቱ እንጠይቃለን፡፡

ህዳር 9 ቀን 2ዐዐ4 ዓም በፌዴራል ማረሚያ ቤቶች (ቃሊቲ) የተፈፀመው የአምባገነኖች የሕገ-መንግሥት ጥሰት ደግሞ አንድ ሌላ ተጨማሪ ማስረጃ ነው፡፡ በእለቱ የማረሚያ ቤቱን ሕግ መሠረት በማድረግ የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ (አንድነት) ሊቀመንበርና ሁለት ም/ሊቀመናብርት፣ የፓርቲው የሥራ አስፈፃሚና የብሔራዊ ም/ቤት አባላት በቃሊቲ በመገኘት በሽብርተኝነት ተጠርጥረው የታሰሩትን የፓርቲውን አባላት፣ የመድረክ አባል ፓርቲ አባላትና ጋዜጠኞችን ለመጠየቅ 6፡ዐዐ ሰዓት ላይ በቃሊቲ በመገኘት ከሕዝብ ጋር ተራ ይዘው ወደ ግቢው ቢገቡም በእስር ቤቱ ኃላፊዎች የተለመደ የማንአለብኝነትና የአምባገነንነት መንፈስ የሕገ-መንግሥቱን አንቀጽ 21 በጥበቃ ሥር ያሉና በፍርድ የታሰሩ ሰዎች መብት በሚለው ስር ተ.ቁ 2 ‹‹ ከትዳር ጓደኞቻቸው፣ ከቅርብ ዘመዶቻቸው ከጓደኞቻቸው (ስርዝ የተጨመረ) . . . ጋር ለመገናኘትና እንዲጎበኛቸውም እድል የማግኘት መብት አላቸው›› የሚለው ተጥሶ ጥየቃውን ተከልክለዋል፡፡ ይህ ዓይነቱ ጥሰት ተገቢ አይደለም በማለት ከኃላፊዎቹ ጋር የተሞከረው ውይይት ሊሳካ አልቻለም፡፡ ምናልባትም የዓይናችሁ ቀለም ስለአላማረን ነው የማትገቡት የሚለው አባባል እዚህም ሊጠቀስ ይችል ይሆናል፡፡ እንደዚህ ዓይነቱ የሕገ-መንግሥት ጥሰት አዲስ አይደለም፡፡ ከዚህ የባሱ የሕገ-መንግሥት ጥሰቶች በከፋና በሚጎዳ ሁኔታ እየተፈፀሙ ነው፡፡ መንግሥት በሕዝብ ስም በአደራ የያዘውን ሥልጣን ለሕዝብ ማጥቂያ እየተጠቀመበት ነው፡፡ በሕግ ሽፋን ሕዝብን የማጥቃት ዘመቻ እያካሄደ ነው፡፡

የዚህ መግለጫ ዋና ዓላማ ምንም ቢዘገይ የመንግሥትን ሥልጣን የያዘው ገዢው ፓርቲ ቆም ብሎ በሰከነ አዕምሮ ስለአገርና ስለ ሕዝብ፤ ስለ ሕገ-መንግሥታዊነት እንዲያስብበት ለማሳሰብ ነው፡፡ እኛ ኢትዮጵያዊን እንደ ሌሎች ሕዝቦች ሁሉ ጉልበተኝነትንና ጥቃትን አምርረን እንጠላለን፡፡ እንታገለዋለንም፡፡ ትግላችንም ጥቃትንና ጉልበተኝነትን ከአገራችን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለማስወገድ ነው፡፡ ኢህአዴግአዊያን ግን ጉልበተኝነትን፣ አምባገነንነትን፣ ጥቃትን፣ እንቃወማለን ሲሉ ‹‹ብሶት የወለደን ነን ሲሉ›› ጉልበተኝነትን፣ አምባገነንነትን፣ ጥቃትን ከአገር ለማጥፋት ሳይሆን እራሳቸውን አዲስ አጥቂዎች፣ አምባገነኖች፣ ጉልበተኞች ለማድረግና ሌሎችን ለመበደልና ለማጥቃት ነው፡፡ አውቀውም ሆነ ሳያውቁ ብሶት የወለዳቸው መሆናቸው ቀርቶ ብሶት የወለደው ሕዝብ እየፈጠሩ ነው፡፡ በእኛ በኩል ኢህአዴግ ከታሪክ ባይማርም ከራሱ ታሪክ በመነሳት ብሶት የወለደው ሕዝብ አምባገነኖችን እንደሚያስወግድ እንገነዘባለን፡፡

ትግላችን ለእኩልነት፣ ለነፃነት ለእድገትና ብልጽግና ነው፡፡ ከሁሉም በላይ ለሕጋዊነትና ለሕገ-መንግሥታዊነት ነው፡፡ የነፃነቶችና መብቶች መከበር ለእድገትና ብልጽግና ቁልፍ ናቸው፡፡ የነፃነት በርን ጠርቅሞ ዘግቶ ሕገ-መንግሥትን እየደፈጠጡ ስለ ልማት መለፈፍ ትርጉም የለውም፡፡ ሂውማን ደቨሎፕሜንት ኢንዲክስ እንደሚያሳየው ከሆነ በ2ዐ11 ኢትዮጵያ ከ185 አገሮች መካከል በእድገት 174ኛ ደረጃ ላይ ነች፡፡ በዓለም ላይ በእድገት የምትበልጠው 11 አገሮችን ብቻ ነው፡፡› በብልጽግና ደረጃም ቢሆን ኢትዮጵያ ለግምገማ ከቀረቡ 11ዐ አገሮች መካከል 1ዐ4ኛ ነች፡፡ ከዓለም በብልጽግና የምትበልጣቸው 6 አገሮች ብቻ ናቸው፡፡ በዴሞክራሲ ደረጃም የለየላት በአምባገነን ሥርዓት ሥር ያለች አገር መሆኗን ጥናቱ ያሳያል፡፡ ወደድንም ጠላንም እውነታው ይህው ነው፡፡ አውቀን እንታረም፡፡ ይህ በተሳሳተ የታሪክ ጎዳና መጓዝ ለአገርም፣ ለሕዝብም ለኢህአዴግም ከባድ ዋጋ የሚያስከፍል እንዳይሆን እንጠንቀቅ እያልን ባንደማመጥ ደግመን ደጋግመን እንናገራለን፡፡

አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ (አንድነት)
ህዳር 14 ቀን 2ዐዐ3 ዓም
አዲስ አበባ