የምስጋና መልእክት ለብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን
ቀን፦ ጥቅምት 19/2003 ዓ.ም
የምስጋና መልእክት ለብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት
እኛ በዲሲና አካባቢው ሀገረ ስብከት ሥር የምንገኝ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪዎች፤ ሰባክያነ ወንጌል፤ የሰንበት ትምህርት ቤትና የምዕመናን ተወካዮች በጥቅምት 17/ 2003 ዓ.ም የሀገረ ስብከታችን ሊቀ ጳጳስ የሆኑት የብፁዕ አቡነ አብርሃም የዝውውር ሀሳብ ለቅዱስ ሲኖዶስ ጉባዔ መቅረቡ አግባብና ወቅታዊ አለመሆኑን አስመልክተን ለእናንተ ለብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት ያቀረብነውን የተማጽኖ መልዕክት ብፁዓን አባቶቻችን፤ ታናናሾች የምንሆነውን የእኛ የልጆቻችሁን ልመናና የተማጽኖ ጩኸት ሳትንቁ አክብራችሁ በመቀበል በልመናችን መሠረት ግራ ቀኙን ተመልክታችሁ ጥቅሙንና ጉዳቱን አመዛዝናችሁ ብፁዕ አባታችን አቡነ አብርሃም የጀመሩትን ሥራ እንዲፈጽሙ በሀገረ ስብከታቸው እንዲቆዩ በመወሰናችሁ በተሰማን ከፍተኛ ደስታ ይህን የምስጋና መልእክት ለመጻፍ በቅተናል።
ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፦ በውሳኔያችሁ ተደስተናል። ምስጋናችንም ከፍ ያለ ነው፡፡ በአባቶቻችን እንድንመካና እንድንኮራም አድርጎናል፡፡ በእናንተ አርቆ አስተዋይነት በተወሰነው ውሳኔም ተደስተናል፡፡ የልጆቻቸውን ልመናና ተማጽኖ ሰምተው ተግባራዊ የሚያደርጉ አባቶችን ያላሳጣን እግዚአብሔር አምላክ የተመሰገነ ይሁን፡፡ ለብፁዓን አባቶቻችን ለእናንተ ሰፊ ዘመናትን ረዥም ወራትን ይስጥልን፡፡
በዲሲና አካባቢው ሀገረ ስብከት ሥር የምንገኝ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን
አስተዳዳሪዎች፤ ሰባክያነ ወንጌል፤ የሰንበት ትምህርት ቤትና የምዕመናን ተወካዮች
ጥቅምት 19/2003 ዓ.ም