ኢትዮጵያ ሶማሊያን ዳግም መውረሯ ፍጹም ትክክል አይደለም ሲሉ በአሜሪካ ስቴት ዲፓርትመንት የአፍሪካ ተጠሪ የሆኑት ጆኒ ካርሰን ተናገሩ

የኢትዮጵያ ጦር ወደሶማሊያ ግዛት ዘልቆ መግባቱን ተከትሎ በአሜሪካ ስቴት ዲፓርትመንት የአፍሪካ ተጠሪ የሆኑት ጆኒ ካርሰን ኢትዮጵያ ሶማሊያን ዳግም መውረሯ ፍጹም ትክክል አይደለም ሲሉ ተናገሩ። ጆኒ ካርሰን ይህን የተናገሩት ማክላቺ ከተባለው ጋዜጣ ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ነው።

ካርሰን ኢትዮጵያ ከአራት አመት በፊት ሶማሊያን በመውረር ለሁለት አመታት ያክል በአገሪቱ ውስጥ ብትቆይም፣ በመጨረሻ አልሸባብን ከመፍጠር በስተቀር ያመጣቸው ውጤት እንደሌለ ገልጸውና በሶማሊያ ሰላም ለማምጣት ማንኛውም እንቅስቃሴ በአፍሪካ ሰላም አስከባሪ በኩል መካሄድ እንዳለበት በመግለጥ የኢትዮጵያን እንቅስቃሴ በእጅጉ ነቅፈዋል።

የዘረኛውና አምባገነኑ መለስ አገዛዝ ቀደም ብሎ በተለይም የ1997 ምርጫን ተከትሎ በሃገሪቱ ተከስቶ የነበረውን ውጥረት አቅጣጫ ለማስቀየር በሶማሊያ ላይ ወረራ ፈጽሞ እንደነበር የሚታወስ ሲሆን ኢትዮጵያዊያን ወታደሮች ሶማሊያ ውስጥ ተገድለው አስከሬናቸው በመንገድ ላይ እስከሚጎተት መደረሱና የኢትዮጵያም ጦር ሶማሊያን ለቆ መወጣቱ አይዘነጋም።

የፋሽስቱ መለስ አገዛዝ በድጋሜ ሶማሊያን ለመውረር ለምን እንደፈለገ ግልጽ ባይሆንም፣ የፖለቲካ ተንታኞች የወያኔ አገዛዝ በምርጫ 97 ማግስት ከፍተኛ ውጥረት ውስጥ መግባቱን ተከትሎ፣ የህዝቡን የትኩረት አቅጣጫ ለማስለወጥ ሲል ሶማሊያን መውረሩን በማስታወስ፣ አሁንም በኢትዮጵያ ውስጥ የሚታዬው የህዝብ መከፋት እየጨመረ መምጣት ስጋት ላይ እየጣለው በመምጣቱ ተመሳሳይ እርምጃ ለመውሰድ መፈለጉን ያሳያል ይላሉ። እነዚህ ወገኖች እንደሚሉት መንግስት ራሱን በጦርነት ውስጥ እንደሆነ አድርጎ በማቅረብ በአገር ውስጥ የሚካሄደውን ተቃውሞ በጸረ ሽብር ትግል ስም ለመጨፍለቅ እንዲመቸው ለማድረግ የወሰደው እርምጃ ነው።

በሌላ በኩል ደግሞ የአካባቢው አገሮች በተለይም ዩጋንዳና ኬንያ በሶማሊያ ውስጥ ያላቸው ጉልበት እየጨመረ መምጣቱን ተከትሎ፣ የፋሽስቱ መለስ አገዛዝ ከምእራቡ አለም የሚያገኘው የዲፕሎማሲና የገንዘብ ድጋፍ እንዳይቋረጥ በመስጋት የወሰደው እርምጃ ነው የሚሉ አሉ።

እንደ ማክላቹ ጋዜጣ ከሆነ ሶማሊያውያን የኢትዮጵያ ጦር ወደ አገራቸው መግባቱን አይደግፉም። የአልሸባብን አስተዳደር በርካታ ሶማሊያውያን እንደሚጠሉት ያስታወሰው ጋዜጣው ፣ አንዳንዶች የኢትዮጵያ ጦር ሶማሊያ ከሚገባ አልሸባብ ይግዛን እስከማለት መድረሳቸውን ገልጧል።

የኢትዮጵያ ጦር ወደ ሶማሊያ መግባቱ እውነት መሆኑ በስፋት እየተዘገበ ባለበት ባሁኑ ሰ አት ፣ የፋሽስቱ አገዛዝ እንደተለመደው አይኔን ግምባር ያድርገው በማለት አሁንም ጦሩ ወደ ሶማሊያ መግባቱን ያስተባብላል።